Popular Posts

Tuesday, February 28, 2017

እንቅጩን የሚናገር መስተዋት

ስለዚህ ርኵሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ። ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ። ቃሉን የሚሰማ የማያደርገውም ቢኖር የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት የሚያይን ሰው ይመስላል፤ ራሱን አይቶ ይሄዳልና፥ ወዲያውም እንደ ምን እንደ ሆነ ይረሳል። ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ ተመልክቶ የሚጸናበት፥ ሥራንም የሚሠራ እንጂ ሰምቶ የሚረሳ ያልሆነው፥ በሥራው የተባረከ ይሆናል። ያዕቆብ መልእክት 1፡21-25
እግዚአብሄር ቃሉን የሰጠን እንድናደርገው ነው፡፡ ቃሉን ስናደርገው ብቻ ነው የሚጠቅመን፡፡ መዋጥ የሚገባንን መድሃኒት ባንውጠውና ከሰውነታችን ጋር ባናዋህደው እንደማይጠቅመን ሁሉ ቃሉም የሚጠቅመን በተግባር ስናደርገውና ከእኛ ጋር ሲዋሃድ ብቻ ነው፡፡
ቃሉን መስማትና ማወቅ ወሳኝ ነው፡፡ ነገር ግን በህይወታችን በእውነት አወቅነው የምንለው ቃል የተገበርነውን ቃል ብቻ ነው፡፡ ምክኒያቱም ፍሬያማ የሚያደርገን የተገበርነው ቃል ብቻ ነው፡፡ ቃሉ በውስጡ ነፃ የሚያወጣ የተጠራቀመ ጉልበት አለው፡፡ ያ የተጠራቀመ ሃያል ጉልበት ሊሰራልን የሚችለው እኛ ውስጥ ሲተገበርና በህይወታችን ስናደርገው ብቻ ነው፡፡ ወሳኙ ውድድር የመስማትና የማወቅ ብቻ ሳይሆን የማድረግም ነው፡
የሰማነው ግን ያልተገበርነው ቃል የእኛ አይደለም፡፡ ያልተገበርነው ቃል እንዲያውም ያታልለናል፡፡ ወይ አላወቅኩትም ብለን እውቀቱን አንፈልግም፡፡ ወይም ደግሞ አውቀነው አልተጠቀምንበት፡፡ ስለዚህ በመሃል ቤት እንቀራለን ራሳችን እናታልላለን፡፡
ሰው ቤቱ ውስጥ ምርጥ መስታወት አስቀምጦ ነገር ግን ያየውን ነገር ቶሎ ካላስተካከለው የመስታወቱ ጥቅም ምኑ ላይ ነው፡፡ እንዲሁም ሰው ቃሉን ሰምቶ ቶሎ መንገዱን ካልወጠና እንደቃሉ ካልተገበረው ቃሉን መስማት ብቻ ምንም አይጠቅመውም፡፡ የሰማው ቃል በእውነት የሚጠቅመው ያደረገው ጊዜ ነው፡፡  
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ቃል #መታዘዝ #አማርኛ #ስብከት #መስተዋት #መፅሃፍቅዱስ #ነፃነት  #እምነት #መስማት #መከተል #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Monday, February 27, 2017

የሰመጠው ጓደኛ ታሪክ

ዎች ማን ኒ የተባሉ ቻይናዊ አገልጋይ The Normal Christian Life በአማርኛ (ክርስትና እንዲህ ነው) ተብሎ በተተረጎመው መፅሃፋቸው ላይ እኛ አማኞች በመንፈስ ቅዱስ ላይ እንዴት መደገፍ አንዳለብን ሲያስተምሩ ይህንን ታሪክ ፅፈዋል፡፡
በድሮ ዘመን  የምንታጠብበት የተዘጋጀ ቦታ ስላልነበረን ሰውነታችንን የምንታጠበው ወንዝ ወርደን ነበር፡፡ እንደተለመደው አንድ ጊዜ ወንዝ ወርደን እየታጠብን እያለ አንዱ ዋና የማይችል ጓደኛችን ውሃ ውስጥ ገባ፡፡ ዋና ባለመቻሉ ለመዳን ባለው መፍጨርጨር ምክኒያት ብቅ ጥልቅ ይል ጀመር፡፡ አንድ በመካከላችን ዋና የሚችል ጓደኛችን ነበርና ገብተህ አውጣው ብለን መጮኽ ጀመርን ፡፡ ነገር ግን ጥያቄያችን ዋና የሚችለውን ጓደኛችንን ብዙም ሊያንቀሳቅሰው አልቻለም፡፡ በዚህም ምክኒያት ቶሎ ወደ ውሃው በመግባት ሊያወጣው አልሞከረም ነበር፡፡ ጓደኛችን ቆየት ብሎ ግን ውሃ ውስጥ ገብቶ ጓደኛችንን አወጣው፡፡
በጣም ተገርመን ለምንድነው ግን መጀመሪያ ወደውሃ ውስጥ ገብተህ ለመርዳት ያልሞከርከው ለሚለው ጥያቄያችን መልሱ ይህ ነበር፡፡ ልክ ውሃ ውስጥ አንደወደቀ እኔም ወደውሃው ብገባ ኖሮ እሱ ብቻ ሳይሆን ሁላችንም እንሰጥም ነበር፡፡ ምክኒያቱም እርሱ በሙሉ ሃይሉ ነበር የነበረው፡፡ ለመዳን በሚያደርገው መፍጨርጨር አንገቴ ላይ ተጠምጥሞ ይደፍቀኝና ይገድለኝ ነበር፡፡
ስለዚህ ነው ትንሽ መጠበቅ የፈለግኩት፡፡   ከትንሽ ጊዜ በኋላ በራሱ ሞክሮ ሲያቅተውና እየደከመ ሲመጣ በትንሽ ሃይል ገፍቼ አወጣዋለሁ ብዬ ነው፡፡ እርሱም ጉልበቱን በመፍጨርጨርና በመሞከር ስለቀነሰ እኔንም ሊገድለኝ የማይችለብት ድካም ላይ ነበር የነበረው ብሎ አስረዳን፡፡
እንዲሁም በህይወታችን የሚያስፈልገን ነገር በራሳችን ጉልበት መፍጨርጨር ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ላይት ማረፍና መደገፍ ነው፡፡ እኛ በራሳችን ጉልበት ለማድረግ ስንሞክርና ስንፍጨረጨር እግዚአብሄር ያርፋል፡፡ እኛ በእርሱ ላይ ስናርፍ ፣ ለእርሱ እሺ ስንልና ራሳችንን በእርሱ ላይ ስንተው እርሱ በእኛ ይሰራል፡፡  
በመንፈስ ብንኖር በመንፈስ ደግሞ እንመላለስ። ገላትያ 5፡25
በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና። ሮሜ ሰዎች 8፡1-2
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #መንፈስቅዱስ #አፅናኝ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መሰጠት #መገዛት #ምሪት #ድምፅ #ቅባት #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #መውደድ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Sunday, February 26, 2017

የወንድሞች ህብረት ሽቱ

ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፥ እነሆ፥ መልካም ነው፥ እነሆም፥ ያማረ ነው። ከራስ እስከ ጢም እንደሚፈስስ፥ እስከ አሮን ጢም፥ በልብሱ መደረቢያ እንደሚወርድ ሽቱ ነው። በጽዮን ተራሮች እንደሚወርድ እንደ አርሞንዔም ጠል ነው፤ በዚያ እግዚአብሔር በረከቱን ሕይወትንም እስከ ዘላለም አዝዞአልና። መዝሙር 133፡1-3
ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ያለው ግንኙነትና ህብረት ወሳኝ ነው፡፡ ሰው ለእግዚአብሄር ክብር ስለተፈጠረ ከእግዚአብሄር ጋር ህብረት ከሌለው ህይወቱን በከንቱነት ያሳልፋል፡፡
ለእግዚአብሄር ከብር የሚኖሩ ወንድሞች ደግሞ እርስ በእርሳቸው ያላቸው ግንኙነት እንዲሁ ወሳኝ ነው፡፡ የእኛ በህብረት መቀመጣችን እግዚአብሄርን ያስደስተዋል፡፡እግዚአብሄር በእኛ አንድነት ደስ ይሰኛል፡፡
እግዚአብሄር በመልኩና በአምሳሉ ፈጥሮናል፡፡ እኛ ስሜት እንዳለን ሁሉ እርሱም ስሜት አለው፡፡ እኛን ደስ የሚለን ነገር እንዳለ ሁሉ እርሱንም ደስ የሚለው ነገር አለ፡፡ እርግጥ ነው ሰውን ደስ የሚያሰኘው ነገር ሁሉ እግዚአብሄርን ደስ አያሰኘውም ፡፡ ሰውን የሚያስደንቀው ነገር ሁሉም እግዚአብሄርን አያስደንቀውም፡፡ ሰውን የሚያምረን ነገር ሁሉ እግዚአብሄርን አያምረውም፡፡  
እግዚአብሄርን የሚያስደስተው ነገር የወንድሞች ህብረት ነው፡፡ ሽቱ መልካም ስሜት እንደሚፈጥር ሁሉና ደስ እንደሚያሰኝ ሁሉ የወንድሞች ህብረት እግዚአብሄርን ደስ ያሰኘዋል፡፡ የአርሞንዔም ጠል ምድሩን እንደሚያለመልመው ሁሉና ምድሩን እንደሚያረካው የወንድሞች ህብረት እግዚአብሄርን ያረካዋል፡፡
እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች ይዘረዝርና ሰባተኛውን በወንድሞች ህብረት ላይ የሚሰራውን በደል ነፍሱ አጥብቃ እንደምትጠየፈው መፅሃፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡
እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች ናቸው፥ ሰባትንም ነፍሱ አጥብቃ ትጸየፈዋለች፤ በሐሰት የሚናገር ሐሰተኛ ምስክር፥ በወንድማማች መካከልም ጠብን የሚዘራ። ምሳሌ 619
ስለዚህ ነው እግዚአብሄርን ለማስደሰትና የወንድሞችን ህብረት ለመጠበቅ ትጋት እንደሚጠይቅ መፅሃፍ ቅዱስ የሚያስተምረው፡፡
በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ። ኤፌሶን 4፡3
ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፥ እነሆ፥ መልካም ነው፥ እነሆም፥ ያማረ ነው። ከራስ እስከ ጢም እንደሚፈስስ፥ እስከ አሮን ጢም፥ በልብሱ መደረቢያ እንደሚወርድ ሽቱ ነው። በጽዮን ተራሮች እንደሚወርድ እንደ አርሞንዔም ጠል ነው፤ በዚያ እግዚአብሔር በረከቱን ሕይወትንም እስከ ዘላለም አዝዞአልና። መዝሙር 1331-3
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ወንድሞች #ፍቅር #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #ህብረት #ግንኙነት #ሽቱ #ያማረ #በፍፁምሃይል #መውደድ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ


Saturday, February 25, 2017

ፍቅር 100 %

ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ፦ እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፥ አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ የምትል ናት። ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ማርቆስ 12፡29-30
እግዚአብሄር የዘላለም ንጉስ ነው፡፡ እግዚአብሄር ከእኛ ግማሽ ወይም የተከፋፈለ ፍቅር አይቀበልም፡፡ እግዚአብሄር ከእኛ ሙሉ ፍቅር ይጠብቃል፡፡ እገዚአብሄር ኩሩ ነው እግዚአብሄር ጎዶሎን ነገር እንዳውም አይቀበለም፡፡
ሁለት አሳብ ላለው በመንገዱም ሁሉ ለሚወላውል ለዚያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች እንዲያገኝ አይምሰለው። ያዕቆብ 1፡7-8
እኛ የእግዚአብሄር ፍጥረት ነን፡፡ ለክብሩ የሰራን ፍጥረቶቹ ነን፡፡ ሲፈጥረን ለምን እንደፈጠረን ሊናገር የሚችለው እርሱ ብቻ ነው፡፡ በእኛ ላይ ሙሉ ስልጣን ያለውና ከእኛ ምን እንደሚፈልግ በሙሉ ስልጣን ማዘዝ የሚችለው እግዚአብሄር ነው፡፡
ይህ ለክብሩ የፈጠረን ጌታ ከእኛ የሚጠብቀው 100% እንድንወደ ነው፡፡
በፍፁም ልባችን እንድንወደው እግዚአብሄር ይፈልጋል፡፡ ልብ የህይወታችን ማእከላዊ ስፍራና የህይወት ሁሉ ምንጭ ነው፡፡ እግዚአብሄር ከልባችን እንድንወደው ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር ከትርፋችን ሳይሆን ከዋናችን እንድንወደው ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄርን ከላይ ከላይ ሳይሆን ከውስጣችን እንድንወደው ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄርን በአንደበታችን ሳይሆን ከልባችን እንድንወደቅው ይፈልጋል፡፡ እገዚአብሄር ለታይታ ሳይሆን በፍፁም እንድወደው ይፈልጋል፡፡  
ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፥ ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤ ማቴዎስ 15፡8
እግዚአብሄር በፍፁም ነፍሳችን እንድንወደው ይጠብቅብናል፡፡ እግዚአብሄር በሙሉ ስሜታቸን እንድንናስቀድመው ይፈልጋል፡፡ ስለእርሱ ስናስብ ልባችን እንዲሞቅ ይፈልጋል፡፡ ስለእርሱ ስንናገር ልባችን እንዲቀጣጠል ይፈልጋል፡፡ እርሱን ስናገልግል በደስታና በፈንጠዝያ እንድናገለግለው ይጠብቃል፡፡ እግዚአብሄር በሙሉ ልባችን እንድንወደው ይፈልጋል፡፡
እግዚአብሄር በፍፁም ሃሳባችን እንድንወደውም ይፈልጋል፡፡ ሃሳባችን በርሱ ሃሳብ እንዲሞላ ይፈልጋል፡፡ በህይወታችን ተግዳሮት ሲያጋጥመን የመጀመሪያው የመፍትሄ ሃሳብ የእርሱ እንዲሆን ይፈልጋል፡፡ ምንም ከመወሰናችን በፊት እርሱን አስበን እንድንወስን ይፈልጋል፡፡ በህይወታችን የእርሱን ሃሳብ ከሌላ  ሃሳብ በፊት እንድናስቀድመው ይፈልጋል፡፡
እግዚአብሄር በፍፁም ሃይላችን እንድንወደው ይፈልጋል፡፡ ባለን ጉልበት ሁሉ እንድናስደስተው ፣ ባለን ጉልበት ሁሉ እንድንከተለው ፣ ባለን ጉልበት ሁሉ ካለምንም ቁጠባና መሰሰት ለእርሱ እንድንኖርለት ይፈልጋል፡፡
ይህን ስናነብ "ይህ ይቻላል?" ብለን ልንጠይቅ እንችላለን፡፡ መልሱ ይቻላል ነው፡፡ እግዚአብሄር ካዘዘው ይቻላል ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄር ከጠየቀው ይቻላል ማለት ነው ምክኒያቱም እግዚአብሄር የማይቻል ነገር ለአፉ ጠይቆ አያውቅም፡፡  
ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ፦ እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፥ አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ የምትል ናት። ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ማርቆስ 12፡29-30
 ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ፍቅር #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #ቸርነት #በፍፁምልብ #በፍፁምሃሳብ #በፍፁምነፍስ #በፍፁምሃይል #መውደድ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Friday, February 24, 2017

የድንጋይ ልብ

ወንድሞች ሆይ፥ ምናልባት ሕያው እግዚአብሔርን የሚያስክዳችሁ ክፉና የማያምን ልብ ከእናንተ በአንዳችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፤ ዕብራውያን 312
ልብ በጣም ወሳኙ የሁለንተናችን ማእከላዊ ክፍል ነው፡፡ ልብ ከጠነከረ ሁሉም ነገር ይጠነክራል፡፡ ልብ ከሳሳ ደግሞ ሁሉም ነገር ይሳሳል፡፡ ልብ እግዚአብሄርን ማመን ካቃተው ነገር ሁሉ ይበላሻል፡፡ እግዚአብሄርን የሚታመን ስስ የስጋ ልብ ካለን ደግሞ ሁሉም ነገር የሰመረ ይሆናል፡፡  
ስለዚህ ነው ኢየሱስን ስንቀበል ልባችን የሚለወጠውና የድንጋይ ልባችን በስጋ ልብ የሚተካው፡፡ ጭካኔን ትተን ርህራሄን የምንለብሰው ፣ ጭለማን ገፍፈን ብርሃንን የምንታጠቀው ፣ ጥላቻን ትተን ፍቅርን የምንለማመደው ልባችን በጌታ በመለወጡ ነው፡፡  የድንጋይ ልብ ደግሞ የሚባለው ለእግዚአብሄር ነገር ምንም ቅናት የሌለው ፣ እሳቱ የጠፋበት ፣ ለእግዚአብሄር ነገር ግድ የሌለው እምነቱ የጠፋበት በጥርጥር የተሞላ ልብ ነው፡፡ ልበ ጠንካራ ሰው ትሁት መሆን ያቃተው ፣ አንገተ ደንዳና ፣ ለእግዚአብሄር እሺ የማይልና ለቃሉ የማይንቀጠቀጥ የእልከኛ ሰው ልብ ነው፡፡
ዛሬ ድምፁን ብትሰሙት ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ በፊት እንደ ተባለ፥ ይህን ከሚያህል ዘመን በኋላ በዳዊት ሲናገር፦ ዛሬ ብሎ አንድ ቀን እንደ ገና ይቀጥራል። ዕብራውያን 4፡7
የህይወት መውጫ ከእርሱ ዘንድ ነውና ልብንህን ጠብቅ ብሎ መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምረናል፡፡  
አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፥ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና። ምሳሌ 4፡23
ልባችንን እንዴት እንድንጠብቅ መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡ ልባችንን የምንጠብቅበት መንገድ እለት በእለት በመትጋተ መሆኑን የእግዚአብሄር ቃል ያስተምረናል፡፡
ልቡን አለመጠበቅ ያለበት ሰው የለም፡፡ ማንም ሰው ከዚህ አደጋ ነፃ አይደለም፡፡ ከክፉና እልከኛ ልብ የምንድነው እለት በእለት በትጋት ስንሰበሰብና ስንመካከር ብቻ ነው፡፡ ማንም እኔ ይሄ አይነካኝም በሚል አጉል ትምክት በእያንዳንዱ ቀን በእግዚአብሄር ቃል መመካከሩን ቸል ቢል ሳያውቀው ክፉና እግዚአብሄርን የሚያስክድ ልብ ይኖረዋል፡፡
ወንድሞች ሆይ፥ ምናልባት ሕያው እግዚአብሔርን የሚያስክዳችሁ ክፉና የማያምን ልብ ከእናንተ በአንዳችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፤ ነገር ግን ከእናንተ ማንም በኃጢአት መታለል እልከኛ እንዳይሆን፥ ዛሬ ተብሎ ሲጠራ ሳለ፥ በእያንዳንዱ ቀን እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ፤  ዕብራውያን 3፡12-13
እግዚአብሄርን የሚያምን ፣ ለእግዚአብሄር ቃል ስስ የሆነ ፣ የዋህና የስጋን ልብ ለመጠበቅ ትጋት ይጠይቃል፡፡ አጥብቀን እንጂ በቸልታና በስንፍና ልባችንን አንጠብቅም፡፡ ልባችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ተለውጧል ፡፡ ያንን የተለወጠ የስጋ ልብ ፣ የሚያምን ልብ መጠበቅ ግን የእየለቱ ትጋታችንን ይጠይቃል፡፡
ይህንን ፅሁፍ ሼር ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ተመካከሩ #ከሃዲ #እልከኛ #ልብ #ቃል #ምስጉን #ሃሳብ #ማሰላሰል #ወንጌል #ደቀመዝሙር #ኢየሱስ #ጌታ #መዳን #አማርኛ #ኢትዮጲያ #አቢይዋቁማ #ፌስቡክ #አዋጅ

ከሃጢያት አለመመለስ እንጂ ሃጢያት ሰውን ከእግዚአብሄር ሊያቆራርጠው አይችልም

ሃጢያት በእግዚአብሄር ዘንድ አፀያፊ ነገር ነው፡፡ ሃጢያት ቀልድ አይደለም፡፡ ሃጢያት ሰውን ከእግዚአብሄር የለያየ ከባድ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ከባድ የሆነ አመፅ እንኳን ሰውን ከእግዚአብሄር እንዲለየው እግዚአብሄር አይፈልግም፡፡
እግዚአብሄር በሰው ላይ ያለው አላማ ፍቅር ነው፡፡ ሰው በሃጢያቱ እንዲሞት እግዚአብሄር አይፈልግም፡፡ የእግዚአብሄር ፍላጎት ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና ከእግዚአብሄር ጋር ያላቸው ህብረት እንዲታደስ ነው፡፡
ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው። 1 ጢሞቴዎስ 2፡3-4
ለሰው ካለው ፍቅር የተነሳ ሃጢያት ከሰው ጋር ያለውን ህብረትን አበላሽቶት እንዳይቀር እግዚአብሄር እቅድን አዘጋጅቷል፡፡ ሰው ንስሃ ከገባ ሃሳቡንና መንገዱን ከቀየረ ሃጢያት ሰውን ከእግዚአብሄር ሊያቆራርጠው አይችልም፡፡ እግዚአብሄር ሃጢያት በመስራታችን ሳይሆን በመመለሳችን ደስ ይሰኛል፡፡ በሃጢያታችን ስናዝንና ስንመለስ እግዚአብሄር ይረካል፡፡    
በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው። 1ኛ ዮሐንስ 1፡9
እግዚአብሄር የኢየሱስ ደም እንዲፈስና ያደረገው በሃጢያት ምክኒያት ነው፡፡ ስለዚህ ነው የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከሃጢያት ሁሉ የሚያነፃው፡፡ ስለዚህ ነው ሰው በማንኛውም ሃጢያት ውስጥ ቢገኝና ከእግዚአብሄር ጋር ያለው ህብረት ቢበላሽ በኢየሱስ ደም በኩል ተመልሶ ወደ ህብረቱ መግባት የሚችለው፡፡  
ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ በብርሃን ብንመላለስ ለእያንዳንዳችን ኅብረት አለን፥ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል። 1ኛ ዮሐንስ 1፡7
ሰው ንስሃ አለመግባቱ ፣ አለመመለሱና በሃጢያት መቀጠሉ እንጂ ሃጢያት መስራቱ ብቻ ሰውን ከእግዚአብሄር ለዘላለም ሊያቆራርጠው አይችልም፡፡ እግዚአብሄር ያዘጋጀውን የመዳኛ መንገድ አለመቀበሉና መጣሉ እንጂ ሃጢያቱ ከእግዚአብሄር ለዘላለም አይለየውም፡፡
ሃጢያት ሰውን ለዘላለም ከእግዚአብሄር የሚለይ ቢሆን ኖሮ ሁላችን ለዘላለም ከእግዚአብሄር በተለየን ነበር፡፡ እኛ ለዘላለም ከእግዚአብሄር እንዳንለያይ እግዚአብሄር በንስሃና መንገድን በመለወጥ ከእግዚአብሄር ጋር ያለን ግንኙነት እንዲታደስ አስቻለን፡፡ አሁንም ማንም የዘላለም ፍርድ ቢያገኘው ከሃጢያቱ ስላልተመለሰ ብቻ ነው፡፡  
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እምነት #ንስሃ #መመለስ #ሃጢያት #ይቅርታ #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #መናዘዝ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

Thursday, February 23, 2017

ሰማይ በጨረፍታ

10-11 በመንፈስም ወደ ታላቅና ወደ ረጅም ተራራ ወሰደኝ፥ የእግዚአብሔርም ክብር ያለባትን ቅድስቲቱን ከተማ ኢየሩሳሌምን ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አሳየኝ፤ ብርሃንዋም እጅግ እንደ ከበረ ድንጋይ እንደ ኢያሰጲድ ድንጋይ ሆኖ እንደ ብርሌ የጠራ ነበረ፤
12 ታላቅና ረጅም ቅጥር ነበራት፥ አሥራ ሁለትም ደጆች ነበሩአት በደጆቹም አሥራ ሁለት መላእክት ቆሙ፥ የአሥራ ሁለቱም የእስራኤል ልጆች ነገዶች ስሞች ተጽፈውባቸው ነበር።
13 በምሥራቅ ሦስት ደጆች፥ በሰሜንም ሦስት ደጆች፥ በደቡብም ሦስት ደጆች፥ በምዕራብም ሦስት ደጆች ነበሩ።
14 ለከተማይቱም ቅጥር አሥራ ሁለት መሠረቶች ነበሩአት፥ በእነርሱም ውስጥ የአሥራ ሁለቱ የበጉ ሐዋርያት ስሞች ተጽፈው ነበር።
15 የተናገረኝም ከተማይቱንና ደጆችዋን ቅጥርዋንም ይለካ ዘንድ የወርቅ ዘንግ ነበረው።
16 ከተማይቱም አራት ማዕዘን ነበራት፥ ርዝመትዋም እንደ ስፋትዋ ልክ ነበረ። ከተማይቱንም በዘንግ ለካት አሥራ ሁለትም ሺህ ምዕራፍ ሆነች፤ ርዝመትዋና ስፋትዋ ከፍታዋም ትክክል ነው።
17 ቅጥርዋንም ለካ፥ መቶ አርባ አራት ክንድ በሰው ልክ፥ እርሱም በመልአክ ልክ።
18 ቅጥርዋም ከኢያሰጲድ የተሠራ ነበረ፥ ከተማይቱም ጥሩ ብርጭቆ የሚመስል ጥሩ ወርቅ ነበረች።
19 የከተማይቱም ቅጥር መሠረት በከበረ ድንጋይ ሁሉ ተጌጦ ነበር፤ ፊተኛው መሠረት ኢያሰጲድ፥ ሁለተኛው ሰንፔር፥ ሦስተኛው ኬልቄዶን፥ አራተኛው መረግድ፥
20 አምስተኛው ሰርዶንክስ፥ ስድስተኛው ሰርድዮን፥ ሰባተኛው ክርስቲሎቤ፥ ስምንተኛው ቢረሌ፥ ዘጠነኛው ወራውሬ፥ አሥረኛው ክርስጵራስስ፥ አሥራ አንደኛው ያክንት፥ አሥራ ሁለተኛው አሜቴስጢኖስ ነበረ።
21 አሥራ ሁለቱም ደጆች አሥራ ሁለት ዕንቆች ነበሩ፤ እየአንዳንዱ ደጅ ከአንድ ዕንቍ የተሠራ ነበረ። የከተማይቱም አደባባይ ጥሩ ብርጭቆ የሚመስል ጥሩ ወርቅ ነበረ።
22 ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክና በጉ መቅደስዋ ናቸውና መቅደስ በእርስዋ ዘንድ አላየሁም።
23 ለከተማይቱም የእግዚአብሔር ክብር ስለሚያበራላት መብራትዋም በጉ ስለ ሆነ፥ ፀሐይ ወይም ጨረቃ እንዲያበሩላት አያስፈልጓትም ነበር።
24 አሕዛብም በብርሃንዋ ይመላለሳሉ፥ የምድርም ነገሥታት ክብራቸውን ወደ እርስዋ ያመጣሉ፤
25 በዚያም ሌሊት ስለሌለ ደጆችዋ በቀን ከቶ አይዘጉም፥
26 የአሕዛብንም ግርማና ክብር ወደ እርስዋ ያመጣሉ።
27 ለበጉም በሆነው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት በቀር፥ ጸያፍ ነገር ሁሉ ርኵሰትና ውሸትም የሚያደርግ ወደ እርስዋ ከቶ አይገባም።
ራእይ 21፡10-27
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#እምነት #ማየት #ሰማይ #ወርቅ #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #ተስፋ #እንቁ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

Tuesday, February 21, 2017

የእምነት ብቸኛው መንገድ

በአይን ከማይታየው መንፈስ ከሆነው ከእግዚአብሄር ጋር ላለን ግንኙነት እምነት በጣም ወሳኝ ነው፡፡ እግዚአብሄርን ለመድረስና ከእግዚአብሄር ለመቀበል የእምነት እጅ ይጠይቃል፡፡ እግዚአብሄርን ለማየት የእምነት እይታ ይጠይቃል፡፡ በአጠቃላይ እግዚአብሄርን ለማስደሰትና ከእግዚአብሄር ጋር ያለው ግንኙነታችን እንዲሰምር እምነት ይጠይቃል፡፡ እንዲያውም ካለእምነት እግዚአብሄርን ማስደሰት አይቻልም፡፡
ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ዕብራውያን 11፡6
ታዲያ እምነትን የምናገኘው እንዴት ነው? እምነት እንዴት ይመጣል? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ብልህነት ነው፡፡
ከእግዚአብሄር ፈቃድ ውጭ እምነት የማይታሰብ ነው፡፡ እምነት ይኖረን ዘንድ መጀመሪያ ስለ ሁኔታችን የእግዚአብሄር ቃል የሚለውን ማግኘት ግዴታ ነው፡፡ እምነት የሚገኘው የእግዚአብሄር ፈቃድ ሲገኝ ብቻ ነው፡፡ እምነት የሚመጣው በእግዚአብሄር ቃል መረዳት ብቻ ነው፡፡
እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው። ሮሜ 10፡17
ከእምነት ጉዞ የሚቀድመው ዋንኛው ነገር የእግዚአብሄርን ፈቃድ ከቃሉ ፈልጎ ማግኘት ነው፡፡ እምነት የሚያመጣውን ቃሉን መስማትና መረዳት ነው፡፡
በእምነት ለመኖር በእግዚአብሄር ቃል መኖር አለብን፡፡ እግዚአብሄርን ለመስማትና ለማመን ቃሉን መስማት አለብን፡፡  
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እምነት #ማየት #አለማየት #ቃል #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #እወጃ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

Monday, February 20, 2017

እምነት እግዚአብሄርን ደስ የሚያሰኝበት ምክኒያት

እምነት በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ምክኒያቱም እግዚአብሄርን ማስደሰተ የምንችለው በእምነት ስንኖር ብቻ ነው፡፡ እምነታችን እግዚአብሄርን ያስደስተዋል፡፡ ካለ እምነት ደግሞ እግዚአብሄርን ለማስደሰት መሞከር ሞኝነት ነው፡፡
ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ዕብራውያን 11፡6
ይህ እግዚአብሄርን ደስ የሚያሰኘው ነገር ምንድነው? እግዚአብሄርን ደስ ያሰኘበት የእምነት ባህሪ መረዳት እግዚአብሄርን በምንም ሁኔታ ውስጥ ለማመን ይረዳናል፡፡  
እምነት በተስፋ ስለሚኖር ነው
ሁሉም ሰው በአይን በሚታይ ነገር ሲኖር እምነት ግን የሚኖረው በአይን ከሚታይ ነገር ከፍ ብሎ ነው፡፡ እምነት እግዚአብሄርን የሚያስደስትበት ምክኒያት እምነት በተስፋ እንጂ የሚኖረው በአይን በሚታይ ነገር አይደለም፡፡ እምነት የሚኖረው በአይን ከሚታየው ክልል አልፎ ነው፡፡  እምነት የሚኖረው በተስፋ ነው፡፡ እምነት የእግዚአብሄርን ቃል ብቻ ተስፋ አድርጎ ይኖራል፡፡
በተስፋ ድነናልና፤ ነገር ግን ተስፋ የሚደረግበቱ ነገር ቢታይ ተስፋ አይደለም፤ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? የማናየውን ግን ተስፋ ብናደርገው በትዕግሥት እንጠባበቃለን። ሮሜ 8፡24-25
እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው። ዕብራውያን 11፡1
እምነት እግዚአብሄርን የሚያስደስትበት ምክኒያቱ እምነት የማይታይን ነገር የሚያይ ስለሆነ ነው፡፡ እምነት የሚያየው የማይታየውን የእግዚአብሄርን ቃል ብቻ ነው፡፡ እምነት የሚሰማይ የእግዚአብሄርን ቃል ብቻ ነው፡፡ እምነት የሚያምነው የማይታየውን እግዚአብሄርን ነው፡፡   
በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም እግዚአብሔርን በጥበብዋ ስላላወቀች፥ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአልና። 1ኛ ቆሮንቶስ 1፡21
እምነት ከሚታየው ይልቅ የማይታየውን ስለሚያስበልጥ ነው
እምነት እግዚአብሄርን የሚያስደስትበት ሌላው ምክኒያት እምነት የሚታየውን ስለማያይ የማይታየውን ስለሚያይ ነው፡፡ እምነት የሚያየው እግዚአብሄር በቃሉ ያለውን የማይታየውን ነው፡፡ እምነት ልቡን የሚጥለው እግዚአብሄር በተናገረው ነገር ላይ ነው፡፡ እምነት የሚከተለው ቃሉን ነው፡፡
እንግዲህ ሁልጊዜ ታምነን፥ በእምነት እንጂ በማየት አንመላለስምና በሥጋ ስናድር ከጌታ ተለይተን በስደት እንዳለን የምናውቅ ከሆንን፥ 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡6-7
እምነት የሚታየውን ስለማያይ ነው
እምነት እግዚአብሄርን የሚያስደስትበት ምክኒያቱ እምነት ከቃሉ ጋር የማይስማማውንም ማንኛውም ሁኔታ አለማየቱ ነው፡፡ እምነት በአካባበው ያሉትን ጊዜያዊ ሁኔዎች አያይም፡፡ እምነት በዙሪያው የከበቡትን ገጠመኞች አያይም፡፡ እምነት በአካባቢው ከሚጮኸው ሁኔታ በላይ በልቡ የሚያሾከሽከውን የእግዚአብሄርን ቃል ያምናል፡፡ እምነት የሚታየውን ሁኔታ አይከተለም፡፡ እምነት እንደሁኔታው እና እነደጊዜው አይራመድም፡፡
ዘርህ እንዲሁ ሊሆን ነው እንደ ተባለ፥ ተስፋ ባልሆነው ጊዜ የብዙ አሕዛብ አባት እንዲሆን ተስፋ ይዞ አመነ። የመቶ ዓመትም ሽማግሌ ስለ ሆነ እንደ ምውት የሆነውን የራሱን ሥጋና የሳራ ማኅፀን ምውት መሆኑን በእምነቱ ሳይደክም ተመለከተ፤ ሮሜ 4፡18-19
የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፥ 2ኛ ቆሮንቶስ 4፡17-18
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እምነት #ማየት #አለማየት #ቃል #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #ተስፋ #እወጃ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