Popular Posts

Tuesday, August 29, 2017

ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም

እግዚአብሔር አምላክም አለ፦ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት። ዘፍጥረት 2፡18
ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም ሲል እግዚአብሔር የፈጠረው ሰው ምን አይነት ሰው እንደነበር እንመልከት፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረውን ሰው ስንመለከት ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም ያለውን ሰው መመልከት እንችላለን፡፡ እግዚአብሔር ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም ያለው ማንኛውምንም ሰው አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም ያለው ሙሉ የሆነን ሰው ነው፡፡  
እግዚአብሔር የፈጠረው ሙሉ ሰውን ነው፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው ከእግዚአብሔር ጋር የተሳካ ግንኙነት የነበረውን ሰው ነው፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው በእግዚአብንሔር የረካን ሰው ነው፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው አንድ ሴትን ሊያስተዳድር የሚችል ሙሉ ብቃት ያለውን ሰው ነው፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው ጎዶሎን ሰው አይደለም፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው 50 % ሰውን አይደለም፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው 100% ሰውን ነው፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው ቤተሰብ ሊመራ የሚችልን ሙሉ ሰውን ነው፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው ተለዋዋጭ ስሜቱን የሚከተልን ሰው ሳይሆን ሚስቱን በምንም ሁኔታ ውስጥ ሊወድድ የሚችልን የውሳኔን ሰው ነው፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው ለቤተሰቡ ሊያቀርብ የሚችል ጠንካራን ሰራተኛ ነው፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው ቤተሰብን ሊሸከም የሚችል ሙሉ ሰውን ነው፡፡
እግዚአብሔር የፈጠረው ሙሉ የምታደርገኝን ሴት እፈልጋለሁ ብሎ በጉድለት የሚጮኽን ሰው አይደለም፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው ተግዳሮት ሲመጣ የሚሸሽና በእርሱ ፋንታ የምታምንለትን ሴት የሚፈልግን ሰው አይደለም፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው ተባርኮ ለበረከት የሚሆንን ወንድ እንጂ ከምስኪንነት የምታነሳውን ሴት የሚፈልግን ወንድ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው በእግዚአብሔር ግንኙነት የረካን ወንድ እንጂ የምታሳልፍለትን ሴት የሚጠብቅን ወንድ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው ጎዶሎን ሰው አይደለም፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው ባለ ራእይን ሰው ነው፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው በመስጠት በመባረክ በማካፈል ላይ ያተኮረን ሰው ነው፡፡
እግዚአብሔር የፈጠረው ሰው ስልጣኑን ከማወቁ የተነሳ ሺን የሚያሳድድን ሰው ነው፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው ሰው እግዚአብሔር ባዘጋጀው አሰራር በትዳር ከአንድ ሴት ጋር አስር ሺን ሊያሳድድ የተዘጋጀን ሰው ነው፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው አንድን ሴት ሊባርክ የተዘጋጀን የተባረከን ሰው ነው፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው አንድን ሴት ሊመራትና የተሻለውን ከውስጥዋ ሊየወጣ የተዘጋጀን ሰው ነው፡፡
እግዚአብሔር የፈጠረው በራስዋ የረካች አንድን ባለራእይ ልትረዳ የተዘጋጀችን ሴት ነው፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው የሚያነሳትን ባል የምትፈልግን ሴት ሳይሆን እግዚአብሔር ስለእኔ ምክኒያት ቤቱን ይባርካል ብላ የምታምንን የእምነትን ሴት ነው፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው የሚያሳልፍላትን ባል የምትፈልግን ሴት ሳይሆን እንደ ልጅ ከአባት እንዴት በፀሎት እንደምትቀበል የምታውቅን ሴት ነው፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው በመስጠት በመባረክ በማካፈል ላይ ያተኮረችን ሴት ነው፡፡
መፅሃፍ ቅዱስ ስለግንኙነት በረከት ሲናገር አንዱ ሺህ ሁለቱ ደግሞ ሁለት ሺህ ያሳድዳሉ አይደለም የሚለው፡፡ እንደዚያ ከሆነማ ሁለቱም ጎዶሎ በመሆናቸው 50 % ሊያዋጡ ነው ማለት ነው፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ ግን በህብረት ውስጥ ስለተቀመጣው ታላቅ እምቅ ሃይልክ ሲናገር አንዱ ሺህ ሁለቱ ደግሞ አስር ሺህ ያሳድዳሉ ነው የሚለው፡፡
ወንድና ሴት ከመጋባታቸው በፊት ሁለቱም በጌታ ሙሉ መሆን አለባቸው፡፡ በጌታ ሙሉ የሆነውን ሰው ነው መፅሃፍ ቅዱስ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም ያለው፡፡ ወንድ 100 % ሴትም መቶ % ሲሆኑ ነው ሲያብሩ አስር ሺህ የሚያሳድዱትና እግዚአብሔ በህብረት ውስጥ ያስቀመጠውን እምቅ ጉልበት የሚለቁት፡፡
ወንድና ሴት ግን ጎዶሎዎች ከሆኑና እርሱም በጎዶሎነት አስተሳሰብ ሙሉ የሚያደርገው ኢየሱስ ላይ ካላተኮረና የምትሞላውን ከፈለገ እርስዋም በዋናው በሚያረካው በእግዚአብሔር ካልረካችና በምስኪንነት አስተሳሰብ የሚሞላትን ከፈለገች ሁለቱም ሳይገናኙ መሃል ላይ ይቀራሉ፡፡ ሁለቱም ሙሉ የሚያደርጋቸውን ክርስቶስን ትተው በጎዶሎነት የሚሞላቸውን ሲፈልጉ እግዚአብሔር በትዳር ውስጥ ያስቀመጠው ታላቅ ሃይል ሳይገለጥ ይቀራል፡፡
ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም ያልሆነው ጎዶሎው እንዲሞላ ሳይሆን ሙላቱ እንዳይባክን ነው፡፡
ስለዚህ ነው ሰው ካገባም በኋላ አላግባብ በሚስቱ ላይ እንዳይደገፍ የእግዚአብሔር ቃል የሚመክረው፡፡ ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ ያላገባ ሰው በእግዚአብሔር ላይ መደገፉን እንዳይለውጥ የሚመክረው፡፡ ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ ሰው ለትዳሩ በሚሰጠው በሚያበረክተውና በሚያካፍለው ነገር ላይ እንጂ ከትዳሩ በሚጠቀመው ነገር ላይ ያለልክ እንዳይደገፍ የሚመክረው፡፡
ዳሩ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እናገራለሁ፤ ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ፥ 1ኛ ቆሮንቶስ 7፡29
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ህይወት #ጋብቻ #ትዳር #ባል #ሚስት #አንድስጋ #እውነት #ትህትና #ትንሳኤ #ህይወት #ወንጌል #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ  #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

No comments:

Post a Comment