Popular Posts

Follow by Email

Wednesday, August 23, 2017

666 እና የመጨረሻው ዘመን

የምንኖረው በመጨረሻ ዘመን ውስጥ ነው፡፡ ኢየሱስ ባልታሰበና ባልተገመተ ሰአት ድንገት እንደሌባ ይመጣል፡፡
ወንድሞች ሆይ፥ ስለ ዘመናትና ስለ ወራት ምንም እንዲጻፍላችሁ አያስፈልጋችሁም፤ የጌታ ቀን፥ ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ፥ እንዲሁ ይመጣ ዘንድ ራሳችሁ አጥብቃችሁ አውቃችኋልና። 1 ተሰሎንቄ 5፡1-2
ስለዚህ ለመጨረሻው ዘመን ጥያቄዎች ቁልፉ መዘጋጀትና መዘጋጀት ብቻ ነው፡፡ ከተዘጋጀን እንወሰዳለን ካልተዘጋጀን አንወሰድም፡፡ ስለዚህ ነው የእግዚአብሄር ሰው ማርቲን ሉተር ኢየሱስ ትላንት እንደሞተ ነገ ተመልሶ እንምደሚመጣ አድርጋችሁ ሁል ጊዜ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ ያለው፡፡
ሰዎች ኢየሱስ ይመጣል ብለው ኑሮ አቁመው ኢየሱስን ይጠብቁ በነበረበት በጳውሎስም ዘመን ሐዋሪያው ጳውሎስ በወሬ አትናወጡ እያለ ኢየሱስ እንደ ድንገት ቢመጣም ግን ያልተፈፀሙ ትንቢቶች እንደነበሩና እሰከዚያም በትጋት የጌታን ስራ መሰራት እንዳለባቸው ይመክራቸዋል፡፡  
በመልእክት፦ የጌታ ቀን ደርሶአል ብላችሁ፥ ከአእምሮአችሁ ቶሎ እንዳትናወጡ እንዳትደነግጡም እንለምናችኋለን። 2ኛ ተሰሎንቄ 2፡1-2
አሁንም በዚህ ዘመን ኢየሱስ የመምጫውን ትክክለኛ ጊዜ ለማወቅ ሰዎች ዘመንን ይመረምራሉ፡፡ በሚያዩዋቸውም ምልክቶች ሲናወጡ ይታያል፡፡
ኢየሱስ ግን ስለዚያች ሰዓት የሚያውቅ ሰው የለም ብሎዋል፡፡
ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያች ሰዓት ግን የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን ከአባት በቀር የሚያውቅ የለም። ማርቆስ 13፡32
የኢየሱስ መምጫውን ትክክለኛ ጊዜ ለመለየት ሰዎች በአለም ላይ የሚሆኑትን ነገሮች ለመተንተን ይሞክራሉ፡፡ በተለይ 666 ምልክትን በተመለከተ ብዙ ፍርሃትና መደናገጥ መናወጥ እንዳለ በተለያዩ ፅሁፎች መረዳት ይቻላል፡፡
በተለይ በባንክ ካርዳችን ላይ ስላለው የማግኔት ከቴክኖሎጂና በአካል ውስጥ ይቀበራል ስለሚባለው ቺፕስ የ 666 መንገድ ነው ተብሎ በመታመኑ ብዙ ፍርሃትና መናወጥ ይታያል፡፡
መፅሃፍ ቅዱስ ግን በተለይ ስለ 666 ምን እንደሚል አምስቱን ዋና ዋና ሃሳቦች እንመልከት፡፡
ታናናሾችና ታላላቆችም ባለ ጠጋዎችና ድሆችም ጌታዎችና ባሪያዎችም ሁሉ በቀኝ እጃቸው ወይም በግምባራቸው ምልክትን እንዲቀበሉ፥ የአውሬውም ስም ወይም የስሙ ቍጥር ያለው ምልክት የሌለበት ማንም ሊገዛ ወይም ሊሸጥ እንዳይችል ያደርጋል። ጥበብ በዚህ አለ። አእምሮ ያለው የአውሬውን ቍጥር ይቍጠረው፤ ቍጥሩ የሰው ቍጥር ነውና፥ ቍጥሩም ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ነው። ራእይ 13፡16-18
1.      የአውሬው ምልክት ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ነው፡፡
የአውሬው ምልክት አወዛጋቢ ምልክት አይደለም፡፡ የአውሬው ምልክት ሰዎች በተለያየ ጊዜ ይህ ምልክታቸው ነው ያ ምልክታቸው ነው ብለው እንደሚናገሩት ብዙ አይነት ምልክት አይደለም፡፡ የአውሬው ምልክት ሚስጥራዊ በብዙ ማባዛትና ማካፈል የሚገኝ ውስብስብ ቁጥር አይደለም፡፡ የአውሬው ቁጥር የማይታወቅ ለመረዳት እጅግ አስቸጋሪ የሚስጠር ቁጥር አይደለም፡፡ የአውሬው ቁጥር የሚገመት ያለጠራ አወዛጋቢ ቁጥር አይደለም፡፡ የአውሬው ቁጥር የተደበቀ ረቂቅ ቁጥር አይደለም፡፡ የአውሬው ቁጥር የሰው ቁጥር ነው፡፡ የአውሬው ቁጥር ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ነው፡፡
2.     ይህ ምልክት በግንባር ወይው በቀኝ እጅ ላይ የሚታይ ምልክት ነው፡፡
ይህ ቁጥር በሚስጥር የሚያዝ የምስጢራዊ ቡድን መለያ አይደለም፡፡ ይህ ቁጥር በግልፅ የሚታይ ቁጥር ነው፡፡ ለምሳሌ ገንዘብን ሁሉም ሰው እንደሚያውቀውና ሁሉም ሰው ቆጥሮና ተማምኖ በግልፅ እንደሚገበያይበት ይህም ቁጥር ግልፅ ቁጥር ነው፡፡ ቁጥሩ ግልፅ ቁጥር ካይደለ በመፅሃፍ ቅዱስ ላይ የተፃፈው የክፋት ቁጥር አይደለም፡፡ ቁጥሩ ሰው ሁሉ ሊያይ በሚችልበት ሁኔታ ግንባር ላይ ወይም ደግሞ ቀኝ እጅ ላይ በግልፅ የሚታይ ነው፡፡
3.     ይህን ምልክት የሌለው ሰው መገበያየት አይችልም፡፡
ይህ ቁጥር የሌለው ሰው መገበያየት አይችልም፡፡ ይህ ቁጥር የማጌጫ ወይም የመዘነጫ ቁጥር አይደለም፡፡ ብር ህጋዊ የመገበያያ ገንዘብ እንደሆነና ሰዎች በብር ካልሆነ እንደማይገበያዩ ሁሉ ይህ ቁጥር በስራ ላይ ከዋለ ከምሮ ያንን ቁጥር በግንባሩ ወይም በእጁ ላይ ያልያዘ አይገዛም አይሸጥም፡፡
ይህን ቁጥር የተሸናፊዎች እና የተከታዮቻቸው ቁጥር ነው፡፡
4.     ሰይጣን የአውሬውን ቁጥር 666 አይጠብቅም
ሰይጣን በኢየሱስ የመስቀል ስራ ሙሉ ለሙሉ በመሸነፉ የተነሳ አሁን የሚጠቀመው የቀረውን ማታለል ብቻ ነው፡፡ ሰይጣን የአውሬውን 666 አይጠብቅም፡፡ ሰይጣን በክርስቶስ ያለሆኑትን ሁሉ እየገዛ ነው፡፡
በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ በእነርሱም፥ በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው። ኤፌሶን 2፡1-2
ሰይጣን በክርስቶስ የሆኑት ካለ እውቀት ከፈቀዱለት ያታልላቸዋል፡፡ ሰይጣን በጌታ የሆኑትን የሚያገኝበት ብቸኛው መንገድ ማታለል ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል ያልተረዱትን ክርስትያኖች በማታለል እንደ አለማዊ እንዲኖሩ ያደረጋቸዋል፡፡ ክርስትያን በመታለል ካልፈቀደለት በስተቀር ሰይጣን ምንም ማድርግ አይችለም፡፡
እንዲህም አላቸው ሰይጣንን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ። እነሆ፥ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ፥ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፥ የሚጐዳችሁም ምንም የለም። ሉቃስ 10፡18-19
የክርስቶስ ተከታዮች በእግዚአብሄር ቃል እውቀት ማነስ ካልተታለልን በስተቀር በዲያቢሎስ ግዛት ውስጥ አይደለንም ሰይጣን ሊገዛን አይችልም፡፡ ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት የሚለው፡፡
በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት። ኤፌሶን 4፡27
5.     ሰይጣን የተሸነፈ ጠላት ነው፡፡
ሰይጣን የተሸነፈ ጠላት ነው፡፡ ሰይጣን የመጨረሻ ፍርዱን እየጠበቀ ያለ መጨረሻው ጥፋት መሆኑ የታወቀ ተስፋ የሌለው ፍጡር ነው፡፡ 666 ይምጣም አይምጣም የክርስቶስ ተከታዮች አሸናፊዎ ናቸው፡፡ ኢየሱስ ስለእኛ ሰይጣንን በሞቱ ድል ነስቶታል፡፡
አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው። ቆላስይስ 2፡15
ወደ ውድድሩ የምንገባው ማሸነፋችንን አውቀን ነው ፡፡ እድላችን የታወቀ ነው፡፡ እንደምናሸንፍ የታወቀ ነው፡፡ የትንቢቱ መፈፀም የሚያበረታታን እንጂ እኛን ሊያናውጠን የሚችል ምንም አዲስ ነገር የለም፡፡
ስለ ፍርድም፥ የዚህ ዓለም ገዥ ስለ ተፈረደበት ነው። ዮሃንስ 16፡11
ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው። 1ኛ ዮሃንስ 5፡4
ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትና ወደ እርሱ ስለ መሰብሰባችን፥ በመንፈስ ወይም በቃል ወይም ከእኛ እንደሚመጣ በመልእክት፦ የጌታ ቀን ደርሶአል ብላችሁ፥ ከአእምሮአችሁ ቶሎ እንዳትናወጡ እንዳትደነግጡም እንለምናችኋለን። 2 ተሰሎንቄ 2፡1-2
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #666 #ስድስትመቶስድሳስድስት #በግንባራቸው #በቀኝእጃቸው #የአውሬውምልክት #ክብር #ኢየሱስይመጣል #እንደሌባ #በድንገት #ዋጋ #እውቀት #ኢየሱስንተመልክተን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና #እምነት #ታላቅነት #ማገልገል #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment