Popular Posts

Thursday, November 9, 2017

እግዚአብሔር የሚያደርግልኝ አያሳስበኝም

ክርስትና የእግዚአብሔርና የህዝቡ የቃል ኪዳን ግንኙነት ነው፡፡ በማንኛውም ቃል ኪዳን እያንዳንዱ ወገን የሚወጣው ድርሻ እንዳለ ሁሉ በክርስትናም እኛ እንደ ህዝብ የምንወጣው ድርሻ አለ እግዚአብሔር ደግሞ እንደ አምላክ የሚወጣው የራሱ ድርሻ አለው፡፡ እኛ እንደ አባት የማናደርገው የእግዚአብሔር ብቻ የሆነ ደርሻ አለ፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ እንደ ልጅ የማያደርገው እኛ ብቻ የምናደርገው ድርሻ ደግሞ አለ፡፡
ለምሳሌ ወታደርና ገበሬ ቃልኪዳን ቢገቡ ወታደር የገበሬውን ደህንነት የመጠበቅ ሙሉ ሃላፊነት ይወስዳል ገበሬው ደግሞ ወታደሩን የመመገብ ሙሉ ሃላፊነትን ይወስዳል፡፡ ቃልኪዳኑ እንዲሰራና ሁለቱም የቃልኪዳኑ ሙሉ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ ገበሬው በእርሻው ላይ ወታደሩ ደግሞ በጥበቃው ላይ ብቻ ማተኮር አለባቸው፡፡
ነገር ግን ወታደሩ የጥበቃ ስራውን ትቶ በየጊዜው እየመጣ ገበሬው በትክክል ያርስ ይሆን? ብሎ ቢጨነቅና ስለሌላው ወገን ድርሻ በመጨነቅ የራሱን ድርሻ የጥበቃውን ስራ ቢያጎድል ሃላፊነቱን አይወጣም፡፡ ገበሬውም ይህ ወታደር በትክክል ይጠብቀኝ ይሆን ብሎ በማይመለከተው በጥበቃ ስራ ላይ ቢጨነቅና ጊዜውን በጭንቀት ቢያጠፋ የቃልኪዳን ሃላፊነቱን መወጣት አይችልም፡፡
በተመሳሳይ መልኩ ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ቃልኪዳን የእኛ ድርሻ አለ የእግዚአብሔር ደግሞ ድርሻ አለ፡፡ እኛ ማተኮር ያለብን በእኛና በእኛ ድርሻ ላይ ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ ስለምንበላው ስለምንጠጣው ስለምንለብሰው መጨነቅ በፍፁም የእኛ ስራ አይደለም፡፡
እግዚአብሔር አቢይን በትክክል ይይዘው ይሆን? የሚያስፈልገውን ያሟላለት ይሆን? እግዚአብሔር አቢይን መንከባከቡን ያውቅበት ይሆን? እግዚአብሔር ድርሻውን በትክክል ይወጣ ይሆን? እያልኩ ብንጨነቅ ህይወቴን አባክነዋለሁ፡፡
እግዚአብሔር በቃል ኪዳኑ ቃል በመፅሃፍ ቅዱስ ላይ የእኛን እና የራሱን ድርሻ በሚገባ ለያይቶ አስቀምጦታል፡፡ እንዲያውም የእርሱን ድርሻ ለመስራት እንዳንሞክር ከሞከርን እንዳማይሳካልን በከንቱም እንደምንደክም አስረድቶናል፡፡ እኛ ግን በራሳችን ድርሻ ላይ ካተኮርን የቃልኪዳን አጋራችን እግዚአብሔር የራሱን ድርሻ በሚገባ እንደሚወጣ አስረድቶናል፡፡
እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡31-33
የቃልኪዳን ድርሻዬን ስላወቅኩ ፣ የምችለውንና የማልችለውን ስለተረዳሁ ፣ ድንበሬምን ስላወቅኩ በህይወቴ የሚያሳስበኝ እኔ ለእግዚአብሔር የማደርግለት ነገር ብቻ ነው፡፡
ለእግዚአብሔር መንግስት የማደርገው ነገር ያሳስበኛል፡፡ የእግዚአብሔርን ፅድቁንና መንግስቱን እንዴት እንደምፈልግ አስባለሁ፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ትክክል ሆኜ የመገኘትን ሃላፊነቴን ለመወጣት ቃሉን አሰላስላለሁ፡፡ ለመንግስቱ በጎነት እንዴት እንደምሰራ አወጣለሁ አወርዳለሁ፡፡ በእግዚአብሔር መንግስት የማደርገው አስተዋፅኦ ያሳስበኛል፡፡
የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር፥ ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው። 2ኛ ቆሮንቶስ 11፡28
ምኔን ልስጠው ? እንዴት ልኑርለት? እንዴት ላስብ ? እንዴት ልናገር? እንዴት ልኑርለት የሚለው ያሳስበኛል፡፡
ከራሴ ድርሻ አልፌ እግዚአብሔር ለእኔ ስለሚያደርግልኝ ነገር ለማሰብ የሚተርፍ አቅምም ጉልበትም የለኝም፡፡ እግዚአብሔር ለእኔ የሚያደርግለኝ ነገር አያሳስበኝም፡፡ እግዚአብሔር ድርሻውን ይወጣል፡፡ እግዚአብሔር ልጁን እንዴት እንዲይዘው ያውቅበታል፡፡ እግዚአብሔርን ማንንም አያማክረውም፡፡ እግዚአብሔ ልጁንም እንዴት እንዲመራው ያውቃል፡፡
ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። ኤርምያስ 29፡11
እኔ ደርሼ ለእግዚአብሔር ልጨነቅለት አይገባም፡፡ እግዚአብሔር እኔን የመንከባከብ ሃላፊነቱን ተወጥቶ ይሆን ብዬ ልስጋ አይገባም፡፡ እግዚአብሔር አያያዙን አውቆበት ይሆን ብዬ ልሰልልው አልሞክርም፡፡ እግዚአብሔርን አያያዙን እንዲረዳ ላግዘው አልሞክርም፡፡
ሃላፊነቴን ለመወጣት እተጋለሁ እርሱ ስለእናንተ ያስባልበና የሚለውን ቃል አምኜ እርፍ እላለሁ፡፡ የእኔ ድርሻ የሚያስጨንቀኝን በእርሱ ላይ መጣል ነው፡፡ የእርሱ ድርሻ ስለእኔ ማሰብ ማቀድና መፈፀም ነው፡፡
እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። 1ኛ ጴጥሮስ 5፡7
የእኔ ድርሻ መፀለይ እና ማስታወቅ ነው፡፡ የእርሱ ድርሻ ለህይወቴ ማቀድ የፈጠረኝን አላማ በህይወቴ ማከናወን ነው፡፡
ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። ፊልጵስዩስ 4፡6
የእኔ ድርሻ የእርሱ አላማ በህይወቴ ላይ ማድረግ ነው፡፡ የእርሱ ድርሻ የሰራሁትን ነገር ወደፍፃሜ ማምጣትና ፍሬያማ ማድረግ ነው፡
እኔም መልሼ፦። የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል፥ እኛም ባሪያዎቹ ተነሥተን እንሠራለን፤ እናንተ ግን በኢየሩሳሌም እድል ፈንታና መብት መታሰቢያም የላችሁም አልኋቸው። ነህምያ 2፡20
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ጭንቀት #ማረፍ #ፀጋ #መንግስት #ቃልኪዳን #ድርሻ #ሃላፊነት #ፅድቅ #ፀሎት #ምልጃ #ምስጋና #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment