Popular Posts

Follow by Email

Tuesday, August 1, 2017

የፍቅር ስርና መሰረት

የእናንተ ሥርና መሠረት በፍቅር ይጸና ዘንድ፥ ኤፌሶን 3፡17
የማንኛውም ሃሳብ ፣ ንግግርና ድርጊት መሰረቱ ፍቅር መሆን አለበት፡፡ ምንም ነገር ለማድረግ ከፈለግን መጀመሪያ በፍቅር ልናደርገው እንዳለን ማረጋገጥ አለብን፡፡ ህይወታችን ከንቱ እንዳይሆን የምንሰራው ነገር ሁሉ መነሻ ሃሳቡ ፍቅር እንደሆነ ማረጋገጥ ከእግዚአብሄር ጋር እንዳንተላለፍ ይጠብቀናል፡፡
ከፍቅር ውጭ ያደረገንውን ነገር ለእግዚአብሄር አደረኩት ማለት አንችልም፡፡ ከፍቅር መነሻ ሃሳብ ውጭ ያሰብነውን ሃሳብ እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ አሰብኩኝ ማለት አንችልም፡፡ ምክኒያቱም በፍቅር ያልተደረገ ማንኛውም መልካም ነገር እንኳን በእግዚአብሄር ፊት ከንቱ ነው፡፡
የፍቅር አምላክ እግዚአብሄር በእኛ ውስጥ ያለውን መልካም ነገር ሁሉ በፍቅር ሃሳብ እንድናስተዳድረው ብቻ ነው የሰጠን፡፡ እግዚአብሄር የሰጠንን ስጦታ ለሌሎች ስንሰጥ እንኳን ቢሆን ካለፍቅር ከተደረገ ከንቱ ነው፡፡
ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። 1ኛ ቆሮንቶስ 13፡2
በክርስትና ህይወት የተሰጡት ማንኛውም ትእዛዞች ግባቸው በፍቅር እንድንኖር መርዳት ነው፡፡ በፍቅር ካልኖርን የእግዚአብሄርን አላማ ስተናል፡፡ በፍቅር ካልኖርን የእግዚአብሄርን ትእዛዝ ተላልፈናል፡፡ ከእግዚአብሄር ሃሳብ ጋር መተላለፋችን ምልክቱ የምናደርገውን ማንኛውም ነገር ከፍቅር ውጭ ማድረጋችን ነው፡፡
የትእዛዝ ፍጻሜ ግን ከንጹሕ ልብና ከበጎ ሕሊና ግብዝነትም ከሌለበት እምነት የሚወጣ ፍቅር ነው፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 1፡5
ነገሮችን ይበልጥ በፍቅር ባደረግናቸው መጠን የእግዚአብሄርን ፈቃድ ይበልጥ በሙላት መፈፀም እንችላለን፡፡ ነገሮችን ከፍቅር ውጭ ባደረግናቸው መጠን ደግሞ ጠቃሚነታችን እየቀነሰ ይሄዳል፡፡
ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም። 1ኛ ቆሮንቶስ 13፡3
በየጊዜው በፍቅር እየኖርኩ ነው ወይ? የማደርገውን ነገር የማደርገው ከፍቅር ነው ወይ? ለማደርገው ነገር ከፍቅር ውጭ ሌላ መነሻ ሃሳብ አለኝ ወይ? ብለን ልባችንን መመርመር ህይወታቸን ከማባከን ይጠብቀናል፡፡ የምናደርጋቸውን ነገሮች በፍቅር እንደምናደርግ እርግጠኛ በሆንን መጠን የእግዚአብሄር አብሮነት ከእኛ ጋር በሃይል ይሆናል፡፡
ስርና መሰረት አይታይም፡፡ ስለመሰረቱ የሚያውቀው ባለቤቱ ብቻ ነው፡፡ መሰረት ከተበላሸ ቤት ይበላሻል፡፡ ስር ከተበከለ ተክል ይበከላል፡፡ ቤትን ማስተካከል የሚቻለው ከመሰረት ነው፡፡ ተክልን ማስተካከል የሚቻለው ከስሩ ነው፡፡
ሌላው ሰው በፍቅር ማድረጋችንና አለማድረጋችንን ላያውቅ ይችላል፡፡ ራሳችንን መፈተሽ ያለብን ራሳችን ነን፡፡ ሰው በፍቅር አድርጋችሁታል ብሎ ሊሳሳት ይችላል፡፡ እግዚአብሄር ግን የፍቅር ልባችንን አይቶ እንደሚጠቅመንና እንደማይጠቅመን ያውቃል፡፡ ስለዚህ ነው አጥብቀን ልባችንን መጠበቅ ያለብን፡፡  
አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፥ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና። ምሳሌ 4፡23
የእናንተ ሥርና መሠረት በፍቅር ይጸና ዘንድ፥ ኤፌሶን 3፡17
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ፍቅር #ስጦታ #ስር #መሰረት #ትእዛዝ #መስጠት #ሃሳብ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #ቸርነት #ትግስት #ፍርሃት #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #መውደድ #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment