ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል። 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡11
የነቢይነት አገልግሎት የእግዚአብሄርን ድምፅ ለህዝቡ ማምጣት ነው፡፡ ነቢያት እግዚአብሄር ሲናገር ይናገራሉ እግዚአብሄር ዝም ሲል ዝም ይላሉ፡፡ ነቢያት እግዚአብሄርን ይከተላሉ እንጂ እግዚአብሄርን አይመሩም፡፡ ነቢያት የእግዚአብሄርን ድምፅ ከማስተላለፍ ውጭ የራሳቸው ድምፅ የላቸውም፡፡
መቼና ምን እንደሚያደርግ የሚወስነው እግዚአብሄር ራሱ ነው እንጂ ነቢዩ አይደለም፡፡
ነቢይ የእግዚአብሄርን ድምፅ ከራሱ አያመጣውም፡፡ ነቢይ በራሱ የሚያመጣው ድምፅ የራሱ እንጂ የእግዚአብሄር ሊሆን አይችልም፡፡
እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ ነቢያቱ ውሸት በስሜ ትንቢት ይናገራሉ፤ አላክኋቸውም፥ አላዘዝኋቸውም፥ አልተናገርኋቸውም፤ የውሸቱን ራእይ ምዋርትንም ከንቱንም ነገር የልባቸውንም ሽንገላ ይሰብኩላችኋል። ኤርምያስ 14፡14
ከእግዚአብሔር አፍ ሳይሆን ከገዛ ልባቸው የወጣውን ቃል የሚናገረቱትን ነቢያት እንዳንሰማቸው የእግዚአብሄር ቃል ያስተምረናል፡፡
የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ትንቢት የሚናገሩላችሁን የነቢያትን ቃል አትሰሙ፤ ከንቱነትን ያስተምሩአችኋል፤ ከእግዚአብሔር አፍ ሳይሆን ከገዛ ልባቸው የወጣውን ራእይ ይናገራሉ። ኤርምያስ 23፡16
እኔ ሳልልካቸው እነዚህ ነቢያት ሮጡ፤ እኔም ሳልነግራቸው ትንቢትን ተናገሩ። ኤርምያስ 23፡21
እውነተኛ ነቢያት እግዚአብሄር ሲናገር የሚናገሩ ዝም ሲል ደግሞ ዝም የሚሉ ናቸው፡፡ ላገኙት ሁሉ ሰው ትንቢትን የሚናገሩ ሰዎች ከእግዚአብሄር የሰሙ ነቢያት አይደሉም፡፡ እግዚአብሄር ዝም ሲል ዝም የማይለዩ አገልጋዮች ከእግዚአብሄር አይደሉም፡፡ ጌታ ዝም ሲል ዝም ለማለት ራሳቸውን ትሁት የማያደርጉ አገልጋዮች የእግዚአብሄር አገልጋዮች አይደሉም፡፡ ስለ እግዚአብሄር ድምፅ ደስ ባላቸው ቁጥር የሚሉት ነገር ያላቸው እውነተኛ ነቢያት አይደሉም፡፡ በትህትና እግዚአብሔር ስለዚህ ምንም አልተናገረኝም የማይል ነቢይ እውነተኛ ነቢይ አይደለም፡፡
ወደ ተራራው ወደ እግዚአብሔር ሰው በመጣች ጊዜ እግሮቹን ጨበጠች፤ ግያዝም ሊያርቃት ቀረበ፤ የእግዚአብሔርም ሰው፦ ነፍስዋ አዝናለችና ተዋት፤ እግዚአብሔርም ያንን ከእኔ ሰውሮታል አልነገረኝምም አለ። 2ኛ ነገሥት 4፡27
አንዴ እግዚአብሄር ለመናገር ተጠቅሞብኛል ብሎ በዚያው የሚቀጥል አገልጋይ የእግዚአብሔር አገልጋይ አይደለም፡፡ አንዴ በእኔ ትንቢት ተናግሮዋል ብሎ ሁሌ ትንቢት ሊያመጣ የሚሞክር አገልጋይ ይሳሳታል፡፡
ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ። 2ኛ ጴጥሮስ 1፡21 ነቢይ ሁሉን አያውቅም፡፡ ነቢይ የፈለገውን ነገር ማወቅ አይችልም፡፡ ነቢይ እግዚአብሄር በጊዜው ከተጠቀመበት ብቻ ከእግዚአብሄር ይናገራል፡፡ ነቢይ እግዚአብሄር በጊዜው የገለፀለትን ብቻ ለእግዚአብሄር ህዝብ ጥቅም ያስተላልፋል፡፡
ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል። 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡11
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #የመንፈስፍሬ #ቅባት #መንፈስቅዱስ #የእግዚአብሔርመንፈስ #መሪ #ቤተመቅደስ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ነቢያት #ነቢይ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ
No comments:
Post a Comment