Popular Posts

Follow by Email

Friday, August 18, 2017

ደካሞች የሚመስሉ የአካል ብልቶች ይልቁን የሚያስፈልጉ ናቸው

ነገር ግን ደካሞች የሚመስሉ የአካል ብልቶች ይልቁን የሚያስፈልጉ ናቸው፤ ከአካልም ብልቶች ያልከበሩ ሆነው የሚመስሉን በሚበዛ ክብር እናለብሳቸዋለን፥ በምናፍርባቸውም ብልቶቻችን ክብር ይጨመርላቸዋል፤ ክብር ያላቸው ብልቶቻችን ግን ይህ አያስፈልጋቸውም። ነገር ግን ብልቶች እርስ በርሳቸው በትክክል ይተሳሰቡ ዘንድ እንጂ በአካል መለያየት እንዳይሆን፥ ለጎደለው ብልት የሚበልጥ ክብር እየሰጠ እግዚአብሔር አካልን አገጣጠመው። አንድም ብልት ቢሣቀይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሣቀያሉ፤ አንድ ብልትም ቢከበር ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል። እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ። 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡22-27
የሰው አዋቂነት የሚለካው ጠንካራውን በመያዝ ደካማውን በመጣል አይደለም፡፡ ደካሞች የሚመስሉ የአካል ብልቶች ይልቁን እንደሚያስፈልጉ ተፈጥሮ እንኳን ያስተምረናል፡፡  
ደካሞች የሚመስሉ የአካል ብልቶች ይልቁን የሚያስፈልጉ ናቸው፡፡
በሰውነታችን የማያስፈልግ የሚመስለን ብልት ካለ ስለጥቅሙ እውቀት ይጎድላል ማለት እንጂ አያስፈልግም ማለት አይደለም፡፡ በሰውነት ክፍላችን እንኳን ስንመለከት እጅግ በጣም አስፈላጊ የአካል ብልቶች ደካማ ብልቶች ናቸው፡፡   
ደካማ የሚመስሉ ብልቶች ይበልጥ እንደሚያስፈልጉ መረዳት አዋቂነት ነው፡፡ ደካማን ከላይ ከላይ የየቶ መናቅና መጣል ሞኝነት ነው፡፡ ሰው በአንድ ነገር ደካማ ነው ማለት ብርታቱ በሌላ ነው ማለት ብቻ እንጂ በአጠቃላይ ደካማ ነው ማለት በፍፁም አይደለም፡፡ የአንድ ሰው በአንድ የህይወት ክፍል ደካማነት የሚያመለክተን ያላየነው ጠንካራ የህይወት ክፍል እንዳለ ነው፡፡ በዚህ ጠንካራ አይደለም ማለት በዚያ ጠንካራ ነው ማለት ነው፡፡ በሁሉም ጠንካራ ሰው እንደሌለ ሁሉ በሁሉም ደካማ ሰው ደግሞ የለም፡፡ ከሰው ድካም ባሻገር ጥንካሬውን ማየት ጥበብ ነው፡፡ የሰውን ድካም ታግሶና ሸፍኖ በጥንካሬው መጠቀም ፍሬያማ ያደርጋል፡፡ ድካምን ብቻ የሚያይ ሰው ማንም ሳይቀረው ሁሉንም አውጥቶ ይጥላል፡፡ ከድካም ባሻገር ጥንካሬን ማየት የሚችል ሰው ደግሞ ድካምን ታግሶ በእያንዳንዱ ጥንካሬ ይጠቀማል፡፡  
ለራሱ ጥቅም ለመጨመር ሲል ድሀን የሚጐዳ፥ ለባለጠጋም የሚሰጥ፥ እርሱ ወደ ድህነት ይወድቃል። ምሳሌ 22፡16
ከአካልም ብልቶች ያልከበሩ ሆነው የሚመስሉን በሚበዛ ክብር እናለብሳቸዋለን፡፡
ያልከበሩ የሚመስሉን የአካል ብልቶች ላይ ሰፊ ጊዜና ጉልበት እናፈስባቸዋለን፡፡ ያልከበሩ የሚመስሉን ብልቶችን በከበረ ነገር እንሸፍናቸዋለን፡፡ የሰው ጥበብ የሚለካው የከበረውን በማሳየት ብቻ ሳይሆን ያልከበረውን በመሸፈንም ነው፡፡ ያልከበረውን የማይሸፍን ሰው የከበረውን እንደሚደብቅ ሰው መረዳቱ ሙሉ አይደለም፡፡ ያልከበሩት ደካማ ብልቶች ይበልጥ ክብር ይለብሳሉ፡፡ ያልከበሩ ብልቶች ይበልጥ ትጋትን እናሳይባቸዋለን፡፡ ፀጋ እንኳን እጅግ የሚበዛው ይበልጥ በሃጢያት ለሚፈተን ለደካማው ሰው መሆኑን መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡ በቀላሉ በሃጢያት ለሚወድቅ ለደካማው ሰው እንጂ ለጠንካራው ሰው ፀጋ ወይም የሚያስችል ሃይል አይበዛም፡፡
