Popular Posts

Follow by Email

Saturday, November 11, 2017

የመርገም ሀሁ

እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው በመልኩና በአምሳሉ ነው፡፡ ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሄር ክብር ነው፡፡ እግዚአብሄር ሰውን ፈጥሮ ባረከው፡፡ እግዚአብሄር ሰውን በመባረክ ወደ ክንውን ወደ መሳካትና ወደፍሬያማነት ለቀቀው፡፡  ነገሮች ሁሉ ለሰው በጎነትና ክንውን እንዲሰሩ እግዚአብሄር ሰውን ባረከው፡፡
እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው፦ ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው። ዘፍጥረት 1፡27-28
ሰው በበረከት በኖረበት ዘመን ሁሉ የኖረው በሙላት በክንውን በፍሬያማነት ነው ፡፡ በሰው ላይ የሚበረታና የሚያይልበት ምንም ነገር አልነበረም፡፡ ተፈጥሮ ሁሉ ይታዘዝለት ነበር፡፡ ተፈጥሮ ሁሉ አንደሃይሉ መጠን ይሰጠው ነበር፡፡ ሰው እግዚአብሄርን በታዘዘ ጊዜ ሁሉም ነገር ለእርሱ ይታዘዝለት ነበር፡፡ ሰው እግዚአብሄርን ታዝዞ በኖረበት ጊዜ ሁሉ የሚሰራው ሁሉ ይከናወንለት ነበር፡፡ ሰው በመታዘዝ በኖረበት ዘመን ሁሉ በታላቅ ስልጣንና ሃይል ኖረ፡፡ ሰው በእግዚአብሄር ስልጣን ስር እስከነበረ ድረስ ለሰው ስልጣን የማይገዛ የማይሰማውና የማይታዘዘው አንድም ሃይል አልነበረም፡፡ እግዚአበሄርን ታዞ በኖረበት ዘመን ሁሉ ሰው በሙላት ኖረ፡፡ ሰው እግዚአብሄርን ታዞ በኖረበት ጊዜ ሁሉ ድካም ፣ አለመከናወን ፣ በሽታና ማጣት በሰው መዝገበ ቃላት ውስጥ የማይታወቁ ነገሮች ነበሩ፡፡ 
ሰው አታድርግ የተባለው ባደረገ ጊዜ ግን ከእግዚአብሄርን በረከት አጣው፡፡ ሰው እግዚአብሄር ላይ ሲያምፅ ነገሮች ሁሉ አመፁበት፡፡ ሰው እግዚአብሄርን መታዘዝ ሲያቆም ሁሉም ነገር ለሰው መታዘዝ አቆመ፡፡ ሰው እግዚአብሄር ላይ በማመፅ የእግዚአብሄርን በረከት እና ስልጣን አጣው፡፡ ሰው እግዚአብሄር ላይ በማመፁ ሁሉም ነገሮች በእርሱ ላይ አመፁ፡፡
ሰው በሃጢያት ሲወድቅና እግዚአብሄር የፈጠረውን አላማ ሲስት ሁሉም ነገር ተዘበራረቀበት፡፡ ሰው በሃጢያት ሲወድቅ በሽታ ማጣት ሞት የሚባሉ ነገሮች የህይወቱ ክፍል ሆኑ፡፡ 
አሁንም ሰው እግዚአብሄር ያዘጋጀውን የመዳኛ መንገድ ኢየሱስን ሲቀበል እግዚአብሄር ይቀበለዋል፡፡ ኢየሱስን የተቀበለ ሰው ከጨለማ ስልጣን ድኖዋል፡፡ ኢየሱስን የሚከተል ሰው ወደፍቅሩ ልጅ መንግስት ፈልሶዋል፡፡
እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን። ቆላስይስ  1:13-14
ኢየሱስን እንደ አዳኝና ጌታችን የተቀበልን ሁሉ በእግዚአብሄር ምህረት ስር ነን፡፡ ኢየሱስን የምንከተል ሁሉ በሰይጣን ምህረት ስር አንኖረም፡፡ ሰይጣን በእኛ ላይ ስልጣን የለውም፡፡
በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም። ዮሃንስ 3፡36
በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ በእነርሱም፥ በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው። ኤፌሶን 2፡1-2
የኢየሱስን የመስቀል ስራ ለእኔ ነው ብለን የተቀበልን ሁላችን አሁን የቁጣ ልጆች አይደለንም፡፡
በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ፥ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን። ኤፌሶን 2፡3
እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም። ሮሜ 8፡1
በክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። ኤፌሶን 1፡3
የበረከት ልጆች እንጂ የመርገም ልጆች አይደለንም፡፡ የተጠራነው በረከትን ልንወርስ እንጂ የተጠራነው ለመርገም አይደለም፡፡  
ክፉን በክፉ ፈንታ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ በዚህ ፈንታ ባርኩ እንጂ፥ በረከትን ልትወርሱ ለዚህ ተጠርታችኋልና። 1ኛ ጴጥሮስ 3፡9
አምላኬም እንደ ባለ ጠግነቱ መጠን በክብር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ይሞላባችኋል። ፊልጵስዩስ 4፡19
እግዚአብሔር፥ ሁልጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ ትበዙ ዘንድ፥ ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል። 2ኛ ቆሮንቶስ 9፡8-9
ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ ተመልክቶ የሚጸናበት፥ ሥራንም የሚሠራ እንጂ ሰምቶ የሚረሳ ያልሆነው፥ በሥራው የተባረከ ይሆናል። ያዕቆብ፡25
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መርገም #እርግማን #ክርስቶስ #ህይወት #ብልፅግና #የብልፅግናወንጌል #መፀለይ #ሞገስ #በረከት #ስኬት #እረኛእግዚአብሄር #ስምረት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #የተትረፈረፈህይወት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #መርካት #ደስታ #እረፍት

No comments:

Post a Comment