Popular Posts

Sunday, November 5, 2017

እነሆ፥ በእረኞች ላይ ነኝ፥ ይላል እግዚአብሔር በጎቼንም ከእጃቸው እፈልጋለሁ፥

የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር፥ በእስራኤል እረኞች ላይ ትንቢት ተናገር፥ እረኞችንም እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ራሳቸውን ለሚያሰማሩ ለእስራኤል እረኞች ወዮላቸው! እረኞች በጎችን ያሰማሩ ዘንድ አይገባቸውምን? ጮማውን ትበላላችሁ ጠጕሩንም ትለብሳላችሁ፥ የወፈሩትን ታርዳላችሁ፤ በጎቹን ግን አታሰማሩም። የደከመውን አላጸናችሁትም የታመመውንም አላከማችሁትም የተሰበረውንም አልጠገናችሁትም የባዘነውንም አልመለሳችሁትም የጠፋውንም አልፈለጋችሁትም በኃይልና በጭቈናም ገዛችኋቸው። እረኛንም በማጣት ተበተኑ፥ ለምድርም አራዊት ሁሉ መብል ሆኑ፥ ተበተኑም። በጎቼ በተራሮች ሁሉና በረዘሙ ኮረብቶች ሁሉ ላይ ተቅበዝብዘዋል፥ በጎቼም በምድር ፊት ሁሉ ላይ ተበትነዋል፤ የሚሻም የሚፈልግም አልነበረም። ስለዚህ፥ እረኞች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ሕያው ነኝና እረኛ ስለሌለ እረኞቼም በጎቼን ስላልፈለጉ እረኞችም ራሳቸውን እንጂ በጎቼን ስላላሰማሩ፥ በጎቼ ንጥቂያ ሆነዋልና፥ በጎቼም ለምድር አራዊት ሁሉ መብል ሆነዋልና ስለዚህ፥ እረኞች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በእረኞች ላይ ነኝ፥ በጎቼንም ከእጃቸው እፈልጋለሁ፥ በጎቼንም ከማሰማራት አስተዋቸዋለሁ። ከዚያም ወዲያ እረኞች ራሳቸውን አያሰማሩም፤ በጎቼንም ከአፋቸው አድናለሁ፥ መብልም አይሆኑላቸውም። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ እነሆ፥ እኔ ራሴ በጎቼን እሻለሁ እፈልግማለሁ። እረኛ በተበተኑት በጎች መካከል ባለ ጊዜ መንጋውን እንደሚፈልግ፥ እንዲሁ በጎቼን እፈልጋለሁ፤ በደመናና በጨለማ ቀን ከተበተኑት ስፍራ ሁሉ አድናቸዋለሁ። ከአሕዛብም ዘንድ አወጣቸዋለሁ ከአገሮችም እሰበስባቸዋለሁ፥ ወደ ገዛ አገራቸውም አመጣቸዋለሁ፤ በእስራኤልም ተራሮች ላይ በፈሳሾችም አጠገብ በምድርም ላይ ሰዎች በሚኖሩበት ስፍራ ሁሉ አሰማራቸዋለሁ።    በመልካም ማሰማርያ አሰማራቸዋለሁ ጕረኖአቸውም በረጅሞቹ በእስራኤል ተራሮች ላይ ይሆናል፤ በዚያ በመልካም ጕረኖ ውስጥ ይመሰጋሉ፥ በእስራኤልም ተራሮች ላይ በለመለመ ማሰማርያ ይሰማራሉ። እኔ ራሴ በጎቼን አሰማራለሁ አስመስጋቸውማለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፡፡ የጠፋውንም እፈልጋለሁ የባዘነውንም እመልሳለሁ የተሰበረውንም እጠግናለሁ የደከመውንም አጸናለሁ፤ የወፈረውንና የበረታውንም አጠፋለሁ በፍርድም እጠብቃቸዋለሁ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እናንተም መንጋዬ ሆይ፥ እነሆ፥ በበግና በበግ መካከል፥ በአውራ በግና በአውራ ፍየልም መካከል፥ እፈርዳለሁ። የቀረውን ማሰማርያችሁን በእግራችሁ የረገጣችሁት፥ በመልካሙ ማሰማርያ መሰማራታችሁ ባይበቃችሁ ነውን? የቀረውንስ ውኃ በእግራችሁ ያደፈረሳችሁት፥ ጥሩውን ውኃ መጠጣታችሁ ባይበቃችሁ ነውን? በጎቼም በእግራችሁ በረገጣችሁት ይሰማራሉ በእግራችሁም ያደፈረሳችሁትን ይጠጣሉ። ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላቸዋል፦ እነሆ፥ እኔ በወፈሩት በጎችና በከሱት በጎች መካከል እፈርዳለሁ። እስክትበትኑአቸው ድረስ በእንቢያና በትከሻ ስለምትገፉአቸው የደከሙትንም ሁሉ በቀንዳችሁ ስለምትወጉአቸው፥ ስለዚህ መንጋዬን አድናለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህም ንጥቂያ አይሆኑም በበግና በበግ መካከልም እፈርዳለሁ። ሕዝቅኤል 34፡1-22
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እረኛ #መጋቢ #ፓስተር #መመገብ #መጠበቅ #ማሰማራት #መንጋ #መፈለግ #መሪ #ቤተመቅደስ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ነቢያት #ነቢይ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment