Popular Posts

Follow by Email

Wednesday, November 1, 2017

ከተፃፈው አትለፍ

ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አንዱ በአንዱ ላይ አንዳችሁም እንዳይታበዩ፦ ከተጻፈው አትለፍ የሚለውን በእኛ ትማሩ ዘንድ፥ ይህን በእናንተ ምክንያት ስለ ራሴና ስለ አጵሎስ እንደ ምሳሌ ተናገርሁ። 1ኛ ቆሮንቶስ 4፡6
ለመንፈሳዊ ብርታትና ውጤት መንፈሳዊ ጤንነት ወሳኝ ነው፡፡ ለመንፈሳዊ ጤንነት ደግሞ ጤናማ ምግብ ወሳኝ ነው፡፡
ማንኛውም ትምህርት ጤናማነቱና ጠቃሚነቱ የሚለካው ደግሞ በእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡
ሰው ለእግዚአብሄር ክብር ስለተፈጠረ ለሰው ልጅ ጥያቄ መፍትሄ ያለው የሰው ጥሩ ጥሩ ሃሳብ ሳይሆን የእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡ የማንኛውም ትምህርት ጤንነት የሚለካውም በእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡ እንደ እግዚአብሄር ቃል ያልሆነ ምንም አይነት ትምህርት የተሙዋላ ጤናን የሚሰጥ ምግብ ሊሆን አይችልም፡፡ እንደ እግዚአብሄር ቃል ጤናማነቱ ያልተረጋገጠን ትምህርት ሰዎችን መግበን ጤናቸውን እንጠብቃልን ማለት ዘበት ነው፡፡ እንደ እግዚአብሄር ቃል ጤንነቱ ያልተጠበቀ ምግብን ሰዎችን አብልተን በክርስትና ህይወታቸው እናበረታቸዋለን ማለት አይቻልም፡፡ እንደ እግዚአብሄር ቃል ጤንነቱ ያለተፈሸ ምግብን አብልተን ሰዎች የእግዚአብሄርን ስራ እንዲሰሩ እናበረታታለን ማለት ልፋት ነው፡፡
የቃሉ አስረማሪዎች ምንም ቢፈተኑ ከቃሉ ላለማለፍ ራሳቸውን ትሁት ማድረግ ይገባቸዋል፡፡ ሰዎች ሲሰሙን ሲወዱን ልዩ ትምህርትን ለማምጣት እንፈተናለን፡፡ ነገር ግን ይህን በትምህርታችን ሰውን የማስደነቅን ፈተና ተቋቁመን ከተፃፈው ላለማለፍ መወሰናችን የሚሰሙንን ጤንነት እንድንጠብቅ ያስችለናል፡፡
ለራስህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ፥ በእነዚህም ጽና፤ ይህን ብታደርግ፥ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህና። 1ኛ ጢሞቴዎስ 4፡16
ከተፃፈው አልፈን ትምህርታችን ጤነኛ ይሆናል ማለት በእሳት መጫወት ነው፡፡ ከተፃፈው አልፈን ትምህርታችን ጤነኛ ይሆናል ብሎ መጠበቅ እንክርዳድ ዘርቶ ስንዴ ለማጨድ እንደመጠበቅ ነው፡፡  
ሰውን የሚፈውሰው የተፃፈው ነው፡፡ በተፃፈው ሃይል ተማመን፡፡ የአንተን ምንም ማጋነን ሳይጨምር የተፃፈው ብቻውን ለሰዎች መድሃኒት ይሰጣል፡፡
ከተፃፈው አትለፍ፡፡ ሄዋን እግዚአብሄር አትብሉ አትንኩትም ብሎዋል ብላ ስታጋንነው የቃሉን ሃይሉን አሳጣችው፡፡ ሰይጣንም ከቃሉ ማለፍዋን ለክፋቱ ተጠቀመበት፡፡
ነገር ግን በገነት መካከል ካለው ከዛፉ ፍሬ እግዚአብሔር አለ:- እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ አትንኩትም።
እውነተኛ አስተማሪ በቃሉ ሃይል የሚያምን ነው፡፡ እውነተኛ አስተማሪ ቃሉ ምንም ሳይጨመርበትና ሳይቀነስበት ስራውን ይሰራል ውጤት ያመጣል ቃሉ ብቻውን በቂ ነው ብሎ የሚያመን ነው፡፡
አስተማሪ በእግዚአብሄር ቃል ብቻ ሳይታመን ሲቀርና የእግዚአብሄርን ቃል ለማጠናከርና ሃይል ሊጨምርለት ሲሞክር ሃይሉን ያሳጣዋል፡፡
አባቱን ወይም እናቱን አያከብርም ትላላችሁ፤ ስለ ወጋችሁም የእግዚአብሔርን ቃል ሻራችሁ። ማቴዎስ 15፡6
ሃዋሪያው ጳውሎስ በዚያ ሁሉ አገልግሎቱ በትህትና በመኖርና በማስተማር ከተፃፈው አትለፍ የሚለውን ምሳሌ ትቶልናል፡፡   
ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አንዱ በአንዱ ላይ አንዳችሁም እንዳይታበዩ፦ ከተጻፈው አትለፍ የሚለውን በእኛ ትማሩ ዘንድ፥ ይህን በእናንተ ምክንያት ስለ ራሴና ስለ አጵሎስ እንደ ምሳሌ ተናገርሁ። 1ኛ ቆሮንቶስ 4፡6
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እግዚአብሄር #አትጨነቁ #ቃልኪዳን #ቃሉንያንቃል #ጤንነት #ንፁህ #አትለፍ #ትምህርት # #ፍሬ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #አትጨነቁ  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment