ለእግዚአብሄር እንደሚገባ መመላለስ በሰው ጉልበት የሚቻል ነገር አይደለም፡፡ እንደ እግዚአብሄር ልጅ መመላለስ የእግዚአብሄር ሃይልና አሰራርን ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ ነው ከመመላለስ በፊት መቀመጥ ይቀድማል የሚባለው፡፡
በሰማያዊ ስፍራ በአብ ቀኝ በተቀመጥንበት ሃይልና ምሪት ለእግዚአብሄር እንደሚገባ መኖር እንችላለን፡፡ በሰማያዊ ስፍራ ባለንበት ስልጣን የምድር ህይወታችንን ሃላፊነት በስኬት እንወጣለን፡፡ በእግዚአብሄር ዘንድ በናለን ልዩ ስፍራ በምደር ላይ ነገሮችን ተቋቁመን እናልፋለን፡፡
በክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። ኤፌሶን 1፡3
በእግዚአብሄር ዘንድ ያለን ስፍራ በምድር ስፍራ እንዳንፈልግ ይረዳናል፡፡ በሰማያዊ ስፍራ ያለብ ስልጣን በሰይጣን ፊት እንዳንዋረድ ያስችለናል፡፡ በእግዚአብሄር ልብ ያለን ስፍራ ስንረዳ ከእግዚአብሄር ውጭ በምድር ምንም ነገር በልባች የመጀመሪያውን ስፍራ እንዳይዝ ያደርገናል፡ በእግዚአብሄ ዘንድ ያለን ከፍታ ስንረዳ በምድር ያለ ምንም ዝቅታ አያስደነግጠንም፡፡ በእግዚአብሄር እንደነገስን ስንረዳ ከጌታ ውጭ ምንም ነገር ንጉስ እንዳይሆንብን ያደርጋል፡፡ በሰማያዊ ስፍራ ያለን ከፍታ በምድር ራሳችንን እንድናዋርድ ያስታጥቀና፡፡ በሰማያዊ ያለን ስፍራ ለምድር ስፍራ እንዳንፎካከር ያግዘናል፡፡ በእግዚአብሄር ያለንን ክብር ስንረዳ የምድሩን ክብር እንድንቀው ያስችለናል፡፡
ኢየሱስ አብ ሁሉን በልጁ እንደ ሰጠው ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣ ወደ እግዚአብሔርም እንዲሄድ አውቆ፥ ከእራት ተነሣ ልብሱንም አኖረ፥ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፤ በኋላም በመታጠቢያው ውኃ ጨመረ፥ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ሊያጥብና በታጠቀበትም ማበሻ ጨርቅ ሊያብስ ጀመረ። ዮሃንስ 13፡3-4
ለእርሱ ለመኖራችን የሚያስፈልገውን ነገር ሳያዘጋጅ እግዚአብሄር አልጠራንም፡፡ ለእርሱ ለመኖርና ለእርሱ በሚገባ ለመመላለስ እግዚአብሄር የጠራን ለክርስትና ህይወት ሁሉ የሚያስፈልገውን ሁሉ ሰጥቶን ነው፡፡
የመለኮቱ ኃይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። 2ኛ ጴጥሮስ 1፡2-3
በሰማያዊ ስፍራ ሳያስቀምጠን በፊት እንደ ልጅ ለእርሱ እንድንመላለስ አልጠየቀንም፡፡
በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን። ኤፌሶን 2፡6-7
በክርስቶስ ያለንን ስፍራ ፣ ስልጣንና ክብር ካላወቅን ለጥሪያችን እንደሚገባ መኖር አንችልም፡፡ በክርስቶስ ያለንን አቅርቦት ካለተረዳን በአቅርቦቱ በድል መመላለስ አንችልም፡፡
ለምሳሌ መኪና የተሰራው ለመነዳት ነው፡፡ መኪና ለመገፋት አልተሰራም፡፡ መኪና የሚነዳውም ሰው ይሁን የሚገፋውም ሰው ሁለቱም መኪናውን አንድ ቦታ ቢያደርሱትም መኪና መንዳትና መግፋት ግን ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ በእግዚአብሄር ዘንድ ያለንን ስልጣን በተረዳን ቁጥር ክርስትና እንደ መኪና መንዳት እንጂ እንደ መኪና መግፋት አይሆንብንም፡፡
እግዚአብሄር በክርስቶስ ባዘጋጀው ጥቅምና መብት ሙሉ ለሙሉ ተጠቃሚ ለመሆን እግዚአብሄርን በማወቅ ማደግ አለብን፡፡ እግዚአብሄር በልቡ እንዳለው ለመመላለስ በቃሉ አማካኝነት ክርስቶስን ማጥናትና መማር አለብን፡፡ የእግዚአብሄር ቃል በሙላት ሊኖርብንና በክርስቶስ እውቀት ማደግ ይገባናል፡፡
በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። 2ኛ ጴጥሮስ 1፡3
እግዚአብሄርን ባወቅነው መጠን እንዴት ከእግዚአብሄር ጋር በሰላም እንደምንኖር እናውቃለን፡፡ እግዚአብሄርን ባወቅነው መጠን ሰላማችን እየበዛ ይሄዳል፡፡ እግዚአብሄርን በተረዳነው መጠን የእግዚአብሄር ፀጋ በህይወታችን በሙላት መፍሰስ ይጀምራል፡፡ እግዚአብሄርን ባወቅነው መጠን ሰውን እንዴት እንደምንይዝ እናውቃለን፡፡ እግዚአብሄርን ባወቅነው መጠን ነገሮችን እንዴት እንደምንዝ እናውቃለን፡፡ እግዚአብሄር በክርስቶስ የሰጠንን ቦታ ስንረዳ የእግዚአብሄርን ሃሳብ በሙላት ፈፅመን እናልፋለን፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#እረፍት #ቅድሚያ #መቀመጥ #ሰማያዊ #በክርስቶስ #በጌታ #እምነት #መደገፍ #ሰንበት #በመንፈሴ #በሃይል #በብርታት #ፀጥታ #መመለስ #ማረፍ #ፅድቁን #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ፀጥታ #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #መታመን #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ
No comments:
Post a Comment