Popular Posts

Follow by Email

Wednesday, August 9, 2017

የመቀመጥ እውነተኛ ትርጉም

በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን። ኤፌሶን 2፡6-7
ኢየሱስ በመስቀል ላይ ያደረገውን ነገር ሁሉ ያደረገው ለእኛ ነው፡፡ ኢየሱስ የተገረፈው ስለደዌው አይደለም ስለእዐኛ ደዌ እንጂ፡፡ ኢየሱስ የሞተው ስለሃጢያቱ አይደለም ስለእኛ ሃጢያት እንጂ፡፡ ኢየሱስ የተቀበረው በሃጢያቱ ስለሞተ አይደለም በሃጢያታችን ስለሞትን እንጂ፡፡ ኢየሱስ የተነሳው ስለሃጢያቱ ስለሞተ አይደለም፡፡ ስለሃጢያታችን ስለሞትን በእኛ ምትክ እንጂ፡፡ ኢየሲስ በአብ ቀፅ የተቀመጠው በአብ ቀኝ ስላልነበረ አይደለም፡፡ እኛ በአብ ቀኝ እንድንቀመጥ እንጂ፡፡
ኢየሱስ በአብ ቀኝ የተቀመጠው ስለእኛ ነው፡፡ ኢየሱስ በአብ ቀኝ የተቀመጠው ስለእኛ ነው፡፡ ኢየሱስ በአብ ቀኝ የተቀመጠው እኛን ወክሎ ነው፡፡
በክርስቶስ በአብ ቀኝ ተቀምጠናል ማለት ምን ማለት ነው፡፡ በአብ ቀኝ የመቀመጣችን ትርጉሙ ምንድነው
1.      በክርስቶስ በአብ ቀኝ መቀመጣችን እግዚአብሄር ሙሉ ለሙሉ አንደተቀበለን ያሳያል፡፡

በክርስቶስ የመስቀል ስራ ምክኒያት እግዚአብሄር ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎናል፡፡ኢየሱስ የሃጢያታችን እዳ ሁሉ በመስቀል ላይ በመክፈሉ እግዚአብሄር እኛን ለመቀበል ደስ ብሎታል፡፡ እኛን ለመቀበል ኢየሱስ በሰራው የመስቀል ስራ እግዚአብሔር ረክቷል፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሃጢያታችንን እዳ ሁሉ ስለከፈለ እግዚአብሄር ከዚህ በላይ የሚጠብቀው ምንም መስዋእት የለም፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ፈፅሞ ከከፈለው የሃጢያት ዋጋ የተነሳ ኢየሱስን እንደ አዳኝ የተቀበልን እኛን እንዳለን ተቀብሎናል፡፡

ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ዮሃንስ 1፡12

ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን፤ ሮሜ 5፡10

2.     በክርስቶስ በአብ ቀኝ መቀመጣችን በጨለማው አለም ላይ ያለንን ስልጣናችንን ያሳያል፡፡

ከክርስቶስ ጋር በአብ መቀመጣችን የእግዚአብሄርን ስራ በምድር ላይ አንዳንፈፅም የሚያግደን ምንም የጠላት ሃይል አስከማይኖር ድረስ በጠላት ሃይል ሁሉ ላይ ስልጣን እንደተሰጠን ያሳያል፡፡

እርሱም መላእክትና ሥልጣናት ኃይላትም ከተገዙለት በኋላ ወደ ሰማይ ሄዶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 3፡22

ለምናምን ከሁሉ የሚበልጥ የኃይሉ ታላቅነት ምን እንዲሆን ታውቁ ዘንድ ነው፤ ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል፤
ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛለት ከሁሉ በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተ ክርስቲያን ሰጠው። እርስዋም አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚሞላ የእርሱ ሙላቱ ናት። ኤፌሶን 1፡18-23

እነሆ፥ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ፥ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፥ የሚጐዳችሁም ምንም የለም።ሉቃስ 10፡19

3.     በክርስቶስ በአብ ቀኝ መቀመጣችን በእግዚአብሄር ዘንድ ያለንን ክብር ያሳያል፡፡

ኢየሱስ ወደምድር የመጣው ስለሃጢያታችን ሊሞት ብቻ አይደለም፡፡ ኢየሱስ ወደምድረ የመጣው የእግዚአብሄር ልጅነትን ክብር ናሙና ሊያሳየን ነው፡፡ ኢየሱስ እንደሰው በምድር የተመላለሰው የእግዚአብሄር ልጅነትን ክብር ምሳሌ ሊሰጠን ነው፡፡ ስለዚህ ነው ኢየሱስ እኔ ያደረግኩትን ከዚህም በላይ ታደርጋላችሁ ያለው፡፡  

ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን። ዮሃንስ 1፡14

እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ፤ እኔም በእነርሱ አንተም በእኔ ስትሆን፥ በአንድ ፍጹማን እንዲሆኑ፥ የሰጠኸኝን ክብር እኔ ሰጥቻቸዋለሁ፤ እንዲሁም ዓለም አንተ እንደ ላክኸኝ በወደድኸኝም መጠን እነርሱን እንደ ወደድሃቸው ያውቃል። ዮሃንስ 17፡22-23

4.     በክርስቶስ በአብ ቀኝ መቀመጣችን ወደ እግዚአብሄር መነግስት መፍለሳችንን ያሳያል፡፡

ኢየሱስ በሞቱ የሰይጣንን ሃይል ድል በመንሳቱ እግዚአብሄር ከጨለማው ስልጣን አድኖናል፡፡ ወደፍቅሩ ልጅ መንግስት አፍልሶናል፡፡ አሁን ያለነው በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ነው፡፡ ዜግነታችን ሰማያዊ ነው፡፡
እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን። ቆላስይስ 1፡13-14

5.     በክርስቶስ በአብ ቀኝ መቀመጣችን የእግዚአብሄርን ወራሽነታችንን ያሳያል፡፡

በክርስቶስ በአብ ቀኝ መቀመጣችን የእግዚአብሄር ወራሽ መሆናችንን ያሳያል፡፡ ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን፡፡ ስለወደፊታችን ምንም አወዛጋቢ ነገር የለውም፡፡ እኛ የእርሱ መሆናችንና የእግዚአብሄር ወራሾች መሆናችንን ለማሳየት መንፈሱን ቀብድ ሰጥቶናል፡፡

በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ፤ እርሱም የርስታችን መያዣ ነው፥ ለእግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እስኪዋጅ ድረስ፥ ይህም ለክብሩ ምስጋና ይሆናል። ኤፌሶን 1፡13-14

እንደ ፈቃዱ ምክር ሁሉን የሚሠራ እንደ እርሱ አሳብ፥ አስቀድመን የተወሰንን በክርስቶስ ደግሞ ርስትን ተቀበልን። ኤፌሶን 1፡11

ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ ማለት የእግዚአብሔር ወራሾች ነን፥ አብረንም ደግሞ እንድንከበር አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን። ሮሜ 8፡17

6.     በክርስቶስ በአብ ቀኝ መቀመጣችን ከእግዚአብሄር ጋር ማረፋችንን ያሳያል፡፡

የእግዚአብሄር ልጆች ነን፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር አብረን የምንሰራ ነን፡፡ እርሱ የሚሰራውን ነው የምንሰራው፡፡ እርሱ የጀመረውን ነው የምንጨርሰው፡፡ በእርሱ ሃይል ነው የምንሰራው፡፡ እርሱ ነው ከእኛ ውስጥ የሚሰራው፡፡ በእርሱ መንፈስ ነው የምንሰራው፡፡ የምንሰራውን ሁሉ የምንሰራው በእረፍት ነው፡፡ እድላችንን እየሞከርን አይደለም፡፡ የምንጋደለው ገድል ውጤቱ የታወቀ ነው፡፡ አስቀድመን አሸናፊዎች ተደርገናል፡፡ አስቀድመን መጨረሻችን ታውቆዋል፡፡ አስቀድመን ተወስነናል

ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤ አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው። ሮሜ 8፡29-30

በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ሮሜ 8፡37
በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን። ኤፌሶን 2፡6-7
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እረፍት #ቅድሚያ #መቀመጥ #ሰማያዊ #በክርስቶስ #በጌታ #እምነት #መደገፍ #ሰንበት #በመንፈሴ #በሃይል #በብርታት #ፀጥታ #መመለስ #ማረፍ #ፅድቁን #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ፀጥታ #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #መታመን #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment