እግዚአብሄርን የመራንን ነገሮች ስናደርግ አንዳንዴ
ሰዎች ላይረዱን ይችላሉ፡፡ የሚመለከታቸው ሰዎች ካልተረዱን ደግሞ በራሳችን ምንም ማድረግ አንችልም፡፡ አብረናቸው የእግዚአብሄርን
ስራ እንድንሰራ የተሰጡን ሰዎች ካልተረዱን ለእግዚአብሄር መልቀቅ አለብን፡፡ የራሳችንን ድርሻ ከተወጣን በኋላ ለእግዚአብሄር አሰራር
ደግሞ ጊዜና ስፍራ መስጠት አለብን፡፡ ለእግዚአብሄር አንድ እያንዳንዱ ሰው ነገር ለማድረግ ራሱ አጥብቆ መረዳት አለብት፡፡
ለእግዚአብሔርም ክብር እየሰጠ፥ የሰጠውንም ተስፋ ደግሞ ሊፈጽም እንዲችል አጥብቆ እየተረዳ፥ ሮሜ 4፡20
እግዚአብሄርም ሰዎች ያላወቁትንና ያልተረዱትን
ነገር እንዲያደርጉ አይጠብቅም፡፡ እኛን እግዚአብሄር ተናገረን ብለን ሰዎችን ማስገደድ አንችልም፡፡ እኛ ነፃ ፈቃድ እንዳለን ሁሉ
ሌሎች ሰዎችም አይ አይደለም ለማለት ፈቃድ እንዳላቸው ማወቅና መቀበል ይገባናል፡፡ ከእግዚአብሄር የሆነውን ለሚመለከታቸው ሰዎች
ከተናገርን በኋላ ራሳችን ለማስፈፀም መሞከር በእግዚአብሄር ሳይሆን በራስ መተማመን ነው፡፡
ድርሻችንን ከተወጣን በኋላ ማረፍና ለእኛ እንደተናገረን
እግዚአብሄር ራሱ እንዲናገራቸው ጊዜ መስጠት ወሳኝ ነው፡፡ እኛን እንደተናገረን ራሱ እግዚአብሄር እንዲናገራቸው እድሉን ካልሰጠን
ሰዎች የተናገርነው ነገር የእኛን የራስ ወዳድነት ፍላጎት አድርገው ሊረዱት ይችላሉ፡፡ ይዘን የመጣነው ሃሳብ የእኛ የግላችን ሃሳብ
እንዳልሆነና የሃሳቡ ዋናው ባለቤት እግዚአብሄር እንደሆነ ለማሳየት እኛ ዝም ማለት ይገባናል፡፡ እኛ ዝም ካላልንና ሰዎች የእግዚአብሄርን
ድምፅ አጥርተው ካልሰሙ የእግዚአብሄርና የእኛን ድምፅ ይቀላቀልባቸዋል፡፡ ስለአንድ ነገር የእግዚአብሄርን ድምፅ ለራሳቸው መስማት
የሚችሉት እኛ ዝም ስንልና ጊዜ ስንሰጥ ብቻ ነው፡፡
ተወዳጆች ሆይ፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፥ ለቍጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና። ሮሜ 12፡19
እግዚአብሄር ከግርግር ባሻገር ለራሳቸው የሚናገራቸው
ስንታገስና ጊዜ ስንሰጥ ነው፡፡ ሰዎች የራሳችንን ጥቅም እንደምናሳድንድ ካሰቡ ስሜታቸው ይረበሻል፡፡ በዚህም ሁኔታ ጌታን በትክክል
መስማት ይሳናቸዋል፡፡ እኛ ዝም በምንልበት ጊዜ ግን እግዚአብሄር ራሱ በዝምታ እንዲናገራቸው ምቹ ሁኔታን እንፈጥርላቸዋለን፡፡
ስለዚህ፥ እነሆ፥ አባብላታለሁ፥ ወደ ምድረ በዳም አመጣታለሁ፥ ለልብዋም እናገራለሁ። ሆሴዕ 2፡16
በአለም
ላይ በአማኞች ብዛት ታላቁን ቤተክርስትያን የመሩት መጋቢ ዲቪድ ዮንጊ ቾ በኮሪያ የኢኮኖሚ ውጥረት ጊዜ እግዚአብሄር 10 ሺህ ሰው
የሚይዝ ቤተክርትስትያን እንዲሰሩ እንደተናገራቸው ይመሰክራሉ፡፡ ስለዚያም እያፀለዩ እያሉ እግዚአብሄር ለሚስታቸው ቤት መስሪያ ያጠራቀሙትን
ገንዘብ የመጀመሪያው መዋጮ አድርገው እንዲሰጡት ይናገራቸዋል፡፡ በእጃቸው የነበረው ብቻኛው ገንዘብ የሚስታቸው ገንዘብ ነበር፡፡
በኮሪያ ባህል ባል ለሚስቱ ቤት ይገዛ ስለነበር እሳቸው ለሚስታቸው ቤት ለመግዛት ያጠራቀሙት የሚስታቸው ቤት መግዣ ገንዘብ ነበር፡፡
እሳቸው ለሚስታቸው እግዚአብሄር ገንዘቡን እንዲሰጡ እንደተናገራቸው ይነግሩዋታል፡፡ የሚስታቸው መለስ ግን ያንን ገንዘብ ለመስጠት በፍፁም እንዳታስብ የሚል ነበር፡፡
እግዚአብሄር ሆይ ያለችውን ሰምተሃል ብለው ፀልየው ይተዉታል፡፡
ሚስታቸው
ግን ልትትወው አልቻለችም፡፡ ሚስታቸው እንቅልፍ አጣች፡፡ እኔ ተኝቼ እነሳለሁ እርስዋ ግን ሌሊቱን ሙሉ ትገላበጣለች እንጂ እንቅልፍ
በአይኑዋ አልዞረም ይላሉ፡፡ በእንቅልፍ ማጣት አይንዋ እያበጠ ሄደች፡፡ በሰባተኛው ቀን ይላሉ ቾ ያንን ገንዘብ ውሰደው አለችኝ
ብለው ለእግዚአብሄር አሰራር ጊዜ በሰጡ ጊዜ እግዚአብሄር ከሚመለከተው ሰው ጋር ነገሮችን እንደጨረሰ ይመሰክራሉ፡፡
እግዚአብሄር
የተናገረንን ለሚመለከታቸው ሰዎች ካሳየን በኋላ መታገስ እና ጊዜ መስጠት እግዚአብሄር ደግሞ በራሱ መንገድ እንዲናገራቸው እድልን
ይሰጠዋል፡፡ ከጊዜ ወደጊዜ ለእግዚአብሄር አሰራር ጊዜ ካልሰጠን የእግዚአብሄርን ስራ ለመስራት ስንሮጥ እንደ ራስ ወዳድ ሰዎች ለጥቅማችን
የምንከራከር ይመስላል፡፡ ስለዚህ ነው ከቤተክርስትያን መሪነት መመዘኛዎች አንዱ አለመከራከርና አለመጨቃጨቅ የሆነው፡፡
የማይሰክር፥
የማይጨቃጨቅ ነገር ግን ገር የሆነ፥ የማይከራከር፥ ገንዘብን የማይወድ፥ 1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡3
ስለዚህ
ነው ሰው ካንተ ጋር ቦክስ ወይም ቡጢ ሊገጥምህ ሲፈልግ አንተ ከቦክሱ ሜዳ ውጣና ባንተ ፋንታ እግዚአብሄርን ወደ ቦክሱ ሜዳው አስገባው
የሚባለው፡፡ እግዚአብሄር በእኛ ፋንታ የሚዋጋው እኛ ከሰዎች ጋር ውጊያን ስናቆም ብቻ ነው፡፡ እራሳችንን የምናየውና ከተሳሳትን
የምንታረመው ለእገዚአብሄር አሰራር ጊዜ ስንሰጥ ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄርም በማሸነፋችን ክብሩን የሚወስደው እኛ ለእግዚአብሄር አሰራር
ጊዜና እድል ስንሰጥ ነው፡፡
እግዚአብሔር
ስለ እናንተ ይዋጋል፥ እናንተም ዝም ትላላችሁ አላቸው። ዘፀአት 14፡14
እናንተ በዚህ ሰልፍ የምትዋጉ አይደላችሁም፤ ይሁዳና ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ተሰለፉ፥ ዝም ብላችሁ ቁሙ፥ የሚሆነውንም የእግዚአብሔርን መድኃኒት እዩ፤ እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ነውና አትፍሩ፥ አትደንግጡም፥ ነገም ውጡባቸው። 2ኛ ዜና 20፡17
እግዚአብሄር
የመራንን ከተናገርን በኋላና እግዚአብሄር ያለንን ካደረግን በኋላ ካላረፍን በስተቀር የእኛ ስራ እንጂ የእግዚአብሄ ስራ አይሆንም
፣ የእኛ ሃይል እንጀ የእግዚአብሄር ሃይል አይሆንም እንዲሁም የእኛ ጥበብ እንጂ የእግዚአብሄር ጥበብን አይሆንም፡፡
ኢዮአስም
እርሱን የተቃወሙትን ሁሉ፦ ለበኣል ትምዋገቱለታላችሁን? ወይስ እርሱን ታድናላችሁን? የሚምዋገትለት ሁሉ እስከ ነገ ይሙት፤ እርሱ
አምላክ ከሆነ መሠዊያውን ካፈረሰው ጋር ለራሱ ይምዋገት አላቸው። መሣፍንት 6፡31
እኛ
ከእግዚአብሄር ጋር አብረን ሰራተኛ ነን እንጂ ከመጀመሪያ እስከመጨረሻ የእግዚአብሄርን ስራ የምንሰራ ብቸኛ ባለቤቶች እና ተሟጋቾች
አይደለንም፡፡ መስራት የምንችለውን ካደረግን በኋላ ለዋናው ባለቤት ጊዜውንና ስፍራውን እንለቃለን፡፡
ይህን
ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ
ፅሁፎች
https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ
መልእክቶች
https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ
#ጌታ #ስፍራ #እውቀት #ጥበብ #ቦክስ #ቡጢ #የማይጨቃጨቅ #ገር #የማይከራከር #ክርስትያን #አማርኛ
#ፍጥነት #ማስተዋል #መፅሃፍቅዱስ #ፈንታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አዲስፍጥረት #እድል
#ጊዜ
No comments:
Post a Comment