Popular Posts

Monday, June 12, 2017

በአስሩ የድህነት አስተሳሰብ ምልክቶች ዛሬ ህይወትዎን ይመዝኑ

ብልፅግና የሚመነጨው ከእግዚአብሄር ሲሆን ድህነት የሚመነጨው ከሰይጣን ነው፡፡ ድህነትም ብልፅግናም የሚያልፈው በሰው አእምሮ ነው፡፡ ሰው የሚበለፅገው አእምሮው ነው፡፡ አእምሮው የበለፀገ ሰው ደሃ መሆን አይችልም፡፡ አእምሮው ደሃ የሆነ ሰው ሊበለፅግ አይችልም፡፡
የድህነት አስተሳሰብ ያለው ሰው ደሃ ነው፡፡ የብልፅግና አስተሳሰብ ያለው ሰው ባለጠጋ ነው፡፡
በልቡ እንዳሰበ እንዲሁ ነውና፤ ምሳሌ 23፡7
·         ምስኪን እኔ - የድህነት አስተሳሰብ
ሰው ራሱን እግዚአብሄር በክርስቶስ እንደሚያየው ካላየና ሰው በሚታይ ነገር ብቻ ራሱን ከመዘነ ድሃ ሰው ነው፡፡ ድሃ ለመሆን ገንዘብ ማጣት አያስፈልግም፡፡ ገንዘብ ኖሮት የእግዚአብሄር አቅርቦት የማይታየውና የእግዚአብሄር የሚያስችል ሃይል መረዳት የሌለው ሰው አስተሳሰቡ ያልበለፀገ ሰው ደሃ ሰው ነው፡፡
·         እንድበለፅግ ሰው ያስፈልገኛል የሚል የድህነት አስተሳሰብ
እኔን ለማንሳት ሃብታም ሰው ይጠይቃል የሚል ሰው ድሃ ሰው ነው፡፡ እኔን ለማንሳት የሚያስፈልገው እግዚአብሄር ብቻ ነው የሚል ሰው ባለጠጋ ሰው ነው፡፡ ለመበልፀግ ሰው አያስፈልግህም፡፡ ለመበልፀግ የሚያስፈልግህ ባለጠጋውን እግዚአብሄን ማወቅና ከእርሱ ጋር እንዴት መኖር እንዳለብህ መረዳት ነው፡፡ ሰው ግን ለብልፅግናውና ስለ እድገቱ አይኑን ከእግዚአብሄር ላይ ካነሳ ደሃ ሰው ነው፡፡ ደሃ ለመሆን ገንዘብ ማጣት የለበትም፡፡
ክብር ከምሥራቅ ወይም ከምዕራብ ወይም ከምድረ በዳ የለምና፤ እግዚአብሔር ፈራጅ ነውና ይህን ያዋርዳል ይህንም ያከብራል። መዝሙር 75፡6-7
·         ያለማመስገን - የድህነት አስተሳሰብ
የማያመሰግን ሰው ድሃ ሰው ነው፡፡ እግዚአብሄርን ላለማመስገን ምክኒያት የሚያገኝ ሰው ድሃ ሰው ነው፡፡ ምንም ቢደረግለት የማይበቃው ሰው ደሃ ሰው ነው፡፡ ለአንዳንድ ሰው ምንም ነገር የሚበቃ አይደለም፡፡ ድሃ ሰው ሁል ጊዜ ጎረቤቱን ያያል ፡፡ የድህነት አስተሳሰብ ያለበት ሰው ከጎረቤቱ የሚመኘው ነገር አያጣም፡፡ አንዳንድ ሰው እግዚአብሔር በቤቱ የሚሰራውን ድንቅ ስለማያይ አይኑ ወደጎረቤቱ ይቀላውጣል፡፡ ለመኖር እጅግ ብዙ ነው የሚያስፈልገው ደሃ ሰው ነው፡፡ ድሃ ሰው ይህ ይህ ይህ ከሌለኝ ዋጋ የለኝም የሚል አስተሳሰብ ያለው ሰው ነው፡፡  ድሃ ሰው ምንም ቢሆንለት ምኞት ቱን መቆጣጠር ስለማያውቅ ይሰቃያል፡፡
ኀጥእ ቀኑን ሁሉ ምኞትን ይመኛል፤ ጻድቅ ግን ይሰጣል፥ አይሰስትም። ምሳሌ 21፡26
ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፥ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ። 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡10
·         ድህነትን መፍራት - የድህነት አስተሳሰብ
አንዳንድ ሰው ድህነትን በጣም ከመፍራቱ የተነሳ ድሃ ላለመሆን ምንም ነገር ያደርገሃል፡፡ ድህነት የሚያስፈራራህ ከሆንክ ከድህነት ፍርሃት ነጻ መውጣት አለብህ፡፡ ድህነትን የሚፈራ ሰው እግዚአብሔን አይፈራም፡፡ የድህነት ፍርሃት የሚመራው ሰው እግዚአብሄር ሊመራው አይችልም፡፡ ማጣትን አይቶ ምንም እንደማያመጣ የተረዳ ሰው ባለጠጋ ሰው ነው፡፡ ድህነትን አልፎበት ልኩን ያየና የናቀው ሰው ባለጠጋ ሰው ነው፡፡ ሰው የሚኖረው በእግዚአብሄር ፀጋ እንደሆነ እንጂ በማግኘት እንዳልሆነ የተረዳ ሰው ባለጠጋ ሰው ነው፡፡  
ይህን ስል ስለ ጉድለት አልልም፤ የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና። መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ። ፊልጵስዩስ 4፡11-12
·         ማግኘትን ማክበር - የድህነት አስተሳሰብ
ሰው ሃብታምም ባይሆን ሃብትን በተሳሳተ መልኩ የሚረዳ ሰው በድህነት እስራት ውስጥ ይኖተራል፡፡ ሃብታም ቢሆን ደስታ እንደሚያስገኝ ማሰብ የድህነት ምልክት ነው፡፡ ሃብት ቢያገኝ እንደሚሳካለት ማሰብ ድህነት ነው፡፡ ሃብት ማድረግ የማይችለው ብዙ ነገር እያለ ሃብት መስራት የማይችለውን ነገር ይሰራል የሚል የተሳተ ግምት ድህነት ነው፡፡ ለሃብት የተሳሳተ ግምት መኖር ድህነት ነው፡፡ እግዚአብር ብቻ የሚሰራውን ነገር ሃብት ይሰራል ብሎ መጠበቅ የድህነት አስተሳሰብ ነው፡፡
እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም ሩጫ ለፈጣኖች፥ ሰልፍም ለኃያላን፥ እንጀራም ለጠቢባን፥ ባለጠግነትም ለአስተዋዮች፥ ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፤ ጊዜና እድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል። መክብብ 9፡11
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፥ ኃያልም በኃይሉ አይመካ፥ ባለ ጠጋም በብልጥግናው አይመካ፤ ነገር ግን የሚመካው፦ ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ ኤርምያስ 9፡23-24
·         ቅንጦት - የድህነት አስተሳሳብ
ደሃ ሰው ራሱን መግዛት ስለማይችል ያለውን ነገር በማያስፈልግ ነገር ላይ ያባክናል፡፡ የድህነት አስተሳሰብ ያለው ሰው ያለውን ጥሪት በሚያስፈልገው ነገር ላይ ሳይሆን በምኞቱ ላይ በማዋል ሃብቱን ያባክናል፡፡ ድሃ ሰው ያለውን ነገር በማያስፈልግ በቅንጦት ነገር ላይ ያባክናል፡፡ የድህነት አስተሳሰብ ያለው ሰው ያለውን ነገር በአላስፈላጊ ነገር ላይ ስለሚያጠፋው በሚያስፈልገው ነገር ይቸገራል፡፡  
ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡6
·         አልችልም - የድህነት አስተሳሰብ
ድሃ ሰው እችላለሁ የማይል ሰው ነው፡፡ ሁሌ አልችልም የሚል ሰው ድሃ ሰው ነው፡፡ እግዚአብሄር በምድር ላይ የሰጠኝን ስራ ሁሉ ሰርቼ ማለፍ እችላለሁ የሚል ሰው ባለጠጋ ሰው ነው፡፡ ሲደክም እንኳን የእግዚአብሄር ፀጋ ድካሜን ይሸፍናል የማይል ሰው ድሃ ሰው ነው፡፡ በመከራ ውስጥ ሲያልፍ እጅ የሚሰጥ ሰው ድሃ ሰው ነው፡፡ በድካሜ የእግዚአብሄር ፀጋ ድካሜን ይፈፅመዋል የማይል ሰው ድሃ ሰው ነው፡፡ ከራሱ አልፎ የሚያስችልን የእግዚአብሄርን ሃይል የማያይ ሰው ድሃ ሰው ነው፡፡  
እርሱም፦ ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ። 2ኛ ቆሮንቶስ 12፡9
አብረንም እየሠራን የእግዚአብሔርን ጸጋ በከንቱ እንዳትቀበሉ ደግሞ እንለምናለን፤ ነገር ግን በሁሉ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ራሳችንን እናማጥናለን፤ በብዙ መጽናት፥ በመከራ፥ በችግር፥ በጭንቀት፥ በመገረፍ፥ በወኅኒ፥ በሁከት፥ በድካም፥ እንቅልፍ በማጣት፥ 2ኛ ቆሮንቶስ 6፡1፣4-5
·         ይቅር አለማለት - የድህነት አስተሳሰብ
ሰው የበደሉትን ይቅር ካላለ ፣ ካልቀቀና የሙጥኝ ካለ ደሃ ሰው ነው፡፡ መበደል የለብኝም ብሎ ካሰበ እና ለመበደል ምንም ቦታ የማይሰጥ ሰው ቋጣሪ ሰው ነው፡፡ እግዚአብሔር በብዙ ይቅር ብሎት ሌላውን ይቅር ማለት የማይችል ደሃ ሰው ነው፡፡ የእግዚአብሄን ይቅርታ ውጦ ሌላን ይቅር የማይል ሰው ስስታም ሰው ነው፡፡  
ከዚያ ወዲያ ጌታው ጠርቶ፦ አንተ ክፉ ባሪያ፥ ስለ ለመንኸኝ ያን ዕዳ ሁሉ ተውሁልህ፤ እኔ እንደ ማርሁህ ባልንጀራህ የሆነውን ያን ባሪያ ልትምረው ለአንተስ አይገባህምን? አለው። ማቴዎስ 18፡32-33
·         አለመስጠት - የድህነት አስተሳሰብ
ሰው የተፈጠረው ለመስጠትና ለመባረከ ነው፡፡ ሃብቱን ራሱ ላይ ብቻ የሚያፈስ ሰው ድሃ ሰው ነው፡፡ መሰብሰብ እንጂ መስጠትና መባረክ የማያውቅ ሰው ድሃ ሰው ነው፡፡ ራስ ወዳድ የሆነ ስለሌላው ግድ የማይለው ሰው ምንም ያህል ሃብት ቢኖረው ድሃ ነው፡፡ እግዚአብሄር በሰጠው ገንዘብ የዘላለምን ወንጌልን የማይሰራ ሰው ድሃ ሰው ነው፡፡ ሰው ባለጠግነቱ የሚለካው በሚያከማቸው ሳይሆን ባከማቸው ባለጠግነት በሚሰራው መልካም ስራ ነው፡፡
ለራሱ ገንዘብ የሚያከማች፥ በእግዚአብሔር ዘንድም ባለ ጠጋ ያልሆነ እንዲህ ነው። ሉቃስ 12፡21
እኔም እላችኋለሁ፥ የዓመፃ ገንዘብ ሲያልቅ በዘላለም ቤቶች እንዲቀበሉአችሁ፥ በእርሱ ወዳጆችን ለራሳችሁ አድርጉ። ሉቃስ 16፡9
በአሁኑ ዘመን ባለ ጠጎች የሆኑት የትዕቢትን ነገር እንዳያስቡ፥ ደስም እንዲለን ሁሉን አትርፎ በሚሰጠን በሕያው እግዚአብሔር እንጂ በሚያልፍ ባለ ጠግነት ተስፋ እንዳያደርጉ እዘዛቸው። እውነተኛውን ሕይወት ይይዙ ዘንድ፥ ለሚመጣው ዘመን ለራሳቸው መልካም መሠረት የሚሆንላቸውን መዝገብ እየሰበሰቡ፥ መልካምን እንዲያደርጉ በበጎም ሥራ ባለ ጠጎች እንዲሆኑ፥ ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ እንዲሆኑ ምከራቸው። 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡17-19
·         አለመተው - የድህነት አስተሳሰብ
የድህነት አስተሳሰብ ያለው ሰው በህይወቱ ለቀቅ ያለ አይደለም፡፡ የእርሱ ነገር ወደሌላ ሰው እንዲያልፍ አይፈልግም፡፡ ለሳንቲምም ቢሆን ይጨቃጨቃል፡፡ መብቱን በፍፁም አሳልፎ አይሰጥም፡፡ ንጥቂያን በቀላሉ አያየውም፡፡ ይሁን አይልም አይተውም፡፡ እኔን ድሃ ሊያደርገኝ የሚችል ሰው የለም አይልም፡፡ እያንዳንዷን ስንጣሪ አንቆ ነው የሚቀበለው፡፡ ይህ ሰው ድሃ ሰው ነው፡፡ ለቀቅ ያለ አስተሳሰብ የለውም፡፡ በውስጡ ባለው በእግዚአብሄር ፀጋ አይመካም፡፡
የሚበልጥና ለዘወትር የሚኖር ገንዘብ በሰማይ ራሳችሁ እንዳላችሁ አውቃችሁ፥ በእስራቴ ራራችሁልኝ የገንዘባችሁንም ንጥቂያ በደስታ ተቀበላችሁ። ዕብራውያን 10፡34
እንዲከስህም እጀ ጠባብህንም እንዲወስድ ለሚወድ መጎናጸፊያህን ደግሞ ተውለት፤ ማንም ሰው አንድ ምዕራፍ ትሄድ ዘንድ ቢያስገድድህ ሁለተኛውን ከእርሱ ጋር ሂድ። ማቴዎስ 5፡40-41
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ብልፅግና #የብልፅግናወንጌል  #በረከት #ስኬት #የድህነትአስተሳሰብ #እረኛእግዚአብሄር #ስምረት #መሰረታዊፍላጎት #ሁሉየእናንተነውና #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #የተትረፈረፈህይወት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment