Popular Posts

Tuesday, November 21, 2017

የእምነት አቡጊዳ

ከእግዚአብሄር ጋር ለመገናኘት እምነት ወሳኝ ነው፡፡ ካለእምነት ከእግዚአብሄር ጋር ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ ካለእምነት ከእግዚአብሄር ጋር መኖር አይቻልም፡፡ ካለእምነት እግዚአብሄርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፡፡
ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ዕብራውያን 11፡6
እግዚአብሄር ከሰው የሚፈልገው የመጀመሪያው እምነት ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሰራውን ስራ ለእኔ ነው ብሎ ማመን እና መቀበል ነው፡፡ ኢየሱስ የእግዚአብሄር ልጅ እንደሆነ ማመን የእምነት የመጀመሪያው ደረጃ ነው፡፡ እምነት መንፈሳዊውን አለም ማየት ነው፡፡ ኢየሱስን ያላመነ ሰው የእግዚአብሄር መንግስት ሊያይ አይችልም፡፡
ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው። ዮሃንስ 3፡3
ኢየሱስን ከማመን ቀጥሎ ለእግዚአብሄር ለመኖርና እግዚአብሄርን ለማገልገል የመጀመሪያውና ወሳኙ እምነት ስለ መሰረታዊ ፍላጎት ጌታን ማመን ነው፡፡ ስለ መሰረታዊ ፍላጎት ጌታን ማመን ቀላል እምነት ይመስላል ፡፡ ነገር ግን ብዙዎችን ከህይወትና ከአገልግሎት ያሰናከለው ስለመሰረታዊ ፍላጎት ጌታን አለማመን ነው፡፡ ለእግዚአብሄር እንድንኖርና እግዚአብሄርን እንድናገለግል የሚያስችለን የእግዚአብሄር ቃል እንዳይሰራብን የሚያገደው ስለመሰረታዊ ፍላጎት ጌታን አለማመን ነው፡፡
የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት ማታለል የሌላውም ነገር ምኞት ገብተው ቃሉን ያንቃሉ፥ የማያፈራም ይሆናል። ማርቆስ 4፡19
ሰው ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ ጌታን ካላመነ ስለሌላ ስለምንም አምናለሁ ቢል ውሸት ነው፡፡ ሰው ስለሌላ ነገር ከማመኑ በፊት የሚቀድመው እርሱ ለእግዚአብሄር ሲኖር እግዚአብሄር መሰረታዊ ፍላጎቱን እንደሚያሟላ ማመን ነው፡፡
እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡31፣33
ስለመሰረታዊ ፍላጎት ጌታን ማመን ከደህንነት ቀጥሎ የእምነት መሰረት ነው፡፡ ሰው ስለ መሰረታዊ ፍላጎቱ ካመነ ስለሌላ ስለምንም ነገር ማመን አይቸግረውም፡፡ ሰው ስለመሰረታዊ ፍሎጎቱ ካላመነ ደግሞ አንደኛ ደረጃን ሳይጨርስ ሁለተኛ ደረጃን ለማለፍ እንደመሞከር ነው፡፡
ስለመሰረታዊ ፍላጎት እምነት ያለው ሰው እግዚአብሄርን በወደደው አቅጣጫ ሊያገለግለው ይችላል፡፡ የመሰረታዊ ፍላጎት ጥያቄ ሙሉ ዜን የሚጠይቅ ስለሆነ ስለመሰረታዊ ፍላጎት የማያምን ሰው ግን እግዚአብሄርን ማገልገል ያቅተዋል፡፡
እግዚአብሄርን ማገልገል የምንችለው ስለመሰረታዊ ፍላጎታችን እግዚአብሄርን በምናምንበት መጠን ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄርን ስለመሰረታዊ ፍላጎታችን በማናምንበት መጠን ህይወታችንን እናባክነዋለን፡፡
አህዛብ መሰረታዊ ፍላጎትን ከማሟላት ያለፈ ስራ የላቸውም፡፡ አህዛብ እግዚአብሄር እንደልጅ እንደሚንከባከባቸው አያምኑም፡፡ አህዛብ አንዱና ብቸኛው የህይወት አላማቸው የሚበላና የሚጠጣ የሚለበስ መፈለግ ነው፡፡ አህዛብ የሚበላ ፣ የሚጠጣና የሚለበስ በመፈለግ ብቻ እግዚአብሄርን የሚያገለግሉበትን ክቡር ህይወት ያባክናሉ፡፡
እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ማቴዎስ 6፡31-32
ስለቤት ኪራይ ፣ ስለልጆች ትምህርት ቤት ፣ ስለመጓጓዣ በአጠቃላይ ስለመሰረታዊ ፍላጎት እግዚአብሄርን ሳያምኑ እግዚአብሄርን እናገለግላለን ማለት ዘበት ነው፡፡
አሁን በክርስትያን ህይወት ውስጥ የሚታዩ ብዙ ችግሮችን ወደኋላ ሄደን ብንፈትሽ እግዚአብሄርን ስለመሰረታዊ ፍላጎት ያለማመን ችግር ውጤት ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች የሚጣሉት ስለመሰረታዊ ፍላት እግዚአብሄርን ካለማመን ነው፡፡ ሰዎች በክርስትና ህይወታቸው ጌታን እንደልባቸው የማገልገል ችግር የመነጨው እግዚአብሄርን ስለመሰረታዊ ፍላጎት ካለማመን ነው፡፡ ሰዎች ለስልጣን የሚዋጉት በተዘዋሪ ስለመሰረታዊ ፍላጎት ካለማመን ነው፡፡ ሰዎች እግዚአብሄርን በማገልገል ላይ ከማተኮር ይልቅ በሌሎች ነገሮች ላይ የሚያተኩሩት ስር መሰረቱ ቢታይ የመሰረታዊ ፍላጎት ጥያቄ ነው፡፡  
ሳይሰስት ተሰጥቶ እግዚአብሄርን የሚያገለግል ሰውን ብናይ ደግሞ እግዚአብሄርን ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ እንዳመነው እርግህጠኛ መሆን እንችላለን፡፡ ስለ ስልጣንና ስለማእረግ ግድ የማይለው አገልጋይ ብናይ ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ በጌታ ላይ የተደገፈ ሰው ስለሆነ ነው፡፡ ስለአገልግሎቱ ስፋትና ስለዝናው ሌት ተቀን የማይጨነቅ ሰው ካየን ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ በእግዚአብሄር ላይ ያረፈ ስለሆነ ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ህዝብ መጥቀም ፣ ማገልገል ፣ ማንሳትና ማሻገር ላይ የሚያተኩር አገልጋይ ካየን እርሱ ለእግዚአብሄር ህዝብ ሲሰራ እግዚአብሄር የእርሱን ቤት እንደሚሰራ ስለተማመነ ነው፡፡   
ሰው እግዚአብሄርን ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ ባመነበት መጠን ብቻ ነው ለእግዚአብሄር ብቻ ለመኖር ነፃ የሚሆነው፡፡ ሰው እግዚአብሄርን ስለሚበላው ፣ ስለሚጠጣውና ስለሚለብሰው በአጠቃላይ ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ ካመነ ሰው ብቻ ነው እግዚአብሄርን ለማገልገል የሚለቀቀው፡፡  
እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡31፣33
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#መሰረታዊፍላጎት #ነፃነት #አትጨነቁ #ቅድሚያ #ምንእንበላለን #ምንእንጠጣለን #ምንእንለብሳለን #አስቀድማችሁ #ፅድቁን #የአለምሃሳብ #የባለጠግነትማታለል #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ምህረት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment