Popular Posts

Follow by Email

Monday, June 19, 2017

የይቅርታ ክብር

እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፥ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፥ ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ፤ ቆላስይስ 313
ይቅር ማለት ክብር ነው፡፡ ማንም መንገደኛ የበደለው ላይ ይይዝበታል ይቅር ማለት ግን ከፍ ያለ የህይወር ደረጃ ነው፡፡ ይቅር
ይቅርታ የጥበበኞች ነው፡፡ ይቅር የሚልና የሚተው ሰው እነዚህን ወሳኝ ጥበቦች የተረዳ ሰው ነው፡፡ ይቅር የሚልና የሚለቅ ሰው መልካም መረዳት ያለውቀ ሰው ነው፡፡
የይቅርታ እውነተኛ ትርጉም
1.      ይቅር የሚል ሰው ይቅር መባሉን የማይረሳ ሰው ነው፡፡
ይቅር መባሉ የማያደንቅና በልቶ ከገሃዲ የሆነ ሰው ይቅር ለማለት ይቸግረዋል፡፡ ይቅር መባሉን የሚያስታውስና የሚያደንቅ ሰው ይቅር ለማለት ይቀለዋል፡፡ ይቅር የሚል ሰው ታላቁ ሃጢያቱ ይቅር የተባለው ሌሎችን ትንንሽ ሃጢያቶች ይቅር እንዲል መሆኑን የተረዳ ሰው ነው፡፡ ይቅርታ ታላቁን ሃጢያት ይቅር ስለመባላችን ለእግዚአብሄር አድናቆታችንንና ምስጋናችንን የምናሳይበት ወርቃማ አጋጣሚ ነው፡፡
ከዚያ ወዲያ ጌታው ጠርቶ፦ አንተ ክፉ ባሪያ፥ ስለ ለመንኸኝ ያን ዕዳ ሁሉ ተውሁልህ፤ እኔ እንደ ማርሁህ ባልንጀራህ የሆነውን ያን ባሪያ ልትምረው ለአንተስ አይገባህምን? አለው። ማቴዎስ 18፡32-33
2.     ይቅር የሚል ሰው ወደፊትም ይቅርታ እንደሚያስፈልገው የሚረዳ ሰው ነው፡፡
የምንኖረው በእግዚአብሄር ምህረት ነው፡፡ የምንኖረው በሰው ምህረት ወይም በሰይጣን ምህረት አይደለም፡፡ የምንኖረው የእግዚአብሄርን ምህረት ተስፋ በማድረግ ነው፡፡ ወደፊትም የእግዚአብሄር ምህረት እንደሚያስፈልገው የሚረዳ ሰው ምህረት ለማድረግ ይበረታታል፡፡ ነገር ግን ከጥፋት ያለፈ የመሰለውና በትእቢት ራሱን ላይ የሰቀለ ሰው ምህረት ለማድርግ ይኩራራል፡፡  
3.     ይቅር የሚል ሰው ነፃ መሆን የሚፈልግ ሰው ነው፡፡
ይቅር የሚል ሰው የበደለውን ሰው መከታተል ፣ ስለበደለው ሰው የራሱን የህይወት መለወጥ የማይፈልግ ሰው ነው፡፡ ይቅር የሚል ሰው የህይወት አላማውን የተረዳ ከሩጫው ማንም እንዲያደናቅፈው የማይፈልግ ሰው ነው፡፡ ይቅር ማለት የሚፈልግ ሰው የበደለውን ሰው በመከታተል በበደለው ሰው ባተሌ በመሆን ህይወቱን ማባከን የማይፈልግ ነው፡፡ ይቅር የማይል ሰው ስለበደለው ሰው ቀን ከሌሊት ሲያስብ ፣ ስለበደለው ሰው ሲናገር ስለበደለው ሰው ሲንቀጠቀጥና ጉልበቱን ሲፈጅ የበደለውን ሰው ኑሮ ይኖራል፡፡ ይቅር የማይል ሰው ስለማይለቅና ስለማይተው የራሱን ህይወት ትቶ ከበደለው ሰው ጋር በደባልነት ይኖራል፡፡ ይቅር የማይል ሰው የራሱን ህይወት ትቶ በደሉን በበዳዩ ላይ ፅፎ ይዞ በዳዩ በየሄደበት የሚከታተል ሰው ነው፡፡  
4.     ይቅር የሚል ሰው ህይወቱን በራሱ መምራት የሚፈልግ ሰው ነው፡፡
ይቅር ማለት የሚፈልግ ሰው ህይወቱን አቅጣጫ ስለበደለው ሰው ለመለወጥ የማይፈልግ ሰው ነው፡፡ ይቅር የሚል ሰው የህይወት ራእዩን ጥሎ በሌላ ጉዳይ መገኘት የማይፈልግ ሰው ነው፡፡ ይቅር ማለት የሚፈልግ ሰው የራሱን የህይወት አላማ በበደለው ሰው ህይወት መለወጥ የማይፈልግ ሰው ነው፡፡ ይቅር ማለትና የበደለውን መልቀቅ የሚፈልግ ሰው የራሱን ህይወት በራሱ መምራት የሚፈልግ ሰው ነው፡፡ ይቅር ማለት የሚፈልግ ሰው የራሱን ህይወት በበደለው ሰው እጅ ላይ መጣል የማይፈልግ ሰው ነው፡፡  
5.       ይቅር ማለት የሚፈልግ ሰው ለዲያቢሎስ እድል ፈንታ መስጠት የማይፈልግ ሰው ነው
ይቅር አለማለትና ጥላቻ የሰይጣን ለም መሬት ነው፡፡ ጥላቻ ለሰይጣን ሰራ ተስማሚ የአየር ሁኔታ ነው፡፡ ሰው ጥላቻን ካስተናገደ ወደደም ጠላም ሰይጣን ይጠቀምበታል፡፡ የሰይጣን አላማው ደግሞ የሚበድለውንም የሚበደለውንም መስረቅ ማረዳ ማጥፋት ነው፡፡ (ዮሃንስ 10፡10) የሰይጣን መጠቀሚያ መሆን የማይፈልግ ስው ይቅር ይላል፡፡ ቆሻሻ መካከል እየኖሩ ዝምብ አይምጣብኝ ማለት እንደማይቻል ሁሉ ይቅር ሳይሉ ስፍራ እየሰጡት ሰይጣን አይንካኝ ማለት አይቻልም፡፡ በተዘዋዋሪ ሰይጣንን  መቃወሚያው መንገድ ጥላቻን አለማስተናገድና ፈጥኖ ይቅር ማለት በምህረት መመላለስ ነው፡፡
በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት። ኤፌሶን 4፡27
6.       ይቅር የሚል ሰው የሰውን ህይወት እንደማይቆጣጠር የተረዳ ሰው ነው፡፡
ይቅር ማለት የሚፈልግ ሰው የራሱ ህይወት እንጂ የሰውን ህይወት መቆጣጠር እንደማይችል ልኩን ያወቀና የተረዳ ሰው ነው፡፡ ይቅር የሚል ሰው ሌላው እንዳይበድለው ማድረግ እንደማይችል ያወቀ ሰው ነው፡፡ ማድረግ የሚችለው ነገር ይቅር ማለት ፣ መተውና  መልቀቅ መሆኑን የተረዳ ሰው ነው፡፡ ይቅር የሚል ሰው ራሱ ተበቃይ እንዳይደለና ፈራጅ ሌላ እንዳለ የተረዳ ሰው ነው፡፡
ተወዳጆች ሆይ፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፥ ለቍጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና። ሮሜ 12፡19
7.       ይቅር ማለት የሚችል ሰው እኔ እሻላለሁ የሚል ሰው ነው፡፡
ይቅር ማለት የሚችል ሰው የበደለው ሰው ስለበደለ ብቻ እንደተጎዳ የሚያስብና ተበዳዩ እንደሚሻል የተረዳ ሰው ነው፡፡ ሰው ከሚበድል መበደል ይሻለዋል፡፡ የሚበድል ሰው አይጠቀምም በከንቱ ይበድላል፡፡ የሚበደል ሰው ግን እግዚአብሄር ይክሰዋል፡፡ ይቅር የሚል ሰው ርህራሄ የሚሰማውና እኔ እሻላለሁ የሚል የአዘኔታ ልብ ያለው ሰው ነው፡፡
እንግዲህ ፈጽሞ የእርስ በርስ ሙግት እንዳለባችሁ በእናንተ ጉድለት ነው። ብትበደሉ አይሻልምን? ብትታለሉስ አይሻልምን? 1 ወደ ቆሮንቶስ 67
8.       ይቅር የሚል ሰው መበደሉ ምንም እንዳማያመጣ የተረዳ ሰው ነው፡፡
የሰው የወደፊት እድል ፈንታ የተያዘው በሰው እጅ አይደለም፡፡ የሰው ፈራጅ እግዚአብሄር ነው፡፡ በፅድቅ የሚፈርድ እግዚአብሄር በሰማይ አለ፡፡ ሰው ተበደለም አልበደለም ለውጥ አያመጣም፡፡ ሰው ተበደለም አልተበደለም ምንም ማለት አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ነው ፈራጅ፡፡ ይቅር የሚል ሰው ፅድቅን በሚያደርገው በእግዚአብሄር የሚመካ ሰው ነው፡፡ ይቅር ሚል ሰው እግዚአብሄርን ደስ የሚያሰኘው ማስተዋል ያለው ሰው ነው፡፡
ነገር ግን የሚመካው፦ ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ ኤርምያስ 924
መበደል ሳይሆን ይቅር አለማለቱ ሰውን ይጎዳዋል፡፡ ሰው ሲበድለን እግዚአብሄር ይክሰናል፡፡ ይቅር ካላልን ግን ይቅር ባለማለታችን እንጎዳለን እንጂ እግዚአብሄር የሚያደርግልን ነገር የለም፡፡ ሰውን የሚጎዳው መበደል ሳይሆን ይቅር አለማለት ነው፡፡
9.       ይቅር የሚል ሰው ይቅር አለማለቱ በዳዩን እንደማይጎዳ የተረዳ ሰው ነው፡፡
በደሉ ተፈፅሟል፡፡ ጥፋተኛ ከሆነ እንደበዳዩ ደረጃ የሚፈርደው እግዚአብሄር ነው፡፡ የተበደለ ሰው ይቅር አለማለቱ በፍርዱ ላይ ምንም ተፅእኖ የለውም፡፡ የተበደለ ሰው ግን ይቅር ካላለ በራሱ ህይወት ላይ ጉዳት ያመጣል፡፡ የተበደለ ሰው ቶሎ ይቅር ስላለ እግዚአብሄር የበዳዩን ጥፋት አያቀልለትም፡፡ ለረጅም ጊዜ ስለያዘው ደግሞ ጥፋቱን አያከብድውም፡፡ ይቅር ያላለ ሰው የሚጎዳው ራሱን ብቻ ነው፡፡   
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ይቅርታ #ምህረት #ፍርድ #ጠላት #ዲያቢሎስ #ስፍራ #ኢየሱስ #ጥላቻ #ትእቢት #መራርነት #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment