Popular Posts

Saturday, June 17, 2017

ስድስቱ ውጤታማ የፀሎት አይነቶች

የተለያዪ አይነት የፀሎት አይነቶች እንዳሉ መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምረናል፡፡ በፀሎት ህይወታችን ፍሬያማ ለመሆን እነዚህን የተለያዩ የፀሎት አይነቶችና መቼና በምን ሁኔታ ውስጥ እንደምንፀልያቸው መረዳት ይኖርብናል፡፡
እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር፥ ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ። 1 ጢሞቴዎስ 21-2
ስለዚህ ምን አይነት ፀሎትና እንዴት እንደምንፀልይ ስለማናውቅ መንፈስ ቅዱስ ሊመራን ይገባል፡፡ በፀሎት ፍሬያማ ለመሆን በመንፈስ ቅዱስ ለይ መደገፍ በጣም ወሳኝ ነው፡፡
እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፤ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፤ ሮሜ 8፡26
ልመና
ልመና በእግዚአብሄር ዘንድ የሚያስፈልገንን ነገር ከእግዚአብሄር ቃል ተረድተን ፈቃዱን አውቀን የምንጠይቅበት የፀሎት አይነት ነው፡፡ ይህ አይነቱን የፀሎት አይነት ለየት የሚያደርገው በእምነት ከፀለይን በኋላ ደግመን ደጋግምን የምንፀልይበት አይደለም፡፡ አንዴ ልመናችንን ካስታወቅን በኋላ የሚጠበቅንብን ማመስገን ብቻ ነው፡፡
በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል። የምንለምነውንም ሁሉ እንዲሰማልን ብናውቅ ከእርሱ የለመነውን ልመና እንደ ተቀበልን እናውቃለን። 1ኛ ዮሐንስ 5፡14-15
ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፥ ይሆንላችሁማል። ማርቆስ 11፡24
የምስጋና ፀሎት
ይህ እግዚአብሄር በህይወታችን ስላደረገው ነገር እውቅና የምንስጥበትና እግዚአብሄርን የምናመሰግንበት የፀሎት አይነት ነው፡፡
ስለ እናንተ እያመሰገንሁ ስጸልይ . . . ኤፌሶን 1፡16
የውዳሴ ፀሎት
ይህ የፀሎት አይነት እግዚአብሄር ስላደረገልን ነገር ሳይሆን እግዚአብሄር ራሱ ስለሆነው ነገር ስለፍቅሩ ፣ ስለዘላለማዊነቱ ፣ ስለሃያልነቱና ስለምህረቱ የምናወድስበትና የምናመልክበት የፀሎት አይነት ነው፡፡
እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ መንፈስ ቅዱስ፦ በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ አለ። ሐዋርያት 13፡2
ምልጃ
ምልጃ ደግሞ ለራሳችንም ይሁን ለሌሎች ሰዎች የምንፀልየው ፀሎት ነው፡፡ ራሳችንን በሌሎች ቦታ አድርገን የሚያልፉበት ሁኔታ እየተሰማን ፣ ህመማቸውን እየታመምን ለእነርሱ የምንቃትተው መቃተት ምልጃ ይባላል፡፡ ምልጃ ደግሞ ደጋግሞ የሚደረግ የፀሎት አይነት እንጂ አንዴ ፀልየን ብቻ የምናመሰግንበት አይደለም፡፡ 
ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ጕበኞችን በቅጥርሽ ላይ አቁሜአለሁ፤ ቀንና ሌሊት ከቶ ዝም አይሉም፤ እናንተ እግዚአብሔርን የምታሳስቡ፥ ኢየሩሳሌምን እስኪያጸና በምድርም ላይ ምስጋና እስኪያደርጋት ድረስ አትረፉ ለእርሱም ዕረፍት አትስጡ። ኢሳይያስ 62፡6-7
 . . . ስለ እናንተ ማሳሰብን አልተውም፤ ኤፌሶን 1፡16
የተቃውሞ ፀሎት
ይህ የፀሎት አይነት ኢየሱስ በመስቀል ላይ ድል የነሳቸውን አለቆችና ስልጣናትን ከህይወታችን የምንቃወምበት የፀሎት አይነት ነው፡፡ ይህን ጸሎት ስንፀልይ እግዚአብሄር የመራንን የመንፈስ አይነት በመጥራት በልጅነት ስልጣናችን መቃወምና ማዘዝ ይገባናል፡፡  
መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ። ኤፌሶን 6፡12
እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል፤ ያዕቆብ 4፡7
የመስዋእትነት ፀሎት
ይህ አይነት ፀሎት ራሳችንን ለጌታ የምንሰጥበት ፀሎት ሲሆን የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለመፈፀም በማሰብ አስቸጋሪ ውሳኔን የምንወስንበትና የምናሳውቅበት ራሳችንን አሳልፈን የምንሰጥበት የፀሎት አይነት ነው፡፡
ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ እያለ ይጸልይ ነበር። ሉቃስ 22፡42
የፀሎት ዋናው ክፍል የእግዚአብሄርን ፈቃድ መረዳት ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ከእግዚአብሄር ቃል ፈልገን እስከምናገኝ ድረስ ለመፀሠለይ መቸኮል የለብንም፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሄርን ፈቃድ ፈልገን ለማግኘት ጊዜ ሳንሰጥ ከእያንዳንዱ ፀሎታችን ፊት "ፈቃድህ ቢሆን" የሚለውን ቃል መጨመር መፅሃፍ ቅዱሳዊ አይደለም ፀሎት አይደለም፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ፈልገን ማግፀት አለብን፡፡ እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል፡፡
 ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #የእግዚአብሄርፈቃድ #ፀሎት #ልመና #ምልጃ #ምስጋና #ውዳሴ #ተቃውሞ #እንደፈቃዱ #መንፈስቅዱስ #እንዲሰማን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #የእግዚአብሄርቃል #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #መጠየቅ #መንበርከክ #ይቃትታል 

No comments:

Post a Comment