Popular Posts

Saturday, June 24, 2017

ከእግዚአብሄር የመቀበል ጥበብ

ብዙ ሰዎች ለእግዚአብሄር እንዴት እንደሚሰጡ ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን ከእግዚአብሄር እንዴት እንደሚቀበሉ አያውቁም፡፡ የእግዚአብሄርን የመስጠት መንገድ ስለማይረዱ ከእግዚአብሄር ጋር ይተላለፋሉ፡፡ ወይም ከእግዚአብሄር የመቀበለን መንገድ ስለማይረዱ የእግዚአብሄርን መስጠት በአንድ አቅጣጫ ብቻ ስለሚጠብቁ እግዚአብሄር ቢሰጣቸው እንኳን ከእግዚአብሄር ስለተቀበሉት እውቅናንና ምስጋናን ለእግዚአብሄር አይሰጡም፡፡ ከእግዚአብሄር የመቀበል ጥበቡ ስለሌላቸው ለእግዚአብሄር አብዝቶ ለመስጠት የሚገባቸውን ያህል አይነሳሱም፡፡
ለእግዚአብሄር ገንዘብን ስንሰጠው ገንዘብን ጨምሮ ብዙ የሚሰጠን ነገሮች አሉ፡፡ ለእግዚአብሄር አብልጥን ለመስጠት ከእግዚአብሄር የመቀበልን ጥበብ መማር ያስፈልጋል፡፡ ለእግዚአብሄር ገንዘባችንን ፣ እውቀታችንን ፣ ጊዜያችንንና ጉልበታችንን ስንሰጠው ዘርፈ ብዙ በሆነ መንገድ እግዚአብሄር ይከፍለናል፡፡
ከእግዚአብሄር የማንፈልገው ነገር ስለሌለና እግዚአብሄር በሁሉም የህይወታችን እቅጣጫና በሁሉም ነገራችን ስለሚያፈልገን ከእግዚአብሄር እንዴት እንደምንቀበል ማወቅ አለብን፡፡ 
ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ዕብራውያን 11፡6
የእግዚአብሄር የአከፋፈል መንገዶች
1.      እግዚአብሄር በሃሳብ ይባርከናል
አንድ ስራ ከሃሳብ ይጀምራል፡፡ አንድ ነገር መስራት እንድንችል እግዚአብሄር ሃሳብን ይሰጠናል፡፡ አንድን ነገር ወደፍፃሜ እንድናመጣ እግዚአብሄር በማስፈፀሚያው ሃሳብ ይባርከናል፡፡ እግዚአብሄር አዳዲስ የፈጠራ ሃሳቦችን ይሰጠናል፡፡ እግዚአብሄር በራእይ ይባርከናል፡፡ ገንዘብ ኖሮን ነገሮችን መረዳትና መፈፀም ካልቻልን ምን ይጠቅመናል?
በሰነፍ እጅ የጥበብ መግዣ ገንዘብ መኖሩ ስለ ምንድር ነው? ጥበብን ይገዛ ዘንድ አእምሮ የለውምና። ምሳሌ 17፡16
ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፥ ለእርሱም ይሰጠዋል። ያዕቆብ 1፡5
2.     እግዚአብሄር በመነሳሳት ይባርከናል
እግዚአብሄር በመፈለግ ይባርካል፡፡ እግዚአብሄር ልባችንን ያነሳሳል፡፡ ምንም ሃሳቡ በሌለን ጊዜ ከመቀፅበት ልባችን አንድን ነገር ለማድረግ ይነሳሳል፡፡ አንድ ነገር ጊዜው ሲሆን እግዚአብሄር ከመቀፅበት ልባችንን ያቀጣጥለዋል፡፡ ይህንን የትኛውም ገንዘብ ሊገዛው የማይችል የእግዚአብሄር የመስጫና የመባረኪያ መንገድ ነው፡፡
ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእናንተ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና። ፊልጵስዩስ 2፡13
3.     እግዚአብሄር በድፍረት ይባርከናል
ሌላው ለእግዚአብሔር ሰጥተን እግዚአብሄር ለእኛ የሚሰጥበት መንገድ ድፍረት ነው፡፡ ከእኛ የተሻለ የሚታይ ነገር ኖሯቸው ያልደፈሩትን ነገር ለመፈፀም እንድንደፍር ድፍረትን በመስጠት ጌታ ይባረከናል፡፡ እኛም እንኳን አስኪገርመን ድረስ እንድንደፍር እምነትን ይሰጠናል፡፡ ምንም ያህል ገንዘብ ሊገዛው የማይችል እግዚአብሄር ለእኛ የሚሰጥበትና የሚባርክበት መንገድ ነው፡፡
እምነት ግን መጥቶአልና ከእንግዲህ ወዲህ ከሞግዚት በታች አይደለንም። ገላትያ 3፡25
ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት፥ ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፥ ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ፥ 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡9
4.     የልቦናችንን አይኖች በማብራት ይከፍለናል
ለእግዚአብሄር ስንሰጥ ከእግዚአብሄር የምንቀበልበት ሌላው መንገድ የአይን መከፈት ነው፡፡ እግዚአብሄር አይናችንን ይከፍታል፡፡ እግዚአብሄር እይታን ይሰጠናል፡፡ እግዚአብሄርን የልቦናችንን አይኖች ያጠራል፡፡ እግዚአብሄር ዋጋ መስጠት ላለብን ነገር ብቻ ዋጋ እንድንሰጥ ያሳየናል፡፡ እግዚአብሄር አጥርተን በማየት ይባርከናል፡፡
የክብር አባት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን በማወቅ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እለምናለሁ። ኤፌሶን 1፡17
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እምነት #መስጠት #ማካፈል #መባረክ #ስጡ #ምፅዋት #መቀበል #ጥበብ #ማስተዋል #እይታ #ሃሳብ #መነሳሳት #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #መዝራት #ከልቡ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #ድሃ #መፅሃፍቅዱስ #በደስታ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment