የአዋጅ
ነጋሪ ቃል፦ የእግዚአብሔርን መንገድ በምድረ በዳ ጥረጉ፥ ለአምላካችንም ጐዳና በበረሀ አስተካከሉ። ሸለቆው ሁሉ ከፍ ይላል፥ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይላል፤ ጠማማውም ይቃናል፥ ስርጓጕጡም ሜዳ ይሆናል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ይገለጣል፥ ሥጋ ለባሹም ሁሉ በአንድነት ያየዋል፥ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና። ኢሳይያስ 40፡3-6
እግዚአብሄር በእያንዳንዱ የህይወት አቅጣጫችን
ሁልጊዜ መገለጥ ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር በእኛ ፋንታ ሃይሉን መግለጥ ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር በድካማችን ሊቆም ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር
በህይወታችን ሊታይ ይፈልጋል፡፡ በህይወታችን አስበን የማናውቀውን ድንቅ ነገር ማድረግ ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር በህይወታች ሃይሉን
ሊያሳይ ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር በህይወታችን ክብሩን እንዲገልጥ ልባችን እንዲዘጋጅ ይፈልጋል፡፡
እግዚአብሄር ግን ጨዋ ነው፡፡ እግዚአብሄር እንደ
ልጆች ለእኛ ክብር አለው፡፡ እግዚአብሄር የሰውን ፈቃድ ይጠብቃል፡፡ እግዚአብሄር የሰውን ፈቃደኝነትና መተባበር ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር
ኩሩ ነው፡፡ እግዚአብሄር ክብሩን ማወቃችንን ማየት ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄርን እንድንፈልገው ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር በህይወታችን
ክብሩን እንዲገልጥ ለእግዚአብሄር መምጫ መንገድን ልንጠርግ ያስፈልጋል፡፡
የአንዳንዱ ሰው ህይወት ለእግዚአብሄር ስራ እንደ
አውራ ጎዳና ነው፡፡ የሌላው ደግሞ ህይወት እንደ ተራራና ሸለቆ የማይመችና የማይጋብዝ መንገድ ነው፡፡ እግዚአብሄር በህይወታችን
ክብሩን እንዲገልጥ መንገድን እንድንጠርግለት ይፈልጋል፡፡ እኛ ማድረግ የማንችለው ነገር እርሱ እንዲያደርግ እኛ ማድረግ የምንችለውን
ነገር መጀመሪያ እንድናደርግ እግዚአብሄር ይፈልጋል፡፡ የእግዚአብሄር ክብርና በጎነት እንዲገለጥ የእኛ ትህትናና የዋህነት ይጠይቃል፡፡
እግዚአብሄር በህይወታችን እንዲገለጥ እግዚአብሄር
ከእኛ የሚጠብቃቸው ነገሮች አሉ፡፡
1.
እግዚአብሄር በእኛ ክብሩን
ለመግለጥ በህይወታችን ያለው ሸለቆ እንዲሞላ ይፈልጋል፡፡
አልችልም አልበቃም
አይገባኝም የምንለውና ሃሞት ቢስነታችንን እምነት ማጣታችንን በእምነት መለወጥ አለብን፡፡ በክርስቶስ በመስቀል ላይ በተከፈለልን
የሃጢያት ዋጋ ምክኒያት ማንኛውም የእግዚአብሄር በጎነት ይገባናል፡፡ እግዚአብሄርን ተስፋ ማድረግ አለብን፡፡ እግዚአብሄን መጠበቅ
አለብን፡፡ የማይቻለውን ነገር ይችላል ብለን ማመን አለብን፡፡ እኛ የማንችለውን ነገር ካላደረገ ምኑን አምላካችን ሆነ፡፡ እኛ የማንችለውን
ታእምር ካላደረገ የአምላክ አስፈላጊነቱ ምኑ ላይ ነው፡፡ ከተፈጥሮ በላይ የሆነውን ነገር ካላደረገ እምነት ምንድነው፡፡ የማናየውን
ነገር ካላደረግ እምነታችን የት አለን፡፡
ነገር ግን በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕርን ማዕበል ይመስላልና። ሁለት አሳብ ላለው በመንገዱም ሁሉ ለሚወላውል ለዚያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች እንዲያገኝ አይምሰለው። ያዕቆብ 1፡6-8
ኢየሱስ፦ ብታምኚስ የእግዚአብሔርን ክብር እንድታዪ አልነገርሁሽምን? አላት። ዮሃንስ 11፡40
2.
እግዚአብሄር በድካማችን ሃይሉን
እንዲያሳይ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይበል፡፡
እግዚአብሄር በህይወታችን
በበጎነቱ እንዲገለጥ ከፍ ያለው ነገር የራስ ጉልበትና ችሎታ ትእቢት እና ትምክት እንዲዋረድ ያስፈልጋል፡፡ ትሁት እንድንሆን ራሳችንን
በፊቱ እንድናዋርድ እግዚአብሄር ይፈልጋል፡፡ የማላውቀው ነገር አለ ስለእኔ ከእኔ በላይ እግዚአብሄር ያውቃል ማለት ይኖርብናል፡፡
እንዲሁም፥ ጐበዞች ሆይ፥ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።
እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤ 1ኛ ጴጥሮስ 5፡6
3.
ጠማማውም ይቃናል፥ ስርጓጕጡም
ሜዳ ይሆናል
ጥርጥራችንንና አለማመናችንን
ማስወገድ አለብን፡፡ የዋሆች መሆን ይጠበቅብናል፡፡ እግዚአብሄር እንዲሚክሰን በማመን ለመጎዳት ለመበለጥ መዘጋጀት አለብን፡፡ ክፉን
በክፉ ላለመመለስ ሃይላችን ለክፋት ላለመጠቀም መወሰን ለክፋት ሞኝ መሆን አለብን፡፡ ለእግዚአብሄር ቃል የዋህ መሆን ይጠበቅብናል፡፡
በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል። ዮሃንስ 15፡7
የዋሆች ብፁዓን ናቸው፥ ምድርን ይወርሳሉና። ማቴዎስ 5፡5
እኛ የእግዚአብሄን ክብር ከምንፈልገው ባለይ እግዚአብሄር በህይወታችን ክብሩን ማሳየት ይፈልጋል፡፡ እኛ ከተዘጋጀን እግዚአብሄር
በህይወታችን ይታያል ክብሩንና በጎነቱን በህይወታችን ይገልጻል፡፡
ለተጨማሪ
ፅሁፎች
https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ክብር #ሃይል #ዘላለም #ጥበብ #የእግዚአብሄርመንግስት #ንጉስ #እርሾ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ
No comments:
Post a Comment