Popular Posts

Tuesday, June 27, 2017

ያለ እምነትም እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት የማይቻልበት 7 ምክኒያቶች

ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ዕብራውያን 11፡6
1.      የሚታየው ሁሉ ከማይታየው ስለሆነ ነው፡፡
ካለእምነት እግዚአብሄርን ማስደሰት የማንችለው የሚታየው ነገር ሁሉ ምንጩ የማይታየው አለም መሆኑን ማመን ስለሆነ ነው፡፡ እምነት የሁሉም ነገር ምንጭ የሆነው የማይታየው ነገር ላይ ማተኮር  ነው፡፡ እምነት የማይታየው ነገር ላይ ለማተኮር የሚታየው ነገር ላይ አለማተኮት ነው፡፡ እምነት የሚታየውን አለመመልከት የማይታየውን መመልከት ስለሆነ ነው፡፡
የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፥ ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና፤ የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው። 2ኛ ቆሮንቶስ 4፡17-18
2.     አስፈላጊና ጉዳዬ ልንለው የሚገባው የማይታየውን ስለሆነ ነው
ካለእምነት እግዚአብሄርን ማስደሰት የማይቻለው የማይታየውን ባንመለከት ሁሉን ነገር ስለምናጣ ነው፡፡ የሚታየውን ባንመለከት ምንም የምናጣው ነገር የለም፡፡ አስፈላጊው ነገር የማይታየው ነገር ነው፡፡ ህይወትን የሚሰጠው የማይታየው መንፈስ ነው፡፡ የህይወት ቁልፋችን ያለው በማይታየው ነገር ውስጥ ነው፡፡ የማንኛውም የህይወት ጥያቄያችንን የሚመልሰው የማይታየው ህይወትና መንፈስ የሆነው የእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡
ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው፤ ሥጋ ምንም አይጠቅምም፤ እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው። ዮሃንስ 6፡63
3.     የማይታየው ወደሚታየው ለመምጣት ትግስት ስለሚጠይቅ ነው፡፡
ካለእምነት እግዚአብሄርን ደስ ማሰኘት የማይቻለው የእምነት ውጤት ቅፅበታዊ ስላይደለ ነው፡፡ በመንፈሳዊ አለም ያለው ነገር ወደ ተፈጥሮአዊ አለም እንዲመጣ ትግስት ይጠይቃል፡፡ ትግስት ደግሞ ራስን መካድና ትህትናን ይጠይቃል፡፡   
በእምነትና በትዕግሥትም የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ፥ ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን። እንዲሁም እርሱ ከታገሰ በኋላ ተስፋውን አገኘ። ዕብራውያን 6፡11-12፣15
4.     የሚታየውን ማንም ሰው ማየት ስለሚችል ነው ፡፡
ያለእምነት እግዚአብሄርን ማስደሰት የማይቻለው እምነት የማይታየውን በማየት በማይታየው ላይ ማተኮር ስለሆነ ነው፡፡ የሚታየውን ለማየት ጥረት አያስፈልግም፡፡ የማይታየውን ለማየት ግን በመጀመሪያ ኢየሱስን አዳኝ አድርጎ በመቀበል ከእግዚአብሄር መወለድ በመቀጠልም እግዚአብሄር ለእኛ ያለውን ፈቃድ ከቃሉ ፈልጎ ማግኘት እንዲሁም በፈቃዱ ላይ መቆም ይጠይቃል፡፡
ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው። ዮሃንስ 3፡3
እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው። ሮሜ 10፡17
5.     የእግዚአብሄርን ተስፋ ብቻ በመያዝ ስለሆነ ነው፡፡
ካለእምነት እግዚአብሄርን ደስ ማሰኘት የማይቻለው እምነት በእግዚአብሄር ተስፋ ላይ ብቻ መቆም ስለሆነ ነው፡፡ እምነት ሌሎች ተስፋዎች አያስፈልጉትም፡፡ እምነት የእግዚአብሄር የተስፋ ቃል በቂው ነው፡፡ እምነት ዝናብና ንፋስ አይደግፉትም፡፡
ዘርህ እንዲሁ ሊሆን ነው እንደ ተባለ፥ ተስፋ ባልሆነው ጊዜ የብዙ አሕዛብ አባት እንዲሆን ተስፋ ይዞ አመነ። ሮሜ 4፡18
ለእግዚአብሔርም ክብር እየሰጠ፥ የሰጠውንም ተስፋ ደግሞ ሊፈጽም እንዲችል አጥብቆ እየተረዳ፥ በእምነት በረታ እንጂ በአለማመን ምክንያት በእግዚአብሔር ተስፋ ቃል አልተጠራጠረም። ሮሜ 4፡20-21
እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፦ ነፋስ አታዩም፥ ዝናብም አታዩም፥ ይህ ሸለቆ ግን ውኃ ይሞላል፤ እናንተም ከብቶቻችሁም እንስሶቻችሁም ትጠጣላችሁ። 2ኛ ነገሥት 3፡17
6.     እምነት ትጋትን ስለሚጠይቅ ነው
ካለ እምነት እግዚአብሄርን ደስ ማሰኘት የማይቻለው እምነት ትጋትን ስለሚጠይቅ ነው፡፡ እምነት የሚመጣው ከእግዚአብሄር ቃል ስለሆነ እምነት የእግዚአብሄርን ቃል መፈለግ ማሰላሰል መናገርና ማድረግ አድርጎም መታገስ ስለሚጠይቅ ነው፡፡ እምነት ሰነፎች እንደ እድል እጄ ይገባ ይሆናል ብለው የሚመኙት ነገር አይደለም፡፡ እምነት ተጋድሎ ነው፡፡
መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፥ የተጠራህለትንም በብዙም ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የታመንህለትን የዘላለምን ሕይወት ያዝ። 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡12
የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋልና። ዕብራውያን 10፡36
7.     የእምነት ምስክርነት እውነተኛ ምስክርነት ስለሆነ ነው፡፡
ካለእምነት እግዚአብሄርን ማስደሰት የማይቻልበት ምክኒያት ሰው በእምነቱ ካልተመሰከረለት በምንም ነገር ሊመሰከርለት ስለማይችል ነው፡፡ በእምነቱ የተመሰከረለት ሰው ደግሞ በሁሉም ነገሩ ይመሰከርለታል፡፡ ምንም ነገር ብናደርግ ካለእምነት ከሆነ ሃጢያት ስለሆነ ነው፡፡(ሮሜ 14፡23) የሰው እውነተኛ ምስክርነት የእምነት ምስክርነት ነው፡፡
እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው። ለሽማግሌዎች የተመሰከረላቸው በዚህ ነውና። ዕብራውያን 11፡1-2
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ልብ #ማመን #ቃል #መናገር #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ማሰላሰል #ማድረግ #ሁሉይቻላል #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment