በቀረውስ፥
ወንድሞች ሆይ፥ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን አስቡ፤ ፊልጵስዩስ 4፡8
ለተሳካ ምድራዊ ህይወት የህይወትን ህግ ጠብቀን
መራመድ እንዳለብን ሁሉ ለተሳካ የክርስትና ህይወት ለመኖር እንደ መፅሃፍ ቅዱስ ስርአት አእምሮዋችንን መግራት ይገባናል፡፡ ሃሳብ
በእግዚአብሄር ቃል መፈተን አለበት፡፡ የእግዚአብሄር ፈቃድን ሃሳብ ፈትነን ማወቅ አለብን፡፡
የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። ሮሜ 12፡2
ለማንኛውም ነገር የሚሰራና የማይሰራ ህግ እንዳለው
ሁሉ ለአስተሳሰብ ህይወታችንም የሚሰራና የማይሰራ መንገድና ህግ አለ፡፡ ለማንኛውም ውጤትና ፍሬያማነት ህግን ጠብቀን መራመድ እንዳለብን
ሁሉ ለክርስትና ህይወታችን ፍሬያማነት የአስተሳሰብን ህግን መጠበቅ ግዴታ ነው፡፡
ሰው በልቡ እንደሚያስበው እንዲሁ ነው፡፡ እንደሚያስብው
እንዲሁ ነውና፡፡ ሰላምን የሚያስብ ሰላማዊ ይሆናል፡፡ ክፋትን የሚያስብ ሰው ክፉ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡
በልቡ እንዳሰበ እንዲሁ ነውና፤ ምሳሌ 23፡7
ለብዙ ነገር ህግ እንዳለ ሁሉ ለአስተሳሰብ ህይወታችንም
ህግ አለው፡፡ እያንዳንዱ ነገር በትክክል የሚሰራበትና የማይሰራበት መንገድ
እንዳለው ሁሉ አእምሮዋችን በትክክል የሚሰራበትና የማይሰራበት መንገድ አለው፡፡
በማንኛውም ነገር የማይደረግና ህግ የሚከለክለው
ነገር እንዳለ ሁሉ በአስተሳሰባችንም ማሰብ ያለብንና ማሰብ የሌለብን ነገሮች አሉ፡፡ በማንኛውም ነገር ጠቃሚ ነገር እንዳለ ሁሉ
በአስተሳሰባችንም የሚፈቀድና ጠቃሚ አስተሳቦች አሉ፡፡
የመፅሃፍ ቅዱስ የአስተሳሰብ ህግ ከተከተልን ህይወታችን
ይባረካል፡፡ የመፅሃፍ ቅዱስ የአስተሳሰብ ህግ ካልተከተልን ግን ህይወታችን ካለ ፍሬ ይቀራል፡፡
የሰው አስተሳሰብ ወሳኝ የህይወት ክፍል ነው፡፡
መፅሃፍ ቅዱስ ወደ አእምሮዋችን የሚመጣውን ነገር ሁሉ እንዳናስብ ያስጠነቅቀናል፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ ለአስተሳሰብ ህይወታችን ህግ እንዲኖረን
ያስተምራል፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ ለማሰብ የምንፈቅድለትና የማንፈቅድለት ነገር እንዳለ መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምረናል፡፡
መፅሃፍ ቅዱስ ፍሬያማ የሚያደርገን ሃሳቦች እንዳሉና
ህይወታችንን የሚያበላሹ አደገኛ ሃሳቦች እንዳሉ ያስተምረናል፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ አስተሳሰባችን በእነዚህ መመዘኛዎች ተመዝነው ያለፉ
ብቻ እንዲሆኑ መፅሃፍ ቅዱስ ያዛል፡፡ እነዚህን መመዘኛዎች ያላሟላ ነገር ማሰብ እንደሌለብን መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡
በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ እውነተኛ የሆነውን
ነገር ሁሉ፥ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥
መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን አስቡ፤ ፊልጵስዩስ 4፡8
እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥
ሰይጣን የውሸት አባት ነው፡፡ ሰይጣን ሊሰርቅ
ሊያርድ ሊያጠፋ ይመጣል፡፡ /ዮሃንስ 10፡10/ ሰይጣን የሰውን ህይወት የሚያጠፋው ውሸትን እንዲያምኑ በማድረግ ብቻ ነው፡፡ ሰይጣን
ሄዋን እንድትወድቅ ያደረገው ውሸትን እንድታምን በማድረግ ነበር፡፡ እውነተኛ የሆነውን ነገር ብቻ ማሰብ ህይወታችንን ከጠላት ይጠብቃል፡፡
የእግዚአብሄር ቃል እውነት ነው፡፡ እንደ እግዚአብሄር ቃል የሆነ ነገር ሁሉ እውነት ነው፡፡ እንደ እግዚአብሄር ቃል ያልሆነን ነገር
ማሰብ ህይወትን ለጥፋት አደጋ ያጋልጣል፡፡
ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥
ጭምትነት ማለት ጨዋነት ፣ ረጋ ማለት ፣ ንፁህ
ላልሆነ ጥቅም አለመስገብገብና ኩሩ መሆን ማለት ነው፡፡ አስተሳሰባችን ረጋ ያለ ሊሆን ይገባዋል፡፡ የሰይጣንና የእግዚአብሄር ድምፅ
የሚለይበት መንገድ ሰይጣን ይስቸኩላል እግዚአብሄር ግን በእረፍት ውሃ ዘንድ ይመራል፡፡ ሰይጣን ያዋክባል እግዚአብሄር ግን በዝምታ
ያሳምናል፡፡ ሰይጣን አሁን ካላደረህክ ያመልጥሃል ይላል፡፡ እግዚአብሄር ግን ተናግሮ እስክትረዳው ይጠብቃል፡፡
እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል። ራእይ 3፡20
ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥
ፅድቅ እውነት እና ትክክለኛውን ነገር ውስጣችን
ያውቀዋል፡፡ እውነተኝነትንም ማሰብ ከእግዚአብሄር ጋር እንድንወግን ያደርገናል፡፡ ትክክለኛውን ነገር አለማድረግ ደግሞ ከእግዚአብሄር
ተቃራኒ እንድንሆን ያደርገናል፡፡
ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥
ሰው በተፈጥሮው ንፁህን ምግብ ካልበላ እንደሚታመም
ሁሉ ሰው ንፁህን ነገር ብቻ ካላሰበ መንፈሳዊ ህይወቱ ይቆሽሻል፡፡ ሰው ሊያቆሽሸው የሚመጣውን ሃሳብ እንቢ ካላለ በስተቀር ከእግዚአብሄር
ጋር ያለው ግንኙነት ያበላሽበታል፡፡ ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ የሚለው፡፡
በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፥ እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፤ ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። 2ኛ ቆሮንቶስ 11፡2-3
ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥
ጥላቻ ከእግዚአብሄር አይደለም፡፡ የጥላቻ ሃሳብ
ከሰይጣን ነው፡፡ ሰይጣን ሰውን ሊጠቀምበት ሲፈልግ ጥላቻን ይከትበታል፡፡ ጥላቻ የገባበት ሰው ለሰይጣን ዘር ለም መሬት ነው፡፡
ስለዚህ የምናስበው ነገር እግዚአብሄርን ይሁን ሰውን እንድንጠላ ሳይሆን እንድንወድ የሚያደርገን ብቻ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ምግብ ስንበላ
መርጠን እንደምንበላ ሁሉ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ ብቻ እንድናስብ ጥላቻ ያለበትን ነገር ሁሉ በፍጥነት ከአስተሳሰብ ህይወታችን
እንድናስወግድ እግዚአብሄር ይፈልጋል፡፡
መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥
እግዚአብሄር መልካም ነው፡፡ በምንም ሁኔታ ውስጥ
ብናልፍ እግዚአብሄር ተስፋችን ነው፡፡ ወድቀን እንኳን እግዚአብሄር የሚያስበውና የሚናገረው ስለመነሳታችን ነው፡፡ ተስፋን የሚያጨልም
ሃሳብ የእግዚአብሄርን መልካምነት እንድንጠራጠር የሚያደርግ ሃሳብን ከአእመሮዋችን በፍጥነት አሽቀንጥረን መጣል ይኖርብናል፡፡
ወንድሞች ሆይ፥ እርስ በርሳችሁ አትተማሙ። ወንድሙን የሚያማ በወንድሙም የሚፈርድ ሕግን ያማል በሕግም ይፈርዳል፤ በሕግም ብትፈርድ ፈራጅ ነህ እንጂ ሕግን አድራጊ አይደለህም። ያዕቆብ 4፥11
በጎነት ቢሆን
እግዚአብሄር መልካም አምላከ ነው፡፡ እኛም ለጆቹ
ማሰብ ያለብን በጎነትን ነው፡፡ ለሰዎች መልካም ማሰብ መልካም መናገር መልካምን ማድረግ የእግዚአብሄር ልጅነት ባሀሪ ነው፡፡ ስንፈጠር
ለክፋት ስላልተፈጠረን ከበጎነት ውጭ ማሰብ ህይወታችንን ይጎዳል፡፡
ምስጋናም ቢሆን፥
ባለን መርካት ፣ ራሳችንን ማጠን ፣ ሁልጊዜ በነገር ሁሉ እግዚአብሄርን ማመስገን ከእኛ ይጠበቅብናል፡፡ ማጉረምረም
ያለበትን ነገር በማሰብ ትክክለኛውን ነገር ማደረግ እንችልም፡፡ ምስጋናን በማሰብ ደግሞ ልንሳሳት አንችልም፡፡ ምስጋና ከእግዚአብሄር
ጋር ላለን ግንኙነት ወሳኝ ነው፡፡
አእምሮዋችን ያመጣልንን ሃሳብ የምናስብ ከሆነ
እንደምናስበው እንሆናለን፡፡ አእምሮዋችንን ከጠበቅን ህይወታችንን እንጠብቃለን፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች
https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#እግዚአብሔር #ጌታ #አእምሮ
#ማደስ #መለወጥ
#መከተል #መከተል
#መምሰል #እግዚአብሔርንመምሰል
#ቃል #ተማሪ
#መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት
#ደቀመዝሙር #ቤተክርስትያን
#አማርኛ #ስብከት
#ነፍስንመካድ #መፅሃፍቅዱስ
#ተከታይ #ህይወት
#ፌስቡክ #አቢይዋቁማ
#አቢይዋቁማዲንሳ
No comments:
Post a Comment