Popular Posts

Wednesday, August 30, 2017

የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል

እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አለ፦ ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አደረጋቸው፥ አለም፦ ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፥ ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፥ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ የሚለውን ቃል አላነበባችሁምን? ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም። እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው። ማቴዎስ 19:4-6
ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል
ሰው ሁሉን ነገር ማድረግ አይችልም፡፡ ሰው ውስን ነው፡፡ ሚስት ከባል ልዩ ፍቅር ትፈልጋለች፡፡ ሰው ከሚስቱ ጋር ለመጣበቅ  ልዩ ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡  ሰው አባቱንና እናቱን ሳይተው ከሚስቱ ጋር መጣበቅ አይችልም፡፡ ሰው አባቱንና እናቱን ካልተወ በስተቀር ከሚስቱ ጋር የሚጣበቅበት አቅም አይኖረውም፡፡ ሚስት ከምትፈልገው ልዩ እንክብካቤና ፍቅር አንፃር ሰው አባቱንና እናቱን ሳይተው በሚስቱ መጣበቅ አይችልም፡፡ ሰው አባቱንና እናቱን ሳይተው ከሚስቱ ጋር መጣበቅ የሚችልበት ትርፍ አቅም የለውም፡፡ ሰው ለሚስቱ ሙሉ ፍቅርና ትኩረት ለመስጠት እንዲችል እናቱንና አባቱን መተው ግዴታው ነው፡፡
ከሚስቱም ጋር ይተባበራል
ፍቅር በመረዳት ራስን ከሌላው ጋር ማስተባበር ነው፡፡ ፍቅር የሌላውን ድካም የራስ ድካም አድርጎ መሸከም ነው፡፡ ፍቅር የሌላውን ገመና እንደራሰ ገመና መሸፈን ነው፡፡ ፍቅር በሌላው ስም መጠራት ለመጠራት መፍቀድ ነው፡፡ ፍቅር ከሌላው ደረጃ ጋር ራስን ማስተባበር ነው፡፡ ፍቅር ሌላውን ሳያሻሽሉ እንዳለ መቀበል ነው፡፡ ፍቅር ከሌላው ጋር ለመቆጠር መፍቀድ ነው፡፡ ፍቅር ከሌላው ጋር ማበር ነው፡፡ ፍቅር  ሌላው ካለው ፣ ከሆነውና ከሚያደርገው ጋር ማበር ነው፡፡
ሰው እናቱንና አባቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፡፡  ሰው ከሚስቱ ጋር ራሱን ያስተባብራል፡፡ ሰው የሚስቱን ስም ይወስዳል፡፡ ሰው የሚስቱን ነገር እንደራሱ ይቀበላል፡፡ ሰው ለሚስቱ ሃላፊነትን ይወስዳል፡፡  ሰው ከሚስቱ ጋር ይቆጠራል፡፡ ሰው የሚስቱን ደረጃ ይወስዳል፡፡ ሰው ሚስቱ ካላት ፣ ከሆነችውንና ከምታደርገው ነገር ጋር ያብራል፡፡
ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ
አንድ ስጋ መሆን ማለት መዋሃድ ማለት ነው፡፡ አንድ ስጋ መሆን ማለት ሌላውን እንደራስ መውደድ ማለት ነው፡፡ አንድ ስጋ መሆን ማለት አለመለያየት አለመከፋፈል አንድ መሆን ማለት ነው፡፡
መፅሃፍ ቅዱስ ስለፍቅር ሲናገር ሌላውን የመውደድ ደረጃ ራስን የመውደድ ደረጃ እንደሆነ ያሰተምራል፡፡ ሰው ግፋ ቢል ራሱን በሚያከብርበት አከባበር ብቻ ነው ሌላውን ሊያከብር የሚችለው፡፡ ሰው ራሱን በሚወድበት መውደድ ነው ሌላውን መውደድ የሚችለው፡፡ ሰው ለራሱ ዋጋ በሚሰጥበት ደረጃ ብቻ ነው ለሌላው ዋጋ ሊሰጥ የሚችለው፡፡ ሰው ለራሱ በሚሳሳበት መጠን ብቻ ነው ለሌላው ሊሳሳ የሚችለው፡፡ ሰው ነፍሱን ከሚወድበት መጠን በላይ የሌላውን ነፍስ አይወድም፡፡ ሰው ራሱን በሚንከባከብበት መጠን ብቻ ነው ሌላውን ሰው የሚንከባከበው፡፡
ሁለተኛይቱም፦ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የምትል እርስዋን የምትመስል ይህች ናት። ከእነዚህ የምትበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለችም። ማርቆስ 12፡31
ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል ያለው፡፡
እንዲሁም ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤ ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና፥ ነገር ግን የአካሉ ብልቶች ስለሆንን፥ ክርስቶስ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደረገላት፥ ይመግበዋል ይከባከበውማል። ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ። ኤፌሶን 5፡28-31
ሰው ለራሱ አክብሮት እንዳለው የሚታየው ለሚስቱ በሚያሳየው አክብሮት ነው፡፡ የገዛ ስጋውን የሚጠላ ሰው እንደሌለ ሁሉና ሰው ስጋውን እንደሚመግበውና እንደሚንከባከበው ሁሉ ሰውም ሚስቱን ይመግባል ይንከባከባል፡፡ ራሴን እወዳለሁ ስጋዬን አልወደውም የሚል ሰው እንደሌለ ሁሉ ለራሱ አክብሮትና ፍቅር ያለው ሰው ለሚስቱ አክብሮትና ፍቅር ይኖረዋል፡፡   
እግዚአብሔር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት፤ ወደ አዳምም አመጣት። አዳምም አለ፦ ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፥ ሥጋም ከሥጋዬ ናት፤ እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል። ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፥ በሚስቱም ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ። ዘፍጥረት 2፡22-24
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ህይወት #ጋብቻ #ትዳር #ባል #ሚስት #ፍቅር #መውደድ #ይተዋል #ይጣበቃል #አንድስጋ #እውነት #ትህትና #ትንሳኤ #ህይወት #ወንጌል #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ  #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

No comments:

Post a Comment