Popular Posts

Friday, June 30, 2017

የንጉስ ልጅነት ክብራችን አይፈቅደውም

ኢየሱስ በመስቀል ላይ የከፈለልንን የሃጢያት እዳ ለእኛ ነው ብለን የተቀበልነው ሁላችን የእግዚአብሄር ልጆች ሆነናል፡፡ ንጉሱ እግዚአብሄር ወደቤተሰቡ ተቀብሎናል፡፡ እያንዳንዱ ቤተሰብ የራሱ የሆነ ዋጋ አሰጣጥና የክብር ደረጃ እንዳለው ሁሉ በእግዚአብሄር ቤተሰብ ውስጥ የንጉስ ልጆች የሚያደርጉዋቸውና የማያደርጓቸው ነገሮች አሉ፡፡ የንጉስ ልጅነት ክብራቸው የሚፈቅደው ነገር አለ የንጉስ ልጅነታቸው ክብር የማይፈቅደው ነገር አለ፡፡
የንጉስ ልጅነታችን ክብር የማይፈቅዳቸው ነገሮች
1.      #ውሸት ክብራችን አይፈቅደውም
ውሸት ሰውን ለሚፈሩ በሰው ፍርሃት ወጥመድ ውስጥ ለወደቁ ሰዎች ነው፡፡ እኛ እግዚአብሄርን ብቻ እንጂ ሰውን አንፈራም፡፡ ውሸት ማንነታቸውን ላልተቀበሉ ያልሆኑትን ለመሆን በመሞከር ጭንቅ ውስጥ ላሉ ሰዎች ነው፡፡ ውሸት ከልጅነት ክብራችን ዝቅ ስለሚያደርገን አንፈቅድም፡፡ እውነት የማንናገርለት ጥቅም የእኛ ደረጃ ስላይደለ እንንቀዋለን፡፡
የምትሠሩት ነገር ይህ ነው፤ እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ፤ በበር አደባባያችሁም የእውነትንና የሰላምን ፍርድ ፍረዱ፤ዘካርያስ 8፡16
2.     #መጣላት ክብራችን አይፈቅድም
ለጥቅማችን መጣላት ክብራችን አይፈቅደውም፡፡ የሚባርክ እግዚአብሄር ስለሆነ በጥቅማችን ቢጣሉንም ፈቀቅ እንላለን፡፡ ሰዎች ቢጣሉንም እንተዋለን፡፡ ሰዎች ቢጣሉን ፈቀቅ እንላለን፡፡  
ከዚያም እልፍ ብሎ ሌላ ጕድጓድ አስቈፈረ፥ ስለ እርስዋም አልተጣሉም፤ ስምዋንም ርኆቦት ብሎ ጠራት እንዲህ ሲል፦ አሁን እግዚአብሔር አሰፋልን፥ በምድርም እንበዛለን። ዘፍጥረት 26፡22
እነሆ የመረጥሁት ብላቴናዬ፥ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ወዳጄ፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፥ ፍርድንም ለአሕዛብ ያወራል። አይከራከርም አይጮህምም፥ ድምፁንም በአደባባይ የሚሰማ የለም። ማቴዎስ 12፡18-19
3.     #መጨቃጨቅ ክብራችን አይፈቅድም
በእግዚአብሄር እናምናለን፡፡ ለጌታ ጊዜን እንሰጣለን፡፡ ሁሉን ነገር በእኔ መንገድ ካልሆነ ብለን በራስ ወዳድነት አንመላለስም፡፡ ጥቅማችንን ከማስከበር ከሰው ጋር አንጨቃጨቅም፡፡ ጥቅማችንን ለማስከበር ሰዎችን አናሳድምም፡፡ ጥቅማችንን ለማስከበር ሰይፍ አንመዝም፡፡ ከጥቅማችን በላይ ለሌላው ሰው እናስባለን እንጠነቀቃለን፡፡ ለመንጋው የማይራሩ ተብሎ እንደተፃፈ ለጥቅማችን ሰውን አንጎዳም፡፡ ስንጠጣበት የነበረውን ምንጭ ለእኔ ካልሆነ ለማንም አይሁን ብለን አደፍርሰን አንሄድም፡፡  
የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ ነገር ግን ገር የሆነ፥ የማይከራከር፥ ገንዘብን የማይወድ፥ 1 ጢሞቴዎስ 3፡3
በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን? ትመኛላችሁ ለእናንተም አይሆንም፤ ትገድላላችሁ በብርቱም ትፈልጋላችሁ፥ ልታገኙም አትችሉም፤ ትጣላላችሁ ትዋጉማላችሁ ነገር ግን አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም፤ ያዕቆብ 4፡1-2
4.     የስስታምን ምግብ መብላት ክብራችን አይፈቅድም
የሰውን ስጦታ ከመቀበላችን በፊት ልቡን እናያለን፡፡ በልቡ ስስትና ቅንአት ይዞ ከሰጠን አንቀበልም፡፡ ብላ ብሎን ቆይቶ የሚከፋው ከሆነ እርሱን ማስደሰት የመጀመሪያ አላማችን ስለሆነ ባለ መብላት እናስደስተዋለን፡፡
የቀናተኛን ሰው እንጀራ አትብላ፥ ጣፋጩ መብልም አይመርህ፤ በልቡ እንዳሰበ እንዲሁ ነውና፤ ብላ ጠጣ ይልሃል፥ ልቡ ግን ካንተ ጋር አይደለም። ምሳሌ 23፡6-7
5.     ትምክታችንን ከንቱ የሚያደርግብንን ነገር ለማድረግ ክብራችን አይፈቅድም
ወንጌልን የሚሰሩት ስለሚያገኙት ጥቅም እንጂ ስለጥሪ ብለው አይደለም እንዲሉ አንፈቅድም፡፡ ወንጌልን የመስራታችንን መነሻ ሃሳብ (motive) ከሚጠራጠሩ ሰዎች ማንኛውንም ጥቅም አንቀበለም፡፡ ማንም ትንሽ ነገር ቢጎድልበት ጥሎ ነው የሚሄደው እንዲል አንፈቅድለትም፡፡ ወንጌልን ስለጥሪ ብቻ መስበካችን ትምክታችን ነው፡፡ ይህንን ትምክታችንን ከንቱ ከሚያደርጉ ሰዎች ስጦታን አንቀበለም፡፡
እኔ ግን ከእነዚህ ሁሉ ምንም አልተጠቀምሁም። እንዲህ እንዲሆንልኝ ይህን አልጽፍም፤ ማንም ትምክህቴን ከንቱ ከሚያደርግብኝ ሞት ይሻለኛልና። 1ኛ ቆሮንቶስ 9፡15
በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን። 1ኛ ቆሮንቶስ 15፡19
6.     የመበለቶችን ቤት መበዝበዝ ክብራችን አይፈቅድም
በነፃ ተቀብላችኋል በነፃ ስጡ የተባልነውን መንፈሳዊ ነገራችንን ከሰዎች ለመጠቀሚያ አናደርገውም፡፡ የእግዚአብሄርን መንፈሳዊ ስጦታ አንነግድበትም፡፡ ለሰዎች ጥቅም የተሰጠንን መንፈሳዊ ስጦታ በማካበድ የሰዎችን ቤት አንበዘብዝም፡፡ በመንፈሳዊ ነገራችንን ተጠቅመን ሰዎችን ለግላዊ ጥቅም መጠቀሚያያችን ለማዋል ክብራችን አይፈቅድም፡፡
የመበለቶችን ቤት የሚበሉ ጸሎታቸውንም በማስረዘም የሚያመካኙ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ። ማርቆስ 12፡40
7.     ማንም ባለጠጋ አደረግኩህ እንዲል ክብራችን አይፈቅድም
እኛን ባለጠጋ የሚያደርግ እግዚአብሄር ነው፡፡ ባለጠጋ የምንሆነው ከእግዚአብሄር ጋር ባለን ቃል ኪዳን ነው፡፡ የእግዚአብሄን ምስጋና እንዲወስድ ማንም አንፈቅድም፡፡ ሰው የሆነ ነገር አድርጎልን አሳለፍኩለት በማለት የእግዚአብሄርን ምስጋና እንዲወስድ ምክኒያትን አንሰጥም፡፡ ስለእኛ መነሳት እግዚአብሄር ብቻውን ሊከበር ስለሚገባ ምስጋናውን ሊቀላቅል ከሚፈልግ ከማንኛውም ሰው አንቀበልም፡፡    
አብራምም የሰዶምን ንጉሥ አለው፦ ሰማይንና ምድርን ወደሚገዛ ወደ ልዑል እግዚአብሔር እጄን ከፍ አድርጌአለሁ፤ አንተ፦ አብራምን ባለጠጋ አደረግሁት እንዳትል፥ ብላቴኖቹ ከበሉት በቀር ከእኔ ጋር ከሄዱትም ድርሻ በቀር፥ ፈትልም ቢሆን የጫማ ማዘቢያም ቢሆን፥ ለአንተ ከሆነው ሁሉ እንዳልወስድ አውናን ኤስኮልም መምሬም እነርሱ ድርሻቸውን ይውሰዱ። ዘፍጥረት 14፡22-24
8.     ነውረኛ ጥቅምን አንወድም
በአራዳም በፋራም ብለን ጥቅምን አናሳድድም፡፡ ንፁህ ጥቅምን ብቻ እንቀበላለን፡፡ ነውረኛ ጥቅምን እንንቃለን፡፡ ጥቅም መምጣቱን ብቻ ሳይሆን የመጣበትንም መንገድ እናያለን፡፡ በንፁህ መንገድ የመጣውን እንቀበላለን በንፁህ መንገድ ካልመጣ ለክብራችን አይመጥንምና አንቀበልም፡፡ በነውር መንገድ የሚመጣ ጥቅምን እንንቃለን፡፡ ሰዎችን አታለን ተቆጣጥረን በመንፈሳዊ ስም አደናግረን እንዲሁም በመናገር ችሎታችን አዋክበንና የማይፈልጉትን አሳምነን ለመጠቀም የንጉስ ልጅነታችን ክብር አይፈቅድም፡፡  
ነውረኛ ረብ የማይወዱ፥ በንጹሕ ሕሊና የሃይማኖትን ምሥጢር የሚይዙ ሊሆኑ ይገባቸዋል።  1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡9
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እግዚአብሔር #አምላክ #ክብር #ምሪት #ሰላም #ቃል #እረፍት #አምልኮ #ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment