ህይወት በልዩ ልዩ አስደናቂ እድሎች እና አጋጣሚዎች የተሞላ ነው፡፡ ህይወት ዝቀን በማንጨርሰው እድልና ጥቅሞች የተሞላ ነው፡፡ ህይወት ለማደግ፣ ለመለወጥ ፣ ለማበብና ለማብራት ምቹ እና ተስማሚ በሆኑ ጊዜያቶች የተሞላ ነው፡፡
ሁላችንም ማደግ መለወጥ መነሳት ማበብ እንችላለን፡፡ ህይወትን በሚገባ ከያዝነውና እንደ ህጉ ከተጫወትን ህይወት ደስ የሚያሰኝና የሚያረካ ጀብድ /adventure/ ነው፡፡
የእግዚአብሄርን ፈቃድ ህይወት እንዲሆንልን ብቻ ሳይሆን እንዲበዛልንም ነው፡፡ ጥቂት ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ሁላችንም በየፊናችን እንድንወጣ ፣ እንድንሰፋ ፣ እንድናብብና እንድናፈራ እግዚአብሄር ይፈልጋል፡፡ ለሁላችንም የሚበቃ አቅርቦትና ጥቅም ተገልጦዋል፡፡
እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ። ዮሃንስ 10፡10
አንዱ ህይወትን በሚገባ አጣጥሞ ሲኖረው ፣ ህይወት ሲበዛለት እና በህይወት ሲያፈራና ሲያበራ እናያለን፡፡ ሌላው ደግሞ ህይወት የማይገፋ ተራራ ሲሆንበት እያንዳንዷ እርምጃ ጭንቅ ስትሆንበት እናያለን፡፡ አንዱ የህይወት ቁልፉን እንዳገኘ ሲከፍት ሲገባና ሲወጣ ስናይ ሌላው ደግሞ የህይወት ቁልፍ ጠፍቶበት ሲፈራ ሲወጣና ሲወርድ ከምኑም ሳይሆን ሲባክን እናያለን፡፡
በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል፥ ይገባልም ይወጣልም መሰማርያም ያገኛል። ዮሃንስ 10፡9
አንዱ ህይወትን አጣጥሞ ሲኖረው ፣ መኖር መኖር ሲለው ፣ እያንዳንዱዋን የህይወቱን አፍታ በእግዚአብሄር መልካምነት ደስ ሲሰኝበት እናያለን፡፡ ሌላው ደግሞ እያንዳንዱ የህይወት ሃላፊነት ሲጨንቀው እንመለከታለን፡፡ አንዱ ትንሽ ጨለማ ውጣ ስታስቀረው ሌላው ግን በብዙ ጨለማ መካከል ደምቆ ያበራል፡፡ ለአንዱ የእንቅፋት ድንጋይ የሆነው ለሌላው መወጣጫ ደረጃ ነው፡፡ ብርሃንሽ መጥቶአልና፥ የእግዚአብሔርም ክብር ወጥቶልሻልና ተነሺ፥ አብሪ። እነሆ፥ ጨለማ ምድርን ድቅድቅ ጨለማም አሕዛብን ይሸፍናል፤ ነገር ግን በአንቺ ላይ እግዚአብሔር ይወጣል ክብሩም በአንቺ ላይ ይታያል፤ ኢሳይያስ 60፡1
አንዳንዱ ህይወት ሲበዛለት ፣ ሲትረፈረፍለት ፣ ሲወጣ ፣ ሲያብብ ፣ ሲያፈራ ስናይ ሌላው ደግሞ አንዱንም ነገር ከውጤት ሳያደርስ ሲዳክር ዘመኑን ይፈጃል፡፡ አንዱ ህይወትን እንደመኪና ተደላድሎ ሲነዳ ሌላው ግን ህይወትን እንደቆመ መኪና ሲገፋ አንዱ የያዘው ሲያንስ ፣ አቅም ሲያንሰው ፣ ህይወትን ሲገፋ ፣ ሲለፋ ሲጥር እንደልፋቱም ሳያገኝ እንደድካሙ ሳያፈራ ይታያል፡፡ አንዱ መንገዱ ሰፍቶለት አማርጦ ሲያደርግ ሌላው ግን ያለውም አንዱ እየጠበበት ሲሄድ ይታያል፡፡ አንዱ ለመኖር ሲፈራ ሌላው ግን በሞት ጥላ መካከል በድፍረት ኖሮ ኖሮ አይጠግብም፡፡
ላለው ይሰጠዋልና ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። ማቴዎስ 13፡12
እግዚአብሄር ሁላችንም እንድናብብ ፣ እንድንሰፋ ፣ እንድንወጣ እየፈለገ ለዚያም በትጋት እየሰራ በሰዎች መካከል ልዩነት ያመጣው ነገር ራእይ ነው፡፡ ራእይ በሁለት ሰዎች መካከል ልዩነትን ያለመጣል፡፡ እግዚአብሄር በህይወታችን ያለውን አላማ መረዳት በሁለት ጓደኛች መካከል ልዩነትን ያመጣል፡፡ የእግዚአብሄርን ለእያንዳንዳችን ያለውን ጥሪና ተልእኮ መረዳት በሁለት አማኞች ህይወት መካከል ልዩነት እንዲታይ ያደርጋል፡፡ የእግዚአብሄርን ራእይ ማግኘት እና አለማግኘት በሁለት አገልጋዮች መካከል ልዩነትን ያመጣል፡፡
የራዕይ እጥረት የህይወት እጥረት ያመጣል ፡፡ የራእይ መብዛት የህይወትን መትረፍረፍን ያመጣል፡፡ የራእይ ጥራት የህይወትን ጥራት ያመጣል፡፡
የሰውነትህ መብራት ዓይንህ ናት። ዓይንህ ጤናማ በሆነች ጊዜ ሰውነትህ ሁሉ ደግሞ ብሩህ ይሆናል። ዓይንህ ታማሚ በሆነች ጊዜ ግን ሰውነትህ ደግሞ የጨለመ ይሆናል። ሉቃስ 11፡34
ህይወት እግዚአብሄር ለህይወታችን ያለውን አላማ ከማወቅ ይጀምራል፡፡ እያንዳንዳችን የተፈጠርንበትን ልዩ አላማ ካወቅን ህይወት በብርሃን ይሞላል፡፡ ከተፈጠርንበትን አላማ ውጭ ከኖርን ህይወታችን አሰቃቂ ይሆናል፡፡
በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም። በእርሱ ሕይወት ነበረች፥ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች። ብርሃንም በጨለማ ይበራል፥ ጨለማም አላሸነፈውም። ዮሐንስ 1፡1-4
በህይወታችን ራእይ በጣም ያስፈልገናል፡፡ የራእይ እጥረት ካለብን የህይወት እጥረት አለብን ማለት ነው፡፡ ኢየሱስ ግን የመጣው ህይወት እንዲሆንልን እንዲበዛልንም ነው፡፡
ህይወት በታላላቅ እድሎች ተግዳሮቶችና ድሎች የተሞላች ነች፡፡ ራእይ ካለንና አጥርተን በህይወታችን የእግዚአብሄርን አላማ ካየን ከህይወት የተሻለውን ነገር ማውጣትና በሚገባ የተኖረ ህይወት ይኖረናል፡፡
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
#ራዕይ #ምሪት #የእግዚአብሄርአጀንዳ #የእግዚአብሄርፈቃድ #የእግዚአብሄርአላማ #የእግዚአብሄርምክር #ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ተግዳሮት #ፍቅር #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አይን #እይታ #አጥርቶ #ራእይ #መሪ
No comments:
Post a Comment