በቤተሰብ አጋርነት በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ሰዎች ውስን ከመሆናቸው የተነሳ ለተሻለ ውጤት ሌላው ሰው ያስፈልጋቸዋል፡፡ የተሻለ ፍሬያማነት ያለው በግንኙነት አጋርነት ነው፡፡ አጋሮቻችን በበዙ ቁጥር ፍሬያማነታችን ይበዛል፡፡ እግዚአብሄር በአጋርነት ያስቀመጠውን በረከት እንዴት መጠቀም እንደምንችል በተረዳን ቁጥር በሁሉም ነገራችን እንሰፋለን እናድጋለን፡፡
ባል በረከት ነው፡፡ ወንድ በተፈጥሮው የራሱ ሞገስ አለው፡፡ ወንድ ሚስትን ሲያገኝ በረከቱ ይበዛል፡፡ ወንድ ሚስት ሲያገኝ ሞገሱ ይጨምራል፡፡ ወንድ ሚስት ሲያገባ ብቻውን ማድረግ ከችለው በላይ ማድረግ ይችላል፡፡ ስለዚህ ነው በአጋርነት ውስጥ የታመቀ ታላቅ ሃይል ስላለ መፅሃፍ ቅዱስ ሚስትን ያገኘ በረከትን አገኘ የሚለው፡፡
ሚስት ያገኘ በረከትን አገኘ፥ ከእግዚአብሔርም ሞገስን ይቀበላል። ምሳሌ 18፡22.
ቤተሰብ የሚከናወነው በሚስትና በባል አጋርነት ነው፡፡ የቤተሰብ ፍሬያማነት የሚለካው ሚስት እና ባል በተናጥል ባላቸው በረከት ሳይሆን በአጋርነታቸው በሚመጣው በረከት ነው፡፡ የቤተሰብ ስኬት የሚለካው ወንድ ወይም ሴት በተናጥል ባላቸው ስኬት ስኬት ሳይሆን በአጋርነት በሚያገኙት ስኬት ብቻ ነው፡፡ የትኛውም የተናጠል ስኬት እንደአጋርነት በቤተሰብ እንደሚገኘው ስኬት ይበልጥ የበዛ አይሆንም፡፡
ወንድ ሲፈጠር አብሮ የተፈጠረው ክህሎት አለው፡፡ ወንድ ቤተሰብን እንዲያገለግልበት አብሮት የተፈጠሩ ስጦታዎች አሉት፡፡ ወንድ የተጠራው ቤተሰቡን ለመጠበቅ በመከላከል ምሪትን ለመስጠት ብሎም አስቸጋሪ ነገርን ከፊት ሆኖ ለመጋፈጥ ችግሮችን ለመጠርመስ ነው፡፡ ባል የቤተሰቡ ደህንነት ለመጠበቅ ፣ ምሪትን ለመስጠትና ዋና የገቢ ምንጭ በመሆን የቤተሰቡን መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላት አገልጋይ ነው፡፡
ሴት እንዲሁ ስትወለድ የተወለደችው ለቤተሰብ ከሚጠቅም ልዩ ክህሎት ጋር ነው፡፡ ሴት በዋነኝነት ቤተሰቡ የምታገለግለው ቤተሰቡን በማስተዳደር ለቤተሰቡ እንክብካቤ ማድረግ ነው፡፡
ወንድ በዋነኝነት የቤተሰቡን ደህንነት የመጠበቅ ክህሎት ከእግዚአብሄር ተችሮታል፡፡ ወንድ ከእግዚአብሄር ስለተሰጠው የመሪነት ስጦታ ምክኒታይ የእግዚአብሄርን ፊት በመፈለግ ቤተሰቡን በትክክለኛው መንገድ የመምራት ታላቅ ሸክም ተጥሎበታል፡፡
ሴት ደግሞ እግዚአብሔር በውስጥዋ ከፈጠረው ክህሎት የተነሳ ለቤተሰብዋ እንክብካቤ ለማድረግ ቤተሰቡ ያለውን ነገር በጥበብ የማስተዳደር ታላቅ ሃላፊነት በእርስዋ ላይ ወድቆዋል፡፡
በቤተሰብ ሙሉን የእግዚአብሄርን መልክ የሚያንፀባርቁት ወንድና ሴት ናቸው፡፡ የወንድና የሴት አጋርነት እግዚአብሄር በቤተሰብ ውስጥ ያስቀመጠው ሙሉ ሃይል እንዲወጣና ለብዙዎች በረከት እንዲሆን ያስችለዋል፡፡
እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። ዘፍጥረት 1፡27
ሊተባበሩ እንጂ ሊወዳደሩ እንደማይችሉ ሁለት የተለያዩ ነገሮች ወንድ ከሴት ጋር ሊፎካከር በፍፁም አይችልም፡፡ አንዱ የሌላውን ጉድለት እንደሚሞላና የሌላውን ድካን እንዲሸፍን የተላከ አጋር የቤተሰብ አባል ለአንድ አላማ ሊሰሩ እንጂ ሊወዳደሩ እንደማይችሉ ሁለት የተለያዩ ነገሮች ወንድና ሴት ሊወዳደሩ አይችሉም፡፡
የከነዓን አባት ካምም የአባቱን ዕራቁትነት አየ፥ ወደ ውጭም ወጥቶ ለሁለቱ ወንድሞቹ ነገራቸው። ሴምና ያፌትም ሸማ ወስደው በጫንቃቸው ላይ አደረጉ፥ የኋሊትም ሄደው የአባታቸውን ዕራቁትነት አለበሱ፤ ፊታቸውም ወደ ኋላ ነበረ፥ የአባታቸውንም ዕራቁትነት አላዩም። ዘፍጥረት 9፡22-23
ወንድ ከሴት የተለየ ችሎታና ሃላፊነት አለበት፡፡ ሴትም ከወንድ የተለየ ሃላፊነትና ችሎታ ጋር ተፈጥራለች፡፡ ሁለቱም በቤተሰብ ያላቸውን ሃላፊነት ከተወጡ ቤተሰቡ እግዚአብሄር ወደዳየለት የክብር ደረጃ ይደርሳል፡፡ ሁለቱም ያላቸው ሃላፊነትና ችሎታ ክቡርና ከእግዚአብሄር የተሰጠ ነው፡፡ የሚያገለግሉበት መንገድ ይለያይ እንጂ ሁለቱም አገልጋዮች ናቸው፡፡ በሚያገለግሉበት የህይወት አቅጣጫ ስልጣኑም አላቸው፡፡
እያንዳንዱ እግዚአብሄር በሰጠው የሃላፊነት ቦታ የተከበረ ነው፡፡ ባልተሰጠው ሃላፊነት አንዱ ለሌላው ይገዛል፡፡ የቤተሰቡን አጠቃላይ መሪነት በተመለከተ ሁሉም የቤተሰቡ አባላት ለወንዱ ይገዛሉ፡፡ የቤተሰቡን ዝርዝር አስተዳደር በተመለከተ ሁሉም የቤተሰቡ አባላት ለሴትዋ ይገዛሉ፡፡
ለእያንዳንዳችሁ በክርስቶስ ፍርሃት የተገዛችሁ ሁኑ። ኤፌሶን 5፡21
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ህብረት #አጋርነት #አብሮማደግ #የጋራ #ሚስት #ባል #ቤተሰብ #ወንድ #ሴት #ዘር #መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ
No comments:
Post a Comment