Popular Posts

Follow by Email

Thursday, August 10, 2017

እንደተቀመጠ መመላለስ

ክርስቶስ የሃጢያታችንን እዳ ሁሉ በመስቀል ላይ ከመክፈሉ የተነሳ በክርስቶስ በአብ ቀኝ መቀመጥ ችለናል፡፡ ክርስትናን በሙላት ለመኖር ከክርስቶስ በአብ ቀኝ መቀመጣችን ግዴታ ነበር፡፡
በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን። ኤፌሶን 2፡6-7
ክርስትና ተግባራዊ ኑሮ ነው፡፡ ካልተቀመጥንና ከተቀመጥነበት የክብርና የስልጣን ስፍራ አስተሳሰብ ካልተነሳን ለእግዚአብሄር እንደሚገባ መመላለስ አንችልም፡፡ ተመላለሱ የሚለውን የጌታን ትእዛዝ መፈፀም የምንችለው ስለመቀመጣችን መረዳት ሲኖረን ነው፡፡ ስለመቀመጣችን ጌታን እንደ አዳኝ ከመቀበል ውጭ ምንም ያደረግነው የለም፡፡ ግን መቀመጥ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ከእግዚአብሄር ቃል ካልተረዳን ግን የመቀመጥን ጥቅም ተጠቃሚዎች መሆን አንችልም፡፡  
በክርስቶስ በአብ ቀኝ እንደተቀመጠ ያልተረዳ ሰው ለእግዚአብሄር እንደሚገባ መመላለስ አይችልም፡፡ እንደተቀመጠ የሚያውቅ ሰው ደግሞ እንደተቀመጠ ሰው ይመላለሳል፡፡ እንደተቀመጠ የሚያውቅ ወይም የማያውቅ ሰው በህይወቱ ይታያል፡፡
ሰው በክርስቶስ በአብ ቀኝ ተቀምጦ እንዳልተቀመጠ መኖር ይችላል፡፡ መቀመጡን ያላወቀ ሰው የሚመላለሰው እንዳልተቀመጠ ሰው ነው፡፡
ያልተቀመጠ ሰው የሚመላለስባቸውምን መንገዶች እንመልከት፡-
1.      እንደተቀመጠ የማያውቅ ሰው አያርፍም፡፡

እንደተቀመጠ የማያውቅ ሰው ነገሮችን የሚያደርገው በእረፍት አይደለም፡፡ እንደተቀመጠ ያልተረዳ ሰው ህይወቱ በግፊት የተሞላ ነው፡፡ እንደተቀመጠ ላልተረዳ ሰው መፀለይ ጭንቅ ነው ፣ የእግዚአብሄርን ቃል ማንበብና ማጥናት ተራራ ነው ፣ እንደተቀመጠ ላልተረዳ ሰው ከወንድሞች ጋር ህብረት ማድረግ ከባድ ስራ ነው ፣ በአብ ቀኝ እንደተቀመጠ ላልተረዳ ሰው ለሌላው የኢየሱስን አዳኝነት መመስከር መከራ ነው፡፡  

2.     እንደተቀመጠ የማያውቅ ሰው ይጨነቃል፡፡

በአብ ቀኝ የተቀመጠበትን የልጅነት ስፍራ እና የእግዚአብሄር ቤተሰብ አባልነቱን ክብር ያልተረዳ ሰው ስለሚባላውና ስለሚጠጣው ሲጨነቅ ህይወቱን ያባክናል፡፡ በአብ ቀኝ እንደተቀመጠ ያልተረዳ ሰው የህይወት ግቡ የእግዚአብሄርን መንግስትና ፅድቁን መፈለግ ሳይሆን እንደምራቂ የሚጨመረውን አህዛብ የሚፈልጉትን ነገር በመከተል ነው፡

ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል። ማቴዎስ 6፡33-34

3.     እንደተቀመጠ የማያውቅ ሰው አይቆምም ይናወጣል፡፡  

በአብ ቀኝ እንደተቀመጥን መረዳታችን የሚታየው በአስቸጋሪ ጊዜ ነው፡፡ ነገሮች እንደፈልግናቸውና እንዳሰብናቸው ባልሄዱ ጊዜ ከሩጫችን የምናቆምና እጃችንን የምንሰጥ ከሆነ በአብ ቀኝ መቀመጣችንን አልተረዳንም፡፡ ክርስቶስን በመቀበላችን እንዲያው በነፃ የእኛን ምንም ጥረት ሳይጨምር የተሰጠንም ቢሆንም እንኳን በአብ ቀኝ መቀመጣችንን መረዳት ግን በህይወታችን ልዩነትን ያመጣል፡፡  

ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፤ ጸንታችሁ ቁሙ፤ በምንም ነገር አትናወጡ። ለጌታ ሥራ ዘወትር የምትተጉ ሁኑ፤ ምክንያቱም ለጌታ የምትደክሙት በከንቱ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ። 1ኛ ቆሮንቶስ 15፡58

4.     እንደተቀመጠ የማያውቅ ሰው በነገሮች ይፈራል፡፡

በክርስቶስ በአብ ቀኝ ወደ ተቀመጠ ሰው ፍርሃት በፍፁም ሊመጣ አይችልም ብንል እውነት አይሆንም፡፡ ነገር ግን በክርስቶስ በአብ ቀኝ እንደተቀመጠ የሚያውቅ ሰው ፍርሃትን እንደማያስተናግድ እናውቃለን፡፡ እንደተቀመጠ ያወቀ ሰው ፍርሃት አያቆመውም፡፡ እንደተቀመጠ ያወቀ ሰው ፍርሃቱ እያለ ስሜቱን ሳይከተል የእግዚአብሄርን ፈቃድ በመፈፀም ይቀጥላል፡፡
  
እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና። 2ኛ ጢሞቴዎስ 1፡7

5.     እንደተቀመጠ የማያውቅ ሰው ምስኪን እኔ አስተሳሰብ ይኖረዋል፡፡

በአብ ቀኝ እንደተቀመጠ የማያውቅ ሰው ስለማንነቱ እርግጠኛ ባለመሆኑ የምስኪንነት ስሜት ይሰማዋል፡፡ እንደተቀመጠ የማያውቅ ሰው የበታችነት ስሜት ያጠቃዋል፡፡ ያንን የበታችነት ስሜት ለመቋቋም ደግሞ በበላይነት ስሜት ሊያካክሰው ይሞክራል፡፡ የበታችነት ስሜት ያለበት ሰው ያንን ለማካካስ ሰዎችን በመቆጣጠር የበላይነት ስሜቱን ሊያሳይ ይጥራል፡፡ ምስኪን እኔ አስተሳሰብ ያለበት ሰው ውድድሩ ሳይጀመር እጁን ይሰጣል፡፡ አልችልም አላልፍም አልወጣም በሚል አስተሳሰን ተሞልቶዋል፡፡ በአብ ቀኝ እንተቀመጠ ያልተረዳ ሰው የእርሱ መጨረሻ በሰዎች እጅ እንደሆነ ይመስለዋል፡፡

ስለዚህም ምክንያት ይህን መከራ ደግሞ ተቀብዬአለሁ፥ ነገር ግን አላፍርበትም፤ ያመንሁትን አውቃለሁና፥ የሰጠሁትንም አደራ እስከዚያ ቀን ድረስ ሊጠብቅ እንዲችል ተረድቼአለሁ።2ኛ ጢሞቴዎስ 1፡12

6.     እንደተቀመጠ የማያውቅ ሰው የተሸነፈ ኑሮ ይኖራል፡፡

በእግዚአብሄር ቀኝ እንደተቀመጠ የማያውቅ ሰው በሰይጣን ምህረት እንደሚኖር ይሰማዋል፡፡ ሰይጣን አስኮናኝ ኑር ብሎ ካልደፈቀደለት ዋጋ እንደሌለው ይሰማዋል፡፡ የእርሱ መጨረሻ በሰይጣን መጠንከርና አለመጠንከር በአለም መጠንከርና አለመጠንከር እንደሚደገፍ ይሰማዋል፡፡ እንደተቀመጠ የማያውቅ ሰው በሰይጣን ፊት ተሸናፊ ነው፡፡ በአብ ቀኝ እንደተቀመጠ የማያውቅ ሰው በአለምና በምኞትዋ ፊት የተሸነፈ ነው፡፡

ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። 1ኛ ቆሮንቶስ 15፡57

በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ሮሜ 8፡37

በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን። ኤፌሶን 2፡6-7

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እረፍት #ቅድሚያ #መቀመጥ #ሰማያዊ #በክርስቶስ #በጌታ #እምነት #መደገፍ #ሰንበት #በመንፈሴ #በሃይል #በብርታት #ፀጥታ #መመለስ #ማረፍ #ፅድቁን #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ፀጥታ #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #መታመን #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment