Popular Posts

Wednesday, August 2, 2017

የፍቅር ሌላኛው ገፅታ

ፍቅርን በአንድ ቃል ወይም አረፍተነገር መግለጽ ያስቸግራል፡፡ ስለፍቅር የተለያዩ ትርጉሞች ተሰጥተዋል፡፡ ፍቅር ስለሌላው መልካም ማሰብ ፣ መልካም መናገርና መልካም ማድረግ ነው፡፡ ፍቅር ራስን ከሌላው ጋር በመረዳት ማስተባበር ነው፡፡
ፍቅርን ሙሉ ለሙሉ ባይገልፁትም ግን የፍቅርን የተለያየ ገፅታ ሊያሳዩ የሚችሉ ቃላቶችን መዘርዘር ይቻላል፡፡
ፍቅር ርህራሔ ነው፡፡
ለሰው ርህራሔ ካለን ፍቅር አለን ማለት ነው፡፡ የሰውን ጉዳት ማየት አለመፈለግ ፍቅር ነው፡፡ የሰውን ውድቀት አለመመኘት ፍቅር ነው፡፡  
ፍቅር ይቅርታ ነው ፡፡
ፍቅር በሰው ላይ በደልን ባለመያዝ ይገለፃል፡፡ ፍቅር ይቅር ማለት ነው፡፡
እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ ነው፥ ከቍጣ የራቀ ምሕረቱም የበዛ። መዝሙር 103፡8
ፍቅር መተው ነው፡፡ 
የምንወደውን ሰው እዳውን እንተውለታለን፡፡ ከእኔ ይለፍ ይጠቀም እንላለን፡፡ ፍቅር የተበደሉትን መተው ነው፡፡ ፍቅር እንደተበደሉት በበደል አለመመለስ ነው፡፡ ፍቅር ሲወሰድበት ማለፍ ነው፡፡ ፍቅር ነገሮችን በትግስት ማለፍ ነው፡፡   
ፍቅር መስጠት ነው፡፡
ፍቅር መልካምነትን መስጠትና ማካፈል ነው፡፡
በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዮሃንስ 3፡16
ፍቅር ለሁልጊዜ አለመቆጣት ነው፡፡
ፍቅር ቁጣን ይረሳል፡፡ ፍቅር በክፉ አይፈርድም፡፡ ፍቅር በክፉ አይቀጣም፡፡ ፍቅር በክፉ አያሳድድም፡፡
እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ ነው፥ ከቍጣ የራቀ ምሕረቱም የበዛ። ሁልጊዜም አይቀሥፍም፥ ለዘላለምም አይቈጣም። መዝሙር 103፡8-9
ፍቅር በሰዎች መዳን መደሰት ነው፡፡
ፍቅር በሰዎች መዳን ፣ ማግኘትና መነሳት ይደሰታል፡፡ ፍቅር የሰዎች ማግኘት እረፍት አይነሳውም፡፡ ፍቅር የሰዎችን ማግኘት ከእርሱ ማግኘት ጋር አያስተያየውም፡፡
ፍቅር አይቀናም፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 13፡4
ፍቅር ሰዎችን መታገስ ነው፡፡
ሰዎችን የማይታገስ ሰውና ሁሉ ነገር በራሱ ፍጥነት እንዲሄድ የሚፈልግ ሰው ለሌላው ፍቅር የሌለው ሰው ነው፡፡ ለሰው ፍቅር ያለው ሰው በደካማው ፍጥነት በመሄድ ከደካማው ጋር ይተባበራል፡፡
በትሕትና ሁሉና በየዋህነት በትዕግሥትም፤ እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ፤ ኤፌሶን 4፡2
ፍቅር ሰዎችን ማክበር ነው፡፡
ለሰዎች አክብሮት የሌለው ሰው ፍቅር የጎደለው ሰው ነው፡፡ ራስን ከፍ ለማድረግ ሰዎችን ማሳነስ ፍቅር አይደለም፡፡ ሰዎችን የሚያሳንስ ሰው ፍቅር የጎደለው ሰው ነው፡፡ በሰዎች ከፍታ ራሱን ከፍ ሊያደርግ የሚፈልግ ሰው በፍቅር አይመላለስም፡፡
ሁሉን አክብሩ፥ ወንድሞችን ውደዱ፥ እግዚአብሔርን ፍሩ፥ ንጉሥን አክብሩ። 1ኛ ጴጥሮስ 2፡17
ፍቅር ሌላውን ሰው ማስቀደም ነው፡፡
ፍቅር ሌላው ካንተ እንዲሻል በትህትና መቁጠር ነው፡፡ ፍቅር በትህትና ከሌላው ጋር መኖር ነው፡፡
ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤ ፊልጵስዩስ 2፡3
ፍቅር የሌላውን ደስታ መፈለግ ነው፡፡
ፍቅር የራስን ምቾትና ደስታ ብቻ ሳይሆን ለሌላው ምቾትና ደስታ ግድ መሰኘት ነው፡፡ ፍቅር ለሌላው የሚሰማን (sensitive) መሆን ነው፡፡
እያንዳንዳችን እንድናንጸው እርሱን ለመጥቀም ባልንጀራችንን ደስ እናሰኝ። ክርስቶስ ራሱን ደስ አላሰኘምና፤ ሮሜ 15፡2
ፍቅር የደካማውን ሸክም መሸከም ነው፡፡  
ፍቅር ከብርታታችን ተነስተን ደካማውን መኮነን አይደለም፡፡ ፍቅር በደካማው ላይ አለመፍረድ ነው፡፡ ፍቅር ደካማው የሚበረታበትን መንገድ መፈለግ ነው፡፡ ፍቅር ደካማውን ለማበርታት በትጋት መስራት ነው፡፡ ፍቅር ከደካማው ጋር ራስን ማስተባበር ነው፡፡
እኛም ኃይለኞች የሆንን የደካሞችን ድካም እንድንሸከም ራሳችንንም ደስ እንዳናሰኝ ይገባናል። ሮሜ 15፡1
ወንድሞች ሆይ፥ ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ፥ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት፤ . . . ከእናንተ እያንዳንዱ የአንዱን ሸክም ይሸከም እንዲሁም የክርስቶስን ሕግ ፈጽሙ። ገላትያ 6፡1-2
ፍቅር ለሌላው መጥቀምና ማስነሳት ነው፡፡  
እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፥ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ። ፊልጵስዩስ 2፡4
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ፍቅር #ስጦታ #ፍቅር #መውደድ #ትህትና #ሸክም #መስጠት #መጥቀም #ምህረ #ሃሳብ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #ቸርነት #ትግስት #ፍርሃት #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #መውደድ #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment