Popular Posts

Tuesday, November 14, 2017

የስኬት መለኪያው

በህይወታችን ስኬት በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ህይወታችን በስኬት ካልተለካ ብክነት ነው፡፡ ህይወቴ በስኬት ጎዳና ላይ ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ በትክክል ካልተመለሰ ህይወታችን ካለፍሬና ውጤት አለመቅረቱ ምንም ማረጋገጫ አይኖረውም፡፡ ስኬት ደግሞ በአጋጣሚ የሚመጣ እድል አይደለም፡፡ ስለስኬት በሙሉ ስልጣን የሚነግረን የእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡
ስኬት ደግሞ የሚለካው የተፈጠርንበትን አላማ በመፈፀም ነው፡፡ ስኬት የሚለካው እግዚአብሄር እንደፈጠረን ንድፍ ወይም ዲዛይን መኖራችንን በመለካት ነው፡፡ ግን ጥያቄው ስኬት በምን ይለካል? ነው፡፡
ስኬት የሚለካው የእግዚአብሄርን ፈቃድ በህይወታችን ለመፈፀም የሚያስችለን የክርስቶስ ባህሪ በእኛ ይታያል ወይ? የሚለውን ጥያቄ በታማኝነት በመመለስ ነው፡፡ በክርስትያና ስኬትን እንደኪሎና ርዝመት መለካት ቀላል ባይሆንም ነገር ግን ስኬት የሚለካባቸውን መመዘኛዎች ከእግዚአብሄር ቃል በመመልከት በስኬት ጎዳና ላይ መሆናችንና አለመሆናችንን መመዘን እንችላለን፡፡
እግዚአብሄር በህይወታችን ያስቀመጠውን ጥሪ ለመፈፀም የክርስቶስ ባህሪ ይጠይቃል፡፡ ኢየሱስ በምድር ላይ የነበረውን አላማ ለመፈፀም የጠየቀው ባህሪ ነበር፡፡ አሁንም እኛ የእግዚአብሄር አላማ በህይወታችን ሙሉ ለሙሉ እንዲፈፀም የሚጠይቀን የክርስቶስ ባህሪ በእኛ ላይ መታየቱ ነው፡፡
ሰዎች የሚያከብሩዋቸውና የሚሰግዱላቸው ነውር የሚባሉ ነገሮችን መናቅ የእግዚአብሄርን ፈቃድ በህይወታችን መሉ ለሙሉ እንድንፈፅም ይረዳናል፡፡ የሰው አስተያየት ሳይሆን የእግዚአብሄር ቃል የህይወታችን መመዘኛ ከሆነ በስኬት ጎዳና ላይ ነን፡፡
የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። ዕብራውያን 12፡1-2
ሩጥ ተቀደምክ ታለፍክ የሚለውን የአለም የፉክክር ድምፅ ችላ ብለንና  በፈቃደኝነት ራሳችንን ከፉክክር አግለን የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለመፈፀም በትግስት ከሮጥን የተሳካልን ሰዎች እንደሆንን ሌላ ማርጋገጫ አያስፈልግም፡፡  
ስኬታማ እንዳንሆን የሚያግደን የክርስቶስ ባህሪ በእኛ ውስጥ አለመታየቱ ነው፡፡ የክርስቶስ ባህሪ የማይታይበት ሰው ስኬታማ ነኝ ቢል ከንቱ  ራሱን ያታልላል፡፡ የክርስቶስ ባህሪ የማይታየበት ሰው በሌላ በሁሉም ነገር ስኬታማ እንደሆነ ቢመስለው ስኬታማ አይደለም፡፡ የክርስቶስን ባህሪ በህይወቱ ለመገንባት ቅድሚያ የማይሰጥ ሰው ህይወቱን በከንቱ ያባክናል፡፡   
እውነተኛ የስኬት መመዘኛ የክርስቶስ ባህሪ በእኛ ውስጥ መታየቱ ነው፡፡ የክርስቶስ ባህሪ በህይወቱ የተገነባ ሰው የእግዚአብሄርን ፈቃድ እየፈፀመ ነው፡፡ የክርስቶስን ባህሪ የተላበሰ ሰው የእግዚአብሄርን ፈቃድ ላለመፈፀም የሚያግደው ምንም ሃይል አይኖርም፡፡ የክርስቶስን ባህሪ በሚኖር ሰው ላይ የሚሰራ ህግ የለም፡፡
የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው። እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም። ገላትያ 5፡22-23
የክርስቶስ ባህሪ ያለው ሰው ህጉን ፈፅሞታል፡፡ የክርስቶስ ባህሪ ካለው ሰው ውጭ የእግዚአብሄርን አላማ በህይወቱ ፈፅሞ ለማለፍ ብቃቱ ያለው ሰው የለም፡፡
ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ይፈጸማልና፥ እርሱም፦ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚል ነው። ገላትያ 5፡14
በየደረጃው ላለው ለእግዚአብሄር አሰራር ራሱን ትሁት ከሚያደርግ ሰው በላይ የእግዚአብሄርን ፈቃድ መፈፀም የሚያስችል ስልጣን ያለው ሰው የለም፡፡
በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን። እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ። ፊልጵስዩስ 2፡5-8
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እግዚአብሔር #ጌታ #ባህሪ #ፍቅር #ትህትና #ትእግስት #መከተል #ክርስቶስእስኪሳል #መምሰል #ክርስቶስንመምሰል #ቃል #ተማሪ #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #ደቀመዝሙር #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ነፍስንመካድ #መፅሃፍቅዱስ #ተከታይ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment