ያልታወቁ
ስንባል የታወቅን ነን፤ የምንሞት ስንመስል እነሆ ሕያዋን ነን፤ የተቀጣን ስንሆን አንገደልም፤ ኀዘንተኞች ስንሆን ዘወትር ደስ ይለናል፤
ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለ ጠጎች እናደርጋለን፤ አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው። 2ኛ ቆሮንቶስ 6፡9-10
በአብ
ቀኝ በክርስቶስ መቀመጣችን ሁሉንም የህይወት ጥያቄያችንን ይመልሳል፡፡ በእግዚአብሄር ፊት ባለን የክብር ብዛት ውርደትን እንታገሳለን፡፡
በእግዚአብሄር ዘንድ ባለን ስፍራ ሰዎች የሚጋደሉለትን የምድርን ነገር ሃብት ፣ ዝና እና ስልጣን እንንቃለን፡፡
በሚመጡ
ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣን
በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን። ኤፌሶን 2፡6-7
እንግዲህ
ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፥ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ እሹ፤ በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን
አይደለም። ቆላስይስ 3፡1-2
1.
ያልታወቁ ስንባል የታወቅን ነን፡፡
በምድር ላይ ታዋቂ ላንሆን አንችላለን፡፡ በእግዚአብሄር ዘንድ ግን ታዋቂዎች ነን፡፡ እግዚአብሄር ልኮናል ፣ እግዚአብሄር
ያውቀናል ፣ እግዚአብሄር ተደስቶብናል፡፡ ሰው እንደሚያይ የማያየው እግዚአብሄር ያውቀናል፡፡ ሰው የናቀውን የሚያከብር እግዚአብሄር
ዋጋ ሰጥቶናል፡፡ ጉዳዬ ልንለው የሚገባው የእግዚአብሄርን እይታ ብቻ ነው፡፡ በሰው ዘንድ ለመታወቅ ጉልበታችን አንጨርስም፡፡ ለጠራን
ለመሮጥ እንጂ ለታዋቂነት ለመፍጨርጨር ትርፍ ጊዜ የለንም፡፡ እግዚአብሄር በህይወታችን እንድንፈፅመው የጠራንን ጥሪ በዝምታ እንፈፅማለን፡፡ ሰው እንደ እግዚአብሄር አያውቀንም የሰው ማክበርን ማዋረድም አያስደንቀንም፡፡
በሰው ዘንድ ያልታወቅን ስንባል የታወቅን ነን፡፡ ሰውንም ለማስደሰት በምድር ላይ የለንም፡፡
ከእግዚአብሔር ክብር ይልቅ የሰውን ክብር ወደዋልና። ዮሃንስ 12፡43
ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን አሁን እሺ አሰኛለሁን? ወይም ሰውን ደስ ላሰኝ እፈልጋለሁን? አሁን ሰውን ደስ ባሰኝ የክርስቶስ
ባሪያ ባልሆንሁም። ገላትያ 1፡10
2.
የምንሞት ስንመስል እነሆ ሕያዋን ነን፡፡
የምንሰራው ምድራዊ እና ስጋዊ ነገር አይደለም፡፡ የምንኖረው ፣ የምንወጣውና የምንገባው በራሳችን ጉልበት አይደለም፡፡
የእግዚአብሄር እርዳታ በሃይል ከእኛ ጋር አለ፡፡ እንድንኖርለትና እንድናገለግለው የጠራን በሃይል ከእኛ ጋር ይሰራል፡፡ ምንም በጎ
ነገር ቢገኝብን ከእርሱ ነው፡፡ በራሳችን ስንደክም እንኳን የእርሱ ሃይል ተሸክሞ ያሻግረናል፡፡ ስንደክም የእግዚአብሄ ፀጋ ይበዛልናል፡፡
ስንዋረድ እግዚአብሄር ያከብረናል፡፡ ስንደክም ያን ጊዜ ሃይለኛ ነን፡፡ የውጭ ሰውነታችን ሲጠፋ የውስጡ ሰውነታችን እለት እለት
ይታደሳል፡፡ የምንሞት ስንመስል ህያዋን እየሆንን ነው፡፡
ስለዚህም አንታክትም፥ ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል። 2ኛ ቆሮንቶስ
4፡16
በተዋረድን ቁጥር እየጠለቅን ስር እየሰደድንና መሰረታችን እየሰፋ ነው፡፡ እምነታችን ሲፈተን ወርቅ በእሳት እንደሚፈተንና
ይበልጥ እንደሚጠራ እምነታችን እየጠራና እየከበረ ነው፡፡
በዚህም እጅግ ደስ ይላችኋል፥ ነገር ግን በእሳት ምንም ቢፈተን ከሚጠፋው ወርቅ ይልቅ አብልጦ የሚከብር የተፈተነ እምነታችሁ፥
ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ፥ ለምስጋናና ለክብር ለውዳሴም ይገኝ ዘንድ አሁን ለጥቂት ጊዜ ቢያስፈልግ በልዩ ልዩ ፈተና አዝናችኋል።
1ኛ ጴጥሮስ 1፡6-7
3.
የተቀጣን ስንሆን አንገደልም፡፡
ሰዎች የተለያየ ነገር ቢያደርጉን አያስቆሙንም፡፡ ምናችንንም ቢወስዱብን ራእያችችንን ፣ እምነታችንንና አገልግሎታችንን
ሊወስዱብን አይችሉም፡፡ ሰዎች ሊያጠፉን ቢፈልጉ የእግዚአብሄር እጅ ከእኛ ጋር ስላል በከንቱ ይደክማሉ፡፡ በእግዚአብሄር ምህረት
ስለምንኖር የሰዎችም ይሁን የሰይጣን ቁጣ በህይወታችን ላይ የሚያመጣው ልዩነት የለም፡፡
አሁንም እላችኋለሁ፦ ከእነዚህ ሰዎች ተለዩ ተዉአቸውም፤ ይህ አሳብ ወይም ይህ ሥራ ከሰው እንደ ሆነ ይጠፋልና፤ ከእግዚአብሔር
እንደ ሆነ ግን ታጠፉአቸው ዘንድ አይቻላችሁም፥ በእርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ። ሐዋርያት 5፡38-39
ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። በዚህ ሁሉ ግን በወደደን
በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ሮሜ 9፡36-37
4.
ኀዘንተኞች ስንሆን ዘወትር ደስ ይለናል፡፡
በአለም በሚሆነው ነገር እናዝናለን፡፡ ሰዎች ለአለማዊነት ህይወታቸውን ሲሰጡና ለአለም ነገር ሲሮጡ ስናይ ፃድቅ ነፍሳችን
ትጨነቃለች፡፡ በጌታ ግን ደስ ይለናል፡፡ በነገሮች ልናዝን እንችላለን በጌታ ግን ሁልጊዜ ደስ ይለናል፡፡ ሰላማችንና ደስታችን አለም
እንደሚሰጠው በሁኔታውች የሚለዋወጥ አይደለም፡፡ በመከራ ብናልፍም በጌታ ግን ደስ ይለናል፡፡ በአለም ያለውን መከራ የምንፈጋፈጠው
በደስታ ነው፡፡ በአለም ያለው የሚያሳዝን ነገር ሁሉ ተሰብስቦ በልባችን ያለውን ደስታ ሊያጠፋው አቅም የለውም፡፡ በልባችን ያለው
ደስታ ከአለም ሃዘን ሁሉ ይበልጣል፡፡
ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፥ ደስ ይበላችሁ። ፊልጵስዩስ 4፡4
5.
ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለ ጠጎች እናደርጋለን፡፡
ራእያችን ሰዎችን ማገልገል እንጂ ለራሳችን መጠቀም አይደለም፡፡ ራእያችን ሰዎችን ማንሳት እንጂ ራሳችን መነሳት አይደለም፡፡
ራእያችን ሰዎችን ማገልገል እንጂ በሰዎች መገልገል አይደለም፡፡ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት እጅግ ከመባረካችን የተነሳ ለምንበላውና
ለምንጠጣው አንጨነቅም፡፡ የሚያሳስበን የሰዎች መባረክ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ቀኝ ከመቀመጣችን የተነሳ የዘወትር ሸክማችን ሰዎችን
ባለጠጋ ማድረግ ነው፡፡
የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር፥ ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው። 2ኛ ቆሮንቶስ 11፡28
የሚያረካን ሰዎች ሲለወጡ ማየት ነው፡፡ የምንረካው ሰዎች ካሉበት ነገር ሲወጡ ነው፡፡ የምንረካው ሰዎች ከከበባቸው ነገር
አልፈው ሲሻገሩ ነው፡፡ የገንዘብ ሃብት ባይኖረንም የሰው ሃብታሞች ነን፡፡ ተቀማጭ ገንዘብ ባይኖረንም በገንዘባችን ያፈራናቸው በሰማይ
የሚቀበሉን ሰዎች አሉ፡፡
እኔም እላችኋለሁ፥ የዓመፃ ገንዘብ ሲያልቅ በዘላለም ቤቶች እንዲቀበሉአችሁ፥ በእርሱ ወዳጆችን ለራሳችሁ አድርጉ። ሉቃስ
16፡9
የሰው መንፈሳዊነት እና ስኬት ባገኘው ገንዘብ የሚሰራው ስራ እንጂ ባጠራቀመው በምድራዊ ሃብቱ አይለካም፡፡ በምድር ቤተመንግስት
ላናስገነባ አንችላለን በህይወታችን ዘመን ሁሉ የእግዚአብሄርን ቤተክርስትያን በገንዘባችን እንደግፋለን፡፡ የብዙ ገንዘብ ባለቤቶች
ባንሆንም ባለን ገንዘብ የመልካም ነገር ባለጠጎች ነን፡፡
ለሚመጣው ዘመን ለራሳቸው መልካም መሠረት የሚሆንላቸውን መዝገብ እየሰበሰቡ፥ መልካምን እንዲያደርጉ በበጎም ሥራ ባለ
ጠጎች እንዲሆኑ፥ ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ እንዲሆኑ ምከራቸው። 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡18-19
የስራችን የምስክር ደብዳቤ በብእርና ቀለም የተፃፈ ሳይሆን በእኛ አማካኝነት የእግዚአብሄር ቃል በልባቸው የተፃፈ ሰዎች
ናቸው፡፡
እንደ ገና ራሳችንን ልናመሰግን እንጀምራለንን? ወይስ እንደ ሌሎች የማመስገኛ መልእክት ወደ እናንተ ወይስ ከእናንተ
ያስፈልገን ይሆንን? ሰዎች ሁሉ የሚያውቁትና የሚያነቡት በልባችን የተጻፈ መልእክታችን እናንተ ናችሁ። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ 3፡1-2
6.
አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው፡፡
በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ ተባርከናል፡፡ ያለን ትልቁ ሃብት የእግዚአብሄር አቅርቦት ነው፡፡ ያለን ትልቁ
ሃብት በእኛ ስም የተከፈተልን መንፈሳዊ ሂሳብ ወይም አካውንት ነው፡፡ እጃችን ባዶ ቢሆንም ከባለጠጋው አባታችን በእምነት እንዴት
እንደምንቀብል የምናውቅ የእምነት ባለጠጎች ነን፡፡ ኪሳችን ባዶ ቢሆንም የሚያስፈልገንን ነገር በሚያስፈልገን ጊዜ የማያሳጣን እግዚአብሄር
እረኛችን ነው፡፡ የሚታይ ሃብት ባይኖረንም የሚያስፈልገንን ሁሉ የምናገኝበት የማይታይ ሃብት አለን፡፡ ምድራዊ ሃብት ባይኖረንም
እግዚአብሄርን የምናስደስትበትና ፈቃዱን በምድር ላይ የምንፈፅምበር እምነት አለን፡፡
በስሌታችሁ የሚበዛውን ፍሬ እንጂ ስጦታውን ፈላጊ አይደለሁም። ፊልጵስዩስ 4፡17
ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን
ዘንድ ያስፈልገዋልና። ዕብራውያን 11፡6
ክርስቶስን የሰጠን እግዚአብሄር አብሮ ሁሉንም ሰጥቶናል፡፡ የሚጎድለን እንዳይኖር አድርጎ በሚያስፈልገን ነገር ሁሉ ባርኮናል፡፡
ስለዚህም ማንም በሰው አይመካ። ነገር ሁሉ የእናንተ ነውና፤ ጳውሎስ ቢሆን አጵሎስም ቢሆን ኬፋም ቢሆን ዓለምም ቢሆን
ሕይወትም ቢሆን ሞትም ቢሆን ያለውም ቢሆን የሚመጣውም ቢሆን፥ ሁሉ የእናንተ ነው፥ እናንተም የክርስቶስ ናችሁ ክርስቶስም የእግዚአብሔር
ነው። 1ኛ ቆሮንቶስ 3፡21-23
ያልታወቁ
ስንባል የታወቅን ነን፤ የምንሞት ስንመስል እነሆ ሕያዋን ነን፤ የተቀጣን ስንሆን አንገደልም፤ ኀዘንተኞች ስንሆን ዘወትር ደስ ይለናል፤
ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለ ጠጎች እናደርጋለን፤ አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው። 2ኛ ቆሮንቶስ 6፡9-10
ለተጨማሪ
ፅሁፎች
https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ
መልእክቶች
https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ
#ጌታ #ያልታወቁ #የታወቅን
#የምንሞት #ሕያዋን #የተቀጣን #አንገደልም #ኀዘንተኞች #ደስ
#ድሆች #ባለጠጎች #የሌለን #ሁሉየእኛነው #ጭንቀት #የባለጠግነትማታለል
#የኑሮሃሳብ #የእለትእንጀራ #የባለግነትምቾት #ዘር #መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ
No comments:
Post a Comment