ነገር ግን ስጦታው እንደ በደሉ መጠን እንደዚያው አይደለም፤ በአንድ ሰው በደል ብዙዎቹ ሞተዋልና፥ ነገር ግን የእግዚአብሔር ጸጋና በአንድ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የሆነው ስጦታ ከዚያ ይልቅ ለብዙዎች በዛ። በደልም እንዲበዛ ሕግ ጭምር ገባ፤ ዳሩ ግን ኃጢአት በበዛበት፥ ኃጢአት በሞት እንደ ነገሠ፥ እንዲሁ ደግሞ ጸጋ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተነሣ በጽድቅ ምክንያት ለዘላለም ሕይወት ይነግሥ ዘንድ፥ ጸጋ ከመጠን ይልቅ በለጠ። ሮሜ 5፡15፣20-21
በምናፍርባቸውም ብልቶቻችን ክብር ይጨመርላቸዋል፡፡
ጠንካራን እንደሰትበታለን እንጂ እንደ ደካማው ያን ያህል ስራ አይጠይቅም፡፡ የእኛ ታላቅ ኢንቨስትመንት ተጠቃሚ የሚሆኑት ደካሞች ናቸው፡፡ በእኛ ውስጥ ያለው ጥንካሬ ለደካሞች ድካም መሸፈኛነት የታቀደ ነው፡፡ በእኛ ውስጥ ያለው ጥንካሬ የደካሞችን ድካም የመሸፈን ታላቅ አላማ አለው፡፡ በእኛ ውስጥ ትርፍ የሆነና ለምንም የማይጠቅም ስጦታ አልተቀመጠም፡፡ በእኛ ውስጥ ብርታት ካለ በሌላው ውስጥ የምንሸፍነው ድካም አለ ማለት ነው፡፡ በዚህ ወር ትርፍ ገንዘብ ከመጣ በሌላው ወር በትርፉ የሚሞላ ጉድለት አለ ማለት ነው፡፡ ገንዘብ ተረፍ ብሎ ከመጣ በሌላ ጎን ፍላጎት አለ ማለት ነው፡፡ ገንዘብ ደግሞ ተረፍ አድርጎ ካልመጣ እግዚአብሄር ይመስገን ፍላጎት የለም ማለት ነው፡፡
የእነርሱ ትርፍ ደግሞ የእናንተን ጉድለት እንዲሞላ በአሁኑ ጊዜ የእናንተ ትርፍ የእነርሱን ጉድለት ይሙላ፤ በትክክል እንዲሆን፥ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፦ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፦ ብዙ ያከማቸ አላተረፈም፥ ጥቂትም ያከማቸ አላጎደለም። 2ኛ ቆሮንቶስ 8፡14-15
ክብር ያላቸው ብልቶቻችን ግን ይህ አያስፈልጋቸውም፡፡
ደካሞችን የሚንቅ ጠንካሮችን የሚያከብር ሰው መረዳት የጎደለው ሰው ነው፡፡ ደካሞች የሚበልጥ ክብር ያስፈልጋቸዋል፡፡ የሰው ክብሩ ደካሞችን በማክበር ነው፡፡ ሰውን በእውነት እንደወደድነው የሚታየው ሲደክም በምናደርገው እንክብካቤ ነው፡፡ ሰውን ማክበራችን የሚፈተነው ሲዋረድ በማክበራችን ነው፡፡ ሰውን በእውነት መውደዳችን የሚፈተነው እንዳንወደው የሚፈትን ነገር ሲገጥመን ነው፡፡ እውነተኛ ፍቅር የሚፈተነው ሰውን ለመውደድ ምክኒያት ስናጣ ነው፡፡ ሰው እርዳታ የሚያስፈልገው ሲደክም ነው፡፡ ወዳጅ የሚወለደው ለመከራ ቀን ነው፡፡ ወዳጅ በእጅጉ የሚያስፈልገው በመከራ ቀን ነው እንጂ ማንም ሰው አብሮ ሊደሰት ፈቃደኛ በሚሆንበርት በሰላም ቀን አይደለም፡፡   
ወዳጅ በዘመኑ ሁሉ ይወድዳል፤ ወንድምም ለመከራ ይወለዳል። ምሳሌ 17፡17
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ልዩነት #አካል #ብልት #ህብረት #አንድነት #ክብር #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #አንድነት #ፀጋ #ብልት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment