ብዙ ብሄሮች የሚኖሩባት አገር ውስጥ ስለምንኖር ስለብሄር ጥያቄ ማሰባችን አይቀርም፡፡ ሰዎች በማህበራዊ መገናኛ በየእለቱ ስለብሄር ይወያያሉ፡፡ በጣም አከራካሪ ስለሆነ ስለብሄር ጥያቄ ሲነሳ አንዳንዴ ዝም ማለት እንመርጣለን፡፡ የብሄር ብሄረሰቦች አገር ውስጥ ስለምንኖር የብሄርን ጥያቄ መሸሽ አንገትን ብቻ አሸዋ ውስጥ ቀብሮ ተግዳሮትን ለማሳለፍ እንደሞከር ነው፡፡ በህይወታችን የብሄር ጥያቄ ባይኖርና ሌሎች ጥያቄዎችን ብቻ ብንመልስ መልካም በሆነ ነበር፡፡ የብሄር ጥያቄ ግን በየእለቱ አብሮን የሚኖር በሚገባ መመለስ የሚገባው ጥያቄ ነው፡፡ ስለብሄር ጥያቄ ሲነሳ መደንገጥ የለብንም፡፡ የብሄርን ጥያቄ በእግዚአብሄ ቃል መፈተሽ ይኖርብናል፡፡
ስለብሄር ጥያቄ አንስተን ሳንናደድና ሳንበሳጭ ማውራትና መነጋገር ካልቻልን በዚያ ነገር ነፃ አይደለም ማለት ነው፡፡ ስለብሄር ጥያቄ ትክክለኛና ሚዛናዊ መልስ ሊገኝ የሚችለው ከቤተክርስትያን ነው፡፡ ስለብሄር ጥያቄ በቂ መልስ ሊሰጥ የሚችለው የእግዚአብሄ ቃል የሆነው መፅሃፍ ቅዱስ ነው፡፡ ስለብሄር ጥያቄ ሌሎች ሲጠይቁን እንደ እግዚአብሄር ቃል የምናምነውን ልናውቅ ያስፈልጋል፡፡
ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁአችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፥ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን። 1ኛ ጴጥሮስ 3፡15
ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሄር ነው፡፡ ለእግዚአብሄር ክብር የተፈጠረው ሰው እግዚአብሄር አታድርግ ያለውን ካደረገ በኋላ ከእግዚአብሄ ክብር ወደቀ፡፡ በአዳም ሃጢያት ምክኒያት ሰው ሁሉ በሃጢያት እስራት ውስጥ ወደቀ፡፡ ይባስ ብሎም ሰው በትእቢት በምድር ላይ ስሙን ለማስጠራት ባደረገው ሙከራ እግዚአብሄር አንድ ወገን አንድ የነበረውን ሰው ቋንቋውን በመደባለቅ ባለ ብዙ ቋንቋ አደረገው፡፡
እግዚአብሔርም አለ፦ እነሆ፥ እነርሱ አንድ ወገን ናቸው፥ ለሁሉም አንድ ቋንቋ አላቸው፤ ይህንም ለማድረግ ጀመሩ፤ አሁንም ያሰቡትን ሁሉ ለመሥራት አይከለከሉም። ዘፍጥረት 11፡6
እግዚአብሄር ያዘጋጀውን የመዳኛ መንገድ ኢየሱስን የተቀበሉ ሁሉ ከነገድ መካከልና ሁሉና ከቋንቋም ሁሉ መካከል ተዋጅተዋል፡፡
ከሰው ዋና ዋና ዝርያዎች ብንነሳ ብሄርን ወይም ወገንተኝነትን በአህጉር ፣ በአገር ፣ በክልል ፣ በነገድ በቤተሰብ ልንከፋፈለው እንችላን፡፡
ብሄር ማለት ምን ማለት ነው፡፡ ብሄር ማለት አንድ ባህል ፣ ቋንቋ ፣ ክልልና የአንድነት ስነልቦና ያለው ህዝብ ማለት ነው፡፡ ብሄርተኝነት ማለት ደግሞ የአንድን ብሄር አባል መሆን ማክበር መቀበል የአንድነትና የወገናዊነት ስሜት ማለት ነው፡፡
ለምሳሌ አፍሪካዊነት ወይም ጥቁር ዘርነት አለ፡፡ ኢትዮጲያዊነት አለ፡፡ ከዚያም ብሄሮች አሉ፡፡ ነገዶች አሉ የዘር ግንድ አለ ቤተሰብ አለ፡፡
ሳሙኤልም የእስራኤልን ነገዶች ሁሉ አቀረበ፥ ዕጣውም በብንያም ነገድ ላይ ወደቀ። የብንያምንም ነገድ በየወገናቸው አቀረበ፥ ዕጣውም በማጥሪ ወገን ላይ ወደቀ። የማጥሪንም ወገን በየሰዉ አቀረበ፥ ዕጣውም በቂስ ልጅ በሳኦል ላይ ወደቀ፤ ፈለጉትም፥ አላገኙትምም። 1ኛ ሳሙኤል 10፡20-21
እንደጥቁር ጥቁር ካልሆነ ወገን ጥቁር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ሲደርስብን እንተባበራለን፡፡ እንደጥቁር በተለይ ጥቁር ላይ ያነጣጠር በደል ሲደረስብን እንደ ጥቁር እንተባበራለን፡፡ አፍሪካን ወክሎ የአለም ዋንጫን የተጫወተን የአፍሪካ ቡድን ስለአፍሪካዊነት ወገንተኝነት ብቻ እንዴት እንደምንደግፍ ልባችን ያውቀዋል፡፡
ከዚያም ቀጥሎ ደግሞ በኢትዮጲያዊነትር ስንበደል ጥቃት ሲደርስብን እናብራለን እንከላከላለን፡፡ በኢትዮጲያ ሶማሊያ ጦርነት እንደ ኢትዮጲያዊነት ተንቀሳቀስን እንጂ ይህ አፍሪካ ነው ይሁን ያጥቃን አላልንም፡፡
የመጣበት ብሄር ሲናቅ ሲጠላ ሲጨቆን ደስ የሚለው ሰው የለም፡፡ በአፍሪካዊነት ወገንተኝነት እንዳለን ሁሉ ፣ በኢትዮጲያዊነት ወገንተኝነት እናዳለ ሁሉ ፣ የብሄር የአንድነት ስሜትና ወገንተኝነትን ስህተት የሚያደረገው ነገር የለም፡፡ ሰዎች በአፍሪካዊነት ሲሰባሰቡ ደስ እንምደሚለን ሁሉ ፣ በኢትዮጲያዊነት ወገንተኝነት ሲሰባሰቡ እና ሲያብሩ ደስ እንደሚለን ሁሉና በቤተሰብ ወገንተኝነት ላይ ጥያቄ እንደሌለን ሁሉ ሰዎች በብሄር ሲሰባሰቡ ሊያስደነግጠን አይገባም፡፡ ለቤተሰቤ ያለኝ የወገናዊነት ስሜት ለነገድ ያለኝን የወገናዊነት ስሜት አይሽረውም ለነገድ ያለኝ የወገናዊነት ስሜት ለብሄር ካለኝ የወገናዊነት ስሜት ጋር አይጋጭም፡፡ ለብሄር ያለን የወገናዊነት ስሜት ለአገር ላለን የወገናዊነት ስሜት መሰረት እንጂ እንቅፋት ሊሆን አይገባም፡፡ ለአገር ያለኝ ወገናዊነት ስሜት ለአህጉር ላለኝ ወገንተኝነት ስሜት ጉልበት እንጂ እንቅፋት አይደለም፡፡
በሚገባ ከተያዘ ከሰፊው የወገናዊነት ስሜት ጀምሮ እስከ ትንሹ የቤተሰብ ወገናዊነትና የአንድነት ስሜት ጠቃሚና አስፈላጊ ናቸው፡፡
ሰው ስለ አፍረካዊነቱና እና ስለ አፍሪካዊነት ወገንተኝነት ስሜቱ ንስሃ መግባት የለበትም፡፡ ሰው ስለ አፍሪካዊነቱ ወገንኝነትና የአንድነት ስሜቱ ሊሸማቀቅ አያስፈልገውም፡፡ እግዚአብሄር ጥቁር አድርጎ ስለፈጠረኝ አይፀፀትም ማንንም ይቅርታ አይጠይቅም፡፡ እግዚአብሄር በብሄር ውስጥ እንድወለድ ስላደረገኝና ከአንድ ብሄር ስለፈጠርኩኝ ማንንም ይቅርታ አልጠይቅም፡፡ እግዚአብሄር በአላማው ስለወሰነው የምኖርበት ስፍራና ዳርቻ ማንንም ይቅርታ አልጠይቅም፡፡
ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደ ሆነ፥ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ፥ የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ዳርቻ መደበላቸው። ቢሆንም ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም። ሐዋርያት 17፡26-27
ማንኛውም መልካም ነገር መስመር ሲለቅ ጎጂ እንደሚሆን ሁሉ ወገናዊነት ስሜት መስመር ሲለቅ ጉዳት አለው፡፡ መልካም ነገር የሚገባው የእኔ ቤተሰብ ፣ የእኔ ነገድ ፣ የእኔ ብሄር ፣ የእኔ አገር ፣ የእኔ አህጉር ብቻ ነው ማለት ክፋትና እግዚአብሄር የፈጠረውን ወገንተኝነት ስሜት እግዚአብሄ ላላቀደው ነገር አላግባብ መጠቀም ነው፡፡
ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤ ፊልጵስዩስ 2፡3
በየደረጃው ያሉትን ወገንተኝነት ስሜቶችን በሚዛናዊነት መያዛችን እግዚአብሄር በወገንተኝነትና በአንድነት ውስጥ ያስቀመጠውን በረከት ተጠቃሚ እንድንሆን ያደርጋል፡፡
የእኔ የወገንተኝነት ስሜት ትክክልና የሌላው የወገንተኝነት ስሜት ስህተት የሚሆን ከመሰለን ስለወገንተኝነት ትክክለኛ መረዳት እንደሌለን ያሳያል፡፡ የወገንተኝነትን አስፈላጊነት በቤተሰብ ተቀብለን በአገር ካልተቀበልን አሁንም የወገንተኝነት መረዳት እንደጎደለን ያሳያል፡፡
ነገር ግን ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፥ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው። 1ኛ ጢሞቴዎስ 5፡8
በየደረጃው ያለንን የወገንተኝነት ስሜት ሌላው ላይ ስናየው የሚያስደነግጠን ከሆነ ነፃ አይደለንም የተሳሳተው መረዳት እስረኞች ነን ማለት ነው፡፡
ሌላው ወገን ከእኛ የሚለይበት ነገር ቢኖርም ለአንድ አላማ አብረን መስራት እንደምንችል ማወቅ ማስተዋል ነው፡፡ ከሌላው ወገን ጋር ለአንድ አላማ ለመስራት የራሱን ወገን ትቶ እኔን መሆን አለበት ማለት አንድነትን አለመረዳት ነው፡፡ ራሱን መሆን ትቶ እኔን ካልመሰለ ለአንድ አላማ መስራት አንችልም ማለት ሊተገበር የማይችል አግባብነት የሌለው ጥያቄ ነው፡፡ እኔን ለመምሰል ራሱን ይተው ማለት ለራስ ወዳደነት የሌላን ራስን የመሆን ነፃነት መንፈግ ነው፡፡ ልዩነት ውበት እንጂ ጥፋት አይደለም፡፡ ወገንተኝነት በአግባቡ ከተያዘ እምቅ ጉልበት ያለው በረከት እንጂ መርገም አይደለም፡፡ ለአንድ አላማ ለመስራት ተመሳሳይ /uniform/ ሰዎች መሆን የለብን፡፡ በወገን የተለያየን ሰዎች ለአንድ ግብ ለአንድ አገር መስራታችን ውበት ነው፡፡ የተለያየን ሰዎች አንዳችን ለአንዳችን እንደምናስፈልግ ማመን ታላቅነት ነው፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #በክርስቶስ #መንፈስ #ማንነት #መልክ #አምሳል #የእግዚአብሄርልጅ #ክብር #ብሔር #ቋንቋ #ወገን #ነገድ #አፍሪካ #ኢትዮጲያ #ነገድ #ቤተሰብ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ማየት #የእግዚአብሄርመንግስት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አዲስፍጥረት #ክርስቶስ #የእግዚአብሄርቤተሰብ #ማእረግ #ስልጣን #ከፍታ
No comments:
Post a Comment