Popular Posts

Sunday, June 25, 2017

የእውነተኛ ብልፅግና ገፅታዎች

ብልፅግና ክንውም ነው፡፡ ሰው ብልቡ ያለውን ነገር ለመፈፀም መቻል ብልፅግና ነው፡፡ ሰው ማድረግ የሚፈልገውን ነገር ጀምሮ ወደፍፃሜ ማምጣት ብልፅግና ነው፡፡
አንዳንድ ሰው ገንዘብ ብቻ ካገኘ ብልፅግና ይመስለዋል፡፡ ክንውን ከገንዘብ በላይ ነው፡፡ ክንውን የሚጠይቃቸው ገንዘብ ሊያደርገው የማይችል ብዙ ነገሮች አሉ፡፡
ክንውን የሚያስፈልገንን ገንዘብ በሚያስፈልገን ጊዜ ማግኘትን ያጠቃልላል፡፡ ብልፅግና የሚገለጥባቸው ሰባት መንገዶች
1.      ብልፅግና ነገሮችን የማስተዳደር ችሎታ ማግኘት ነው፡፡  
ሰው ሁሉም ነገር ኖሮት እንዴት እንደሚያስተዳድረው ጥበቡ ከሌለው ክንውን ይጎድለዋል፡፡ ሰው የሚያስፈልገውን ገንዘብ ወይም ቁሳቁስ ነገር አግኝቶ ያገኘውን ነገር ለታሰበለት አላማ ማዋል ካልቻለ ክንውን የለም፡፡

2.     ብልፅግና ብክነትን መቀነስ ነው፡፡
ክንውን ብክነትን መቀነስ ነው፡፡ ሰው ያገኘውን ነገር የተወሰነውን እጅ ቢያባክንና የቀረውን እጁን ቢጠቀምበት ልዩነት ያመጣው የብክነቱ መብዛትና ማነሱ እንጂ ያገኘው ገንዘብ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ብክንውን ሲባርክ የብክነትን ቀዳዳውን እንድትረዳና እንድትቀንስ ያደርግሃል፡፡ እግዚአብሄር ሲባርክ ክብደት መስጠት ላለብህ ነገር ቅድሚያ እንድትሰጥ መረዳት በመስጠት ክንውንን ይሰጥሃል፡፡
ጥበብን የወደደ ሰው አባቱን ደስ ያሰኛል፤ ጋለሞቶችን የሚከተል ግን ሀብቱን ያጠፋል። ምሳሌ 29፡3
የከበረ መዝገብና ዘይት በጠቢብ ሰው ቤት ይኖራል፤ አእምሮ የሌለው ሰው ግን ይውጠዋል። ምሳሌ 21፡20
3.     ብልፅግና ከትክክለኛ ሰው ጋር መገናኘት ነው፡፡
በልብህ ላለው ስራ የሚያስፈክግህን ሰው ማግኘት ክንውን ነው፡፡ ሁሉም ነገር ኖሮህ እንደራሱ አድርጎ የሚሰራልህ ትክክለኛውን ሰው ካላገኘህ ልትከናወን አትችልም፡፡ በአለም ላይ ይልቁ ሃብት ሰው ነው፡፡ እግዚአብሄር በታማኝ ሰው ይባርካል፡፡ እግዚአብሄር ሲባርክህ የሚያስፈልግህ ችሎታ ካለው ቁልፍ ሰው ጋር ያገናኝሃል፡፡
እንደ እርሱ ያለ፥ ስለ ኑሮአችሁ በቅንነት የሚጨነቅ፥ ማንም የለኝምና፤ ፊልጵስዩስ 2፡20
4.     ብልፅግና የምትበላውና የምትዘራውን መለየት ነው፡፡
የምትዘራውን ከበላህ ክንውን የለም፡፡ ክንውን የምትበላውን ብቻ እንድትበላና ሌላውን ደግሞ እንድትዘራውና ብዙ እንድታጭድ ያስተምርሃል፡፡ ብልፅግና ለወደፊት ማፍሰስ ያለብህን መዋእለ ንዋይ ወይም ኢንቨስት ማድረግ ያለብህን መረዳቱን ይሰጥሃል፡፡
ለዘሪ ዘርን ለመብላትም እንጀራን በብዙ የሚሰጥ እርሱም የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል ያበረክትላችሁማል፥ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያሳድጋል፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 9፡10
የከበረ መዝገብና ዘይት በጠቢብ ሰው ቤት ይኖራል፤ አእምሮ የሌለው ሰው ግን ይውጠዋል። ምሳሌ 21፡20
5.     ብልፅግና መሰረታዊ ፍላጎትና ቅንጦት የመለየት ችሎታ ነው፡፡
የክርስትያን የመጨረሻ ክንውን መሰረታዊ ፍላጎቱን አማልቶ ጌታን መከተል ነው፡፡ እግዚአብሄር መሰረታዊ ፍላጎታችንን ለማሟላት ቃል ገብቷል፡፡ እግዚአብሄር የምንፈልገውን ሁሉ አያሟላም፡፡ ስለዚህ እግፍዚአብሄር የሰጠንን ሃብት በመሰረታዊ ፍላጎት ላይ ብቻ የማዋል ጥበብ ብልፅግና ነው፡፡ ሰው እግዚአብሄር የሰጠውን ሃብት በቅንጦት ላይ አባክኖት ሊከናወን አይችልም፡፡  
ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፥ አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል። 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡6-8
6.     ብልፅግና እግዚአብሄር የሰጠህን ሰው በሚገባ የመያዝ ችሎታ ነው፡፡
እግዚአብሄር ለሰው የሚሰጠው ታላቁ ሃብት ሰው ነው፡፡ ሰው ብቻውን ያን ያህል ለውጥ ሊያመጣ አይችልም፡፡ ለሰው ሰው ያስፈልገዋል፡፡ ብልፅግና እግዚአብሄር ያመጣልንን እድል የመጠቀም ችሎታ ነው፡፡ ሰውን እንደአቅሙ እንደ ደረጃው እንዴት ማክበርና መያዝ እንዳለበት ካላወቀ ክንውን ከየትም አይመጣም፡፡
ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ፥ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር ወዲያው ሄደ። ማቴዎስ 25፡15
7.     ብልፅግና በህይወት መደሰት መቻል ነው፡፡
ህይወትን ሃላፊነት ብቻ አይደለም፡፡ ህይወት እንድንደሰትበት የተሰጠን ስጦታ ነው፡፡ ሰው ባለበት ደረጃ በደረሰበት ደረጃ ደስ መሰኘት ከቻለ ያ ክንውን ብልፅግና ነው፡፡ ሰው ደስ የመሰኘት ቀጠሮውን "ይህን ሳገኝ እንዲህ ስሆን" እያለ የሚያስተላልፈው ከሆነ ክንውን አይደለም፡፡ ሰው ዛሬ ባለበት ደረጃ ባለበት ሁኔታ በህይወቱ ደስ መሰኘት ካልቻለ የተከናወነ ሰው አይደለም፡፡
እነሆ፥ እኔ ያየሁት መልካምና የተዋበ ነገር ሰው እግዚአብሔር በሰጠው በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ፥ ከፀሐይ በታችም በሚደክምበት ድካም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ ነው፤ ይህ እድል ፈንታው ነውና። እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ ባለጠግነትንና ሀብትን መስጠቱ፥ ከእርስዋም ይበላና እድል ፈንታውን ይወስድ ዘንድ በድካሙም ደስ ይለው ዘንድ ማሠልጠኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። መክብብ 5፡18-19
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ብልፅግና #የብልፅግናወንጌል #መፀለይ #ሞገስ #በረከት #ስኬት #እረኛእግዚአብሄር #ስምረት #መሰረታዊፍላጎት #ሁሉየእናንተነውና #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #የተትረፈረፈህይወት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #መርካት #ደስታ #የልብስፋት #ማስተዳደር #እረፍት

No comments:

Post a Comment