Popular Posts

Thursday, August 3, 2017

ከሁሉ የሚበልጥ ፍቅር

ፍቅርን የሚተካከለው ነገር የለም፡፡ ፍቅር ከፍ ያለ ነው የህይወት ደረጃ ነው፡፡
ደግሞም ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ አሳያችኋለሁ። ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው። 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡31፣ 13፡13
ፍቅር የሚበልጥ የጥበብ ደረጃ ነው፡፡
ፍቅር ከፍተኛው የጥበብ ደረጃ ነው፡፡ ህይወቱን በከንቱ ላለማባከን ጥበብን የሚፈልግና የሚከተል ሰው ፍቅርን መከተል አለበት፡፡ በብልሃት መኖር የሚፈልግ ሰው በፍቅር ነው መኖር ያለበት፡፡ ህይወቱን በማይሆን ነገር ላይ ማባከን የማይፈልግ ሰው በፍቅር መኖር ነው ያለበት፡፡ አዋቂ ሰው በፍቅር ነው የሚኖረው፡፡ የገባው ሰው በፍቅር ለመኖር የወሰነ ሰው ነው፡፡
ከእናንተ ጥበበኛና አስተዋይ ማን ነው? በመልካም አንዋዋሩ ስራውን በጥበብ የዋህነት ያሳይ። ነገር ግን መራራ ቅንዓትና አድመኛነት በልባችሁ ቢኖርባችሁ፥ አትመኩ በእውነትም ላይ አትዋሹ። ይህ ጥበብ ከላይ የሚወርድ አይደለም፤ ነገር ግን የምድር ነው፥ የሥጋም ነው፥ የአጋንንትም ነው፤ ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ስራ ሁሉ አሉና። ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፥ በኋላም ታራቂ፥ ገር፥ እሺ ባይ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት፥ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት። ያዕቆብ 3፡13-17
ፍቅር የሚበልጥ የቅድስና ደረጃ ነው
ፍቅር ትእዛዞች ሁሉ በአንድ ላይ የሚፈፀሙበት የቅድስና መንገድ ነው፡፡ ሰው በፍቅር ኖሮ አይስትም፡፡ ሰው በፍቅር ኖሮ አይሳሳትም፡፡ ሰው በፍቅር አይቆሽሽም፡፡ ሰው በፍቅር አይበላሽም፡፡ እንደ ፍቅር አስተማማኝ ጥላ የለም፡፡ እንደ ፍቅር አስተማማኝ ቅድስና የለም፡፡ በፍቅር እንደ መኖር የእግዚአብሄርን ህግ የምንፈፅምበት የተሻለ መንገድ የለም፡፡  
ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ይፈጸማልና፥ እርሱም፦ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚል ነው። ገላትያ 5፡14
ከእናንተ እያንዳንዱ የአንዱን ሸክም ይሸከም እንዲሁም የክርስቶስን ሕግ ፈጽሙ። ገላትያ 6፡2
ፍቅር የሚበልጥ ያለ የስልጣን ደረጃ ነው፡፡
ፍቅር ታላቅ ስልጣን አለው፡፡ ፍቅር አሸናፊ ነው፡፡ ፍቅር ሃያል ነው፡፡ ፍቅር ባለስልጣን ነው፡፡ ፍቅር የማይረታው ነገር የለም፡፡ በምንም የማይሸነፉ ብዙ ሃያላን ነገሮች አሉ፡፡ ለፍቅር ግን የማይሸነፍ ምንም የለም፡፡  
ጠላትህ ግን ቢራብ አብላው፤ ቢጠማ አጠጣው፤ ይህን በማድረግህ በራሱ ላይ የእሳት ፍም ትከምራለህና። ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ። ሮሜ 12፡20-21
ፍቅር የሚበልጥ የምስክርነት ደረጃ ነው፡፡
ብዙ ነገሮች ማስመሰያ አላቸው ብዙ ሰዎችን ያሳስታሉ፡፡ ፍቅርን አይቶ የማይለይ ሰው የለም፡፡ ከተማረው እስካልተማረው ፍቅርን ይለያል፡፡ ምንም አያቅውቅም የምንለውን ሰው ፍቅርን ሲያይ ግን ያውቀዋል፡፡ ምንም መለየት አይችልም የምንለው ሰው ፍቅርን ግን ይለያል፡፡ ፍቅር የማይማርከው ሰው የለም፡፡ ሰው ፍቅራችንን ካላየ ጌታችንን መከተል አይችልም፡፡ ፍቅራችንን አይቶ ጌታችንን አለመከተል አይችልም፡፡
እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፥ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ። እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ። ዮሃንስ 13፡34-35
ፍቅር የሚበልጥ የህይወት ዘይቤ ነው፡፡
ፍቅርን የሚበልጠው ምንም ነገር የለም፡፡ ፍቅርን የሚከተል በእግዚአብሄር ይኖራል፡፡ ፍቅር የሚበልጥ የህይወት ዘይቤ ነው፡፡ በፍቅር የሚኖር በእግዚአብሄር እንደሚኖር ማረጋገጫው ነው፡፡ በፍቅር የሚኖር ሰው እግዚአብሄር በእርሱ ይኖራል፡፡
እኛም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር አውቀናል አምነንማል። እግዚአብሔር ፍቅር ነው፥ በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል። 1ኛ ዮሐንስ 4፡16
ደግሞም ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ አሳያችኋለሁ። 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡31
ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው። 1ኛ ቆሮንቶስ 13፡13

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ፍቅር #መውደድ #ቃል #መሰረት #ትእዛዝ #መስጠት #ሃሳብ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #ቸርነት #ትግስት #ፍርሃት #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #መውደድ #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment