Popular Posts

Follow by Email

Wednesday, November 22, 2017

ስለሚበላና ስለሚለበስ የሚያምን ሰው ልዩ ምልክት

ካለእምነት እግዚአብሄርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፡፡ ካለእምነት ከእግዚአብሄር ጋር መኖር አይቻልም፡፡ ካለእምነት ከእግዚአብሄር ጋር መስራት አይቻልም፡፡ እግዚአብሄር እምነትን ከእኛ ይጠብቃል፡፡ እግዚአብሄር ቃሉን እንድናምን ይፈልጋል፡፡ ከደህንነት ቀጥሎ መሰረታዊው እምነት ደግሞ እግዚአብሄር እንደሚያስፈልገን ሁሉ እንደሚያውቅና እንደሚጨምር ማመን ነው፡፡
ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡32-33
ሰው ስለሚበላው ስለሚጠጣውና ስለሚለብሰው ካመነ በነፃነት ለእግዚአብሔር መኖር ይችላል፡፡ ሰው ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ እግዚአብሄርን ካመነ በሁለንተናው እግዚአብሄርን ለማገልገል ይለቀቃል፡፡
እምነት የልብ ስለሆነ አንድ ሰው ማመኑና አለማመኑን ማወቅ ቀላል አይደለም፡፡ ነገር ግን ስለሚበላና ስለሚለበስ የሚያምን ሰውም ምልክቶች ከእግዚአብሄር ቃል መመልከት እንችላለን፡፡  
1.      ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው አይጨነቅም፡፡
ስለ መሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው ጉልበቱን የእግዚአብሄርን ነገር በመፈለግ ላይ እንጂ በጭንቀት ላይ አያፈስም፡፡ የሚያምን ሰው የጭንቀትን ፍሬ ቢስነት ይረዳል፡፡ የሚያምን ሰው በእግዚአብሄርን ፅድቅና መንግስቱን በመፈለግ ላይ ሙሉ በሙሉ ከመጠመዱ የተነሳ ለጭንቀት የሚተርፍ ትርፍ ጊዜና ጉልበት የለውም፡፡ ስለፍላጎቱ በእግዚአብሄር የሚታመን ሰው ጭንቀት ጉልበቱን እንዲበላ አይደፈቅድለትም፡፡
ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ ጌታን የማያምን ሰው የእግዚአብሄርን ስራ በሚሰራበት ጊዜና ጉልበቱ ሲጨነቅ ይውላል፡፡ የማያምን ሰው ጉልበቱን በትክክለኛው በእግዚአብሄር መንግስት ላይ ማፍሰስን አያውቅም፡፡ የማያምን ሰው ምንም ነገር በትክክል መስራት ሳይችል በጭንቀት ብቻ ካለፍሬ ይቀራል፡፡ የማያምን ሰው የሚያስጨንቀው ነገር ጌታ እንዲሆንበት ይፈቅድለታል፡፡ ስለመሰረታዊ ግፍላጎቱ የማያምን ሰው ይጨነቃል በጭንቀትም ውድ ህይወቱን ያባክናል፡፡
ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ስለ ነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት፥ ወይም ስለ ሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፤ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን? ማቴዎስ 6፡25
2.     ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው ይፀልያል፡፡
ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው ከመጨነቅ ይልቅ ይፀልያል፡፡ እግዚአብሄርን የሚያምን ሰው ይፀልያል በእምነትም ያመሰግናል፡፡ አማኝ የሚያስጨንቀውን ይጥላል በእግዚአብሄር ላይ መልሶም አይወስደውም፡፡ የሚያምን ሰው በእግዚአብሄር ይተማመናል ያርፋል፡፡  
የማያምን ሰው በመጨነቁ ትልቅ ስራ እንደሰራ ያስባል፡፡ የማያምን ሰው መፀለይ በሚገባው ጊዜ ሲጨነቅ ይውላል፡፡ የማያምን ሰው ጉልበቱንና ጊዜውን በጭንቀት ላይ ያሳልፋል፡፡ የማያምን ሰው ቢፀልይም  ጭንቀቱን መልሶ ይወስደዋል፡፡ የማያመን ሰው መጨነቁ የህይወት አንዱ ስራ ይመስለዋል፡፡ ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የማያምን ሰው ሸክሙን  በእግዚአብሄር ላይ እንዴት እንደሚጥለው አያውቅም፡፡ የማያምን ሰው በእግዚአብሄር እንዴት እንሚያርፍ አያውቅም፡፡
እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ማቴዎስ 11፡28
3.     ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው ልቡን ይሰማል፡፡
እግዚአብሄርን ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው ሞትክ አለቀልህ ጠፋህ የሚለውን የውጭውንና የአእምሮውን ድምፅ ሳይሆን የልቡን ድምፅ በዝምታ ይሰማል፡፡
በአንድ አካልም የተጠራችሁለት ደግሞ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ፤ የምታመሰግኑም ሁኑ። ቆላስይስ 3፡15
ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ በእግዚአብሄር የማይታመን ሰው በአእምሮ የሚመጣውን ሃሳብ ሁሉ ያስተናግዳል፡፡ ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ በእግዚአብሄር የማይታመን ሰው ይታወካል ሰላም የለውም፡፡
ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም። ዮሃነስ 14፡27
4.     ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው በእግዚአብሄር ይወራረዳል፡፡
ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው ይህን ካላገኘሁ አይሆንም የሚለው ፍላጎት የለም፡፡ የሚያምነ ሰው በምንም ነገር ውስጥ እግዚአብሄር እንደሚያስችለው ያምናል፡፡ ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው በከፍታም በዝቅታም በምንም ነገር ውስጥ በክርስቶስ እንደሚበረታ ያውቃል፡፡
መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። ፊልጵስዩስ 4፡12-23
ስለፍላጎቱ የሚያምን ሰው ሰው በእግዚአብሄር ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ እንደማይኖር ያውቃል፡፡
እርሱም መልሶ፦ ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል አለው። ማቴዎስ 4፡4
ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ በእግዚአብሄር የሚታመን ሰው የሌለኝ ነገር የማያስፈልገኝ ነው ብሎ በእግዚአብሄር እረኝነትና  አቅርቦት ሙሉ ለሙሉ ይታመናል፡፡
እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ። መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል። ዮሃንስ 10፡10-11
ስለፍላጎቱ የሚያምን ሰው እግዚአብሄር በሰጠው ነገር ብቻ መኖር እንደሚችል ያውቃል፡፡ ስለፍላጎቱ የሚያምን ሰው እግዚአብሄር የሰጠው ነገር ለአላማው በቂ እንደሆነ ያምናል፡፡ እግዚአብሄርን የሚያምን ሰው በእግዚአብሄር እቅርቦት ላይ ምንም ትችት የለውም፡፡
ስለፍላጎቱ በእግዚአብሄር የማየታመን ሰው ገንዘቡ ተቆጥሮ እሰካልገባ አያምንም፡፡ ስለፍላጎቱ የማያምን ሰው የሚያየውን ብቻ ያምናል፡፡
ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፥ አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል። 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡7-8
5.     ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው ከአለም ፉክክር ራሱ ያገላል፡፡
እግዚአብሄርን የሚታመን ሰው በአለም ካለ ክፉ የፉክክር መንፈስ በፈቃዱ ራሱን ያገላል፡፡ እግዚአብሄርን የሚታመን ሰው ከሌላው ጋር ተፎካክሮም ለእግዚአብሄር ኖሮም እንደማይችል ይረዳል፡፡ እግዚአብሄርን የሚያምን ሰው የፉክክርን ክፋትና አታላይነት ይረዳል፡፡
ስለፍላጎቱ ጌታን የማያምን ግን ሰው የደረሰበት ደረጃ ለመድረስ ይጥራል፡፡ ስለፍላጎቱ የማያምን ሰው በሰው ፊት ሙሉ መስሎ ለመታየትና ላለመበለጥ ይዳክራል፡፡ ስለፍላጎቱ የማያምን ሰው የሰውን ደረጃ ለማሟላት ህይወቱን ያባክናል፡፡ ስለፍላጎቱ በእግዚአብሄር የማይታመን ሰው ከጭንቀት አርፎ እግዚአብሄርን ማገልገል ያቅተዋል፡፡
በእሾህ መካከል የተዘራውም ይህ ቃሉን የሚሰማ ነው፥ የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት መታለል ቃሉን ያንቃል፥ የማያፈራም ይሆናል። ማቴዎስ 13፡22
6.     ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ ጌታን የሚያመን ሰው የተረጋጋ ህይወት አለው፡፡
ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው ከማረፍ ውጭ ሲቅበዘበዝ አይታይም፡፡ ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው አይናወጥም፡፡ ጌታን የሚያምን ሰው ለጌታ ሙሉ ለሙሉ ለመኖር ነፃ ነው፡፡ በጌታ የሚታመን ሰው የረካ በመሆኑ ሌላውን ለማርካት ይሮጣል፡፡
የምትባረክ ነፍስ ትጠግባለች፥ የረካም እርሱ ደግሞ ይረካል። ምሳሌ 11፥25
ደስ ያላት ልብ መልካም መድኃኒት ናት፤ ያዘነች ነፍስ ግን አጥንትን ታደርቃለች። ምሳሌ 17፡22
ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ በጌታ ሰላም ያለው ሰው ለሌላው ሰላምን ይሰጣል፡፡ ስለመሰረታዊ ፍለጎቱ የረካ ሰው ትኩረቱ አንድ ስለሆነ ሰላሙን ሊወስድ የሚችል ምንም ሃይል አይኖርም፡፡
ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ ያልረካ ሰው ሁለት ነገሮችን በአንድ ላይ ለማድረግ ስለሚሞክር ሁለቱንም ማድረግ ያቅተዋል፡፡ ስለፍላጎቱ በጌታ ያልታመነ ሰው ሌሎችን ስለማገልገልና ሌሎችን ስለመጥቀም ሲሰማ ቁጣ ቁጣ ይለዋል፡፡ ስለፍላጎቱ የማያምን ሰው "ምስኪን እኔ" አስተሳብ "ለእኔስ ማን አለኝ?" የሚል ምስኪንነት አስተሳሰብ አለው፡፡
ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በጽዮን ድንጋይን ለመሠረት አስቀምጣለሁ፤ የተፈተነውን፥ የከበረውን፥ መሠረቱ የጸናውን የማዕዘን ድንጋይ የሚያምን አያፍርም። ኢሳያስ 28፡16
7.     ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያመን ሰው ሰውን የበረከቱ ምንጭ አያደርግም፡፡
ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ ጌታን የሚያምን ሰው አይጣላም አይጨቃጨቅም፡፡ ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ ጌታን የሚያምን ሰው የእርሱን ነገር ከሰው ጋር አያያይዘውም፡፡
በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን?ያዕቆብ 4፡1
ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ ጌታን የሚያምን ሰው ሰውን የበረከቱ ምንጭ አያደርግም፡፡
ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የማያመን ሰው ሰውን ለመጥቀም ሳይሆን በሰው ለመጠቀም ያስባል፡፡ ስለፍላጎቱ የማያንምን ሰው ከዚህ የምጠቀመው ምንድነው ብሎ ስለግል ጥቅሙ ሁሌ ያስባል፡፡ ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ በጌታ የማይታመን ሰው የእግዚአብሄርን አቅርቦት ስለማያይ አገልግሎትን የጥቅም ማግኛ መንገድ ያደርገዋል፡፡ ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የማይታመን ሰው እግዚአብሄር ለሌሎች ጥቅም የሰጠውን የፀጋ ስጦታ በጥቅም ይቸረችረዋል፡፡ ስለፍላጎቱ የማይታመን ሰው እግዚአብሄር ለሌሎች ጥቅም የሰጠውን ነገር ሁሉ ወደግል ስሙ ያዞረዋል፡፡ ስለ መሰረታዊ ፍላጎቱ የማያምን ሰው በግል በማይጠቀምበት ምንም ነገር ውስጥ የመሳተፍ ሃሞቱ የለውም፡፡
ድውዮችን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሡ፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ አጋንንትን አውጡ፤ በከንቱ ተቀበላችሁ፥ በከንቱ ስጡ። ማቴዎስ 10፡8
8.     ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ ጌታን የሚታመን ሰው ነውረኛ ረብን ይጠላል፡፡
ስለፍላጎቱ በአግዚአብሄር የሚታመን ሰው ክቡርና ነውረኛን ጥቅምን ይለያል፡፡ በእግዚአብሄር የሚታመን ሰው በፊቱ የመጣውን ሁሉ አያግበሰብስም፡፡ ስለፍላጎቱ የሚታመን ሰው ኩሩ ነው፡፡ ስለፍላጎቱ ጌታን የሚያመን ሰው ለቀቅ ብሎ ይኖራል፡፡ በእግዚአብሄር የሚታመን ሰው ክብር ከእግዚአብሄር ብቻ እንደሚመጣ ይረዳል፡፡
ክብር ከምሥራቅ ወይም ከምዕራብ ወይም ከምድረ በዳ የለምና፤ እግዚአብሔር ፈራጅ ነውና ይህን ያዋርዳል ይህንም ያከብራል። መዝሙር 75፡6-7
ነውረኛ ረብ የማይወዱ፥ በንጹሕ ሕሊና የሃይማኖትን ምሥጢር የሚይዙ ሊሆኑ ይገባቸዋል። 1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡9
ስለፍላጎቱ የማይታመን ሰው የጥቅም ደረጃ የለውም፡፡ ስለፍላጎቱ ጌታን የማይታመን ሰው የህይወት መርህ የለውም ወደተመቸው ይገለባበጣል፡፡ ስለፍላጎቱ የማይታመን ሰው ጥቅም ይሁን እንጂ የሚንቀውና እንቢ የሚለው ነገር የለም፡፡ በእግዚአብሄር የማይታመን ሰው እግዚአብሄር በክብር እንደሚባረክ አይረዳም፡፡  
አምላኬም እንደ ባለ ጠግነቱ መጠን በክብር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ይሞላባችኋል። ፊልጵስዩስ 4፡19 
የክርስትናም የመጨረሻ ደረጃና የስኬት ጣራ ስለመሰረታዊ ፍላጎት ጌታን ታምኖ ጌታን መከተል ነው፡፡ 
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#መሰረታዊፍላጎት #ነፃነት #አትጨነቁ #ቅድሚያ #ምንእንበላለን #ምንእንጠጣለን #ምንእንለብሳለን #አስቀድማችሁ #ፅድቁን #የአለምሃሳብ #የባለጠግነትማታለል #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ምህረት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment