Popular Posts

Saturday, November 25, 2017

የፍላጎትና የቅንጦት መለያ መንገድ

የፍላጎትና የቅንጦት መለያ መንገድ
ሰው የተፈጠረው ለእግዚአብሄር ክብር ነው፡፡ ለእግዚአብሄር ክብር የተፈጠረው ሰው የተፈጠረው ለተወሰነ አላማና ግብ ነው፡፡ ሰው ሁሉንም ነገር ማድረግ አይችልም፡፡ ሰው በምድር ላይ ማድረግ የሚችለው የተወሰነውን የእግዚአብሄርን ልዩ አላማ ብቻ ነው፡፡
እግዚአብሄርን ስንከተል እርሱ የሚያስፈልገንን ሁሉ ያሟላል፡፡ እግዚአብሄር የሚያቀርብልን የሚያስፈልገንን ነገር ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄር የምንፈልገውን ነገር ሁሉ አያቀርብልንም፡፡ ሰውም የሚያገኘው አቅርቦት በተጠራበት በተለየ አላማ ላይ ብቻ የተመሰረተ ነው፡፡ እግዚአብሄር ለሰው የሚያቀርበው ለፈጠረው አላማ ብቻ ነው፡፡  የፈጠረው ሰው የሚያስፈልገው ነገር እንዳይጎድልበት እግዚአብሄር በትጋት ይሰራል፡፡ ለመሰረታዊ ፍላጎታችን ሁሉ እግዚአብሄር ሙሉ ሃላፊነትን ይወስዳል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር ለቅንጦት ፍላጎታችን ሃላፊነት አይወስድም፡፡ 
የሰው ስኬት የሚወሰነው በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነት መረዳት በመቻሉ ላይ ነው፡የሰው ተግባራዊ ጥበብ የሚለካው በመሰረታዊ ፍላጎትና በቅንጦት መካከል ያለውን ልዩነት በመረዳቱ ነው፡፡ በቅንጦትና በመሰረታዊ ፍላጎት መካከል ያለውን ልዩነት ለማወቅ አንዳንዴ ቀላል ባይሆንም ስለሁለቱ ልዩነት ከእግዚአብሄር ቃል መማር እንችላለን፡፡ የእግዚአብሄር ቃልን ከተመለከትንና ከተረዳን ህይወታችንን በመሰረታዊ ፍላጎት ላይ ብቻ በማተኮር እግዚአብሄር የሚሰጠንን አቅርቦት ለታለመለት አላማ በሚገባ መጠቀም እንችላለን፡፡
ሁለት ተመሳሳይ ሰዎችን የሚለየው ይህ መርህ ነው፡፡ አንዱ ያገኘውን ነገር ሁሉ ራሱን በመግዛት በሚያስፈልገው በመሰረታዊ ፍላጎት ላይ ብቻ ያጠፋዋል፡፡ ሌላው ደግሞ በሚፈልገው ነገር ላይ ሁሉ ማጥፋት ሲጀምር የሚያስፈልገው ዋናው ነገር ይጎድለዋል፡፡
ለራሱ ባሪያ ሆኖ የተጠቃ ሰው እንጀራ ጐድሎት ራሱን ካከበረው ሰው ይሻላል። ምሳሌ 12፡9
የሚበላው ሳይኖረው ከሚኵራራ ይልቅ፣ ራሱን ዝቅ አድርጎ ሠራተኛ የሚያሳድር ይሻላል። ምሳሌ 12፡9 (አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
ብዙን ጊዜ ችግራችን የእግዚአብሄር አቅርቦት ማግኘት እጥረት አይደለም፡፡ ብዙ ጊዜ ችግራችን መሰረታዊ ፍላጎትንና ቅንጦትን መለየት  አለመቻላችንና ለመሰረታዊ ፍላጎት የተሰጠንን አቅርቦት በቅንጦት ላይ ስለምናውለው ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ከራሳችንና ከሰዎች ጋር ሰላም የምናጣው ከመሰረታዊ ፍላጎት አልፈን ለቅንጦት ስንሮጥ ነው፡፡
በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን? ትለምናላችሁ፥ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁና አትቀበሉም። ያዕቆብ 4፡1፣3
በክርስትና ስኬታማ ለመሆን የመሰረታዊ ፍላጎት መርህ ሊገባን ይገባል፡፡ በህይወት ለመሳካት መሰረታዊ ፍላጎትን ከቅንጦት መለየት አስፈላጊ ስለሆነ ሁለቱን እንዴት እንደምንለይ ከእግዚአብሄር ቃል እንመልከት፡፡
መሰረታዊ ፍላጎትን መለያው መንገዶች
1.      መሰረታዊ ፍላጎት ግዴታ የሆነ ነገር ነው፡፡
መሰረታዊ ፍላጎት በጣም ግዴታ ከመሆኑ የተነሳ ፍላጎታችን ካልተሟላ የህይወት አላማችንን መፈፀም አንችልም፡፡ መሰረታዊ ፍላጎት እግዚአብሄር በምድር ላይ ያስቀመጠንን ልዩ አላማ ለመፈፀም ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡
አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል። 1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 6፡8
አንዳንዴ ግን አጥተነው እስካላየን ድረስ ብዙ ነገሮች የሚያስፈክልጉን ይመስለናል፡፡ አጥተነው ግን ምንም ሳንሆን በተግባር እስካላየን ድረስ የማንረዳው ብዙ የሚያስፈልጉ የሚመስሉን ነገር ግን የማያስፈልጉ ነገሮች አሉ፡፡
መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። ፊልጵስዩስ ሰዎች 4፡12-13
ለምሳሌ የምግብ አላማ ብርታት መስጠት ፣ ሰውነታችንን መገንባትና ከበሽታ መከላለከል ነው፡፡ ይህን ሁሉ የሚያደርግልን ምግብ መብላት መሰረታዊ ፍላጎት ሲሆን ስለምግቡ ጣእም ፣ ስለምግቡ ትኩስነትና ቅዝቃዜ ከተነጋገርን ግን ስለመሰረታዊ ፍላጎት ሳይሆን ስለምቾት ወይም ቅንጦት እየተነጋገርን ነው፡፡ ቅንጦት ቢገኝ ጥሪ ነው ነገር ግን ግዴታ አይደለም፡፡
ብዙ ዘራችሁ፥ ጥቂትም አገባችሁ፤ በላችሁ፥ ነገር ግን አልጠገባችሁም፤ ጠጣችሁ፥ ነገር ግን አልረካችሁም፤ ለበሳችሁ፥ ነገር ግን አልሞቃችሁም፤ ደመወዙን የተቀበለ ሰው በቀዳዳ ከረጢት ያደርገው ዘንድ ደመወዙን ተቀበለ። ሐጌ 1፡6
2.     መሰረታዊ ፍላጎት ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ነው፡፡
በሁለቱ መካከል መምረጥ ግዴታ ከሆነብን የምንመርጠው ነገር መሰረታዊ ፍላጎት ነው፡፡ መሰረታዊ ፍላጎት የምናስቀድመው ነገር ነው፡፡ ቅንጦት ቢቆይ ችግር የለውም እንዲውም ባይገኝ ያን ያህል አስፈላጊ አይደለም የምንለው ነገር ቅንጦት እንጂ መሰረታዊ ፍላጎት አይደለም፡፡
ለዚህ ምሳሌ የሚሆንን የእስራኤል ህዝብ ነው፡፡ የእስራኤል ህዝብ ከግብፅ ሲወጡ በህይወታቸው ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ነፃነታቸው እንጂ በመንገድ ላይ የሚበሉት የምቾት ወይም የቅንጦት ምግብ አልነበረም፡፡ በምድር በዳ ሲጓዙ እግዚአብሄር ሁሉንም ፍላጎት የሚያሟላ ጉልበት የሚሰጥ ፣ ሰውነትን የሚገነባና ከበሽታ የሚከላከል ንጥረ ነገርን ሁሉ ያካተተመናን መናን ሰጣቸው፡፡ የእስራኤ ህዝብ ግን እንደለመዱት አይነት ሆድን ያዝ የሚያደርግ ከበድ ያለ ምግብ ስላልነበረ ስለመና በእግዚአብሄር ላይ አጉረመረሙ፡፡ የእስራኤል ህዝብ ጥያቁ የመሰረታዊ ፍላጎት ጥያቄ ሳይሆን የምቾትና የቅንጦት ጥያቄ ነበር፡፡
ሕዝቡም በእግዚአብሔርና በሙሴ ላይ፦ በምድረ በዳ እንሞት ዘንድ ከግብፅ ለምን አወጣችሁን? እንጀራ የለም፥ ውኃ የለም፤ ሰውነታችንም ይህን ቀላል እንጀራ ተጸየፈ ብለው ተናገሩ። ዘኍልቍ 21፡5
በሁሉም የህይወታችን አቅጣጫ በመሰረታዊ ፍላጎትና በቅንጦት መካከል ያለውን ልዩነት ተረድረተን ለመሰረታዊ ፍላጎት ቅድሚያ ከሰጠን በህይወታችን ከእኛ አልፈን ብዙዎችን ማገልገል እንችላለን፡፡
ያም ሆነ ይህ የክርስትና የመጨረሻ ደረጃ የመጨረሻው የስኬት ጣራ ስለ መሰረታዊ ፍላጎት ጌታን ታምኖ ጌታን መከተል ነው፡፡
ፀሎት፡ እግዚአብሄር አምላክ ሆይ ይህንን ቃል እንድሰማ ስለረዳኝ አመሰግናለሁ፡፡ እግዚአብሄር ሆይ በተማርኩት መሰረት ለመሰረታዊ ፋልጎት ቅድሚያ መሰጠት እችል ዘንድ ልዩነቱን ስለምታስተምረኝ አመሰግናለሁ፡፡ በእያንዳንዱም የህይወት ክፍሌ በሁለቱ መካከል መለየት አችል ዘንድ ጥበብን ስለምትሰጠኝና ስለምትረዳኝ አከብርሃለሁ፡፡ በጌታ በኢየሱስ ስም አሜን፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#መሰረታዊፍላጎት #ነፃነት #አትጨነቁ #ቅድሚያ #ምንእንበላለን #ምንእንጠጣለን #ምንእንለብሳለን #አስቀድማችሁ #ፅድቁን #የአለምሃሳብ #የባለጠግነትማታለል #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ምህረት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment