Popular Posts

Sunday, December 31, 2017

ለአመፅ አታቅርቡ ለፅድቅ አቅርቡ

ብልቶቻችሁንም የዓመፃ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለኃጢአት አታቅርቡ፥ ነገር ግን ከሙታን ተለይታችሁ በሕይወት እንደምትኖሩ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፥ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ። ሮሜ 6፡13
ብልቶቻችን ከአመፃም ከፅቅድቅም ገለልተኛ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ብልቶቻችን ወይ አመፃ ያልፍባቸዋል ወይ ፅድቅ ያልፍባቸዋል፡፡ ብልቶቻችን ፅድቅ ካለፈባቸው ሁለት ነገር ባንዴ ሊያልፍባቸው ስለማይችል አመፃ ሊያልፍባቸው አይችልም፡፡
ከብርጭቆ ውስጥ ውሃውን ካወጣነው ከመቀፅበት በአይን የማይታይ አየር ብርጭቆውን ይሞላል፡፡ ውሃም አየርም የሌለው ገለልተኛ ሊሆን አይችልም፡፡
አንድ ነገርን ላለማድርግ አንድ ነገርን ማድረግ ወሳኝ ነው፡፡ ብልቶቻችንን የአመፃ የጦር እቃ አድርጎ ላለማቅረብ ከምንታገል ይልቅ ብልቶቻችንን የፅድቅ የጦር እቃ አድርጎ ማቅረብ ከመቀፅበት የአመፃ የጦር እቃ እንዳይሆኑ ውጤታማ ያደርገናል፡፡  
ፅቅድ ያለፈበባቸው ብልቶቻችን አብሮ አመፃ ሊያልፍባቸው አይችልም፡፡
ስለዚህ አመፃ እንዳያልፍበት ከፈለግን በጊዜ በፅድቅ ቦታ ማስያዝ አለብን፡፡ በፅድቅ ቦታውን የያዘ ብልት ለአመፃ ትርፍ ቦታ የለውም፡፡  
የውሃ ማስተላለፊያን ቧንቧ ሙቅ ውሃ ካስተላለፈ ቀዝቃዛ ውሃ ለማስተላለፍ ቦታ እንደማይቀረው ሁሉ መንፈሳዊም ነገር እንዲሁ ነው፡፡ በእለት ተእለት ህይወታችን የእግዚአብሄር ቃል የሚለውን በማድረግ የእግዚአብሄር ቃል የማይለውን አለማድርግ እንችላለን፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል በመታዘዝ አለመታዘዝን እንበቀላለን፡፡
መታዘዛችሁም በተፈጸመች ጊዜ አለመታዘዝን ሁሉ ልንበቀል ተዘጋጅተናል። 2ኛ ቆሮንቶስ 10፡6
ሰው ብልቶቹን የአመፃ መጠቀሚያ አድርጎ ላለማቅረብ ከአመፃ ጋር ከመጋደል ይልቅ የፅድቅ መጠቀሚያ ማድረግ በተዘዋዋሪ ውጤታማ ያደገዋል፡፡ ሰው ብልቶቹን የአመፃ የጦር እቃ አድርጎ ላለማቅረብ የሚያዋው አስቀድሞ የፅድቅ የጦር እቃ አድርጎ ማቅረብ ነው፡፡
ብልቶቹን የፅድቅ የጦር እቃ አድርጎ ያቀረበ ሰው ብልቶቹ የአመፃ የጦር እቃ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ብልቶቹ የፅድቅ የጦር እቃ ያልሆኑ ሰው ግን ወደደም ጠላም ብልቶቹ የአመፃ የጦር እቃ ላይሆኑ አይችሉም፡፡  
ሰው ራሱን ለሃጢያት ለመስጠት አስቀድሞ ራሱን ለፅድቅ መስጠት አለበት፡፡ ሰው ራሱን ለፅድቅ ሳይሰጥ ለሃጢያት አልስጥ ብሎ ቢመኝ አይሆንም፡፡ ሰው ወይ የፅድቅ መጠቀሚያ ይሆናል ወይም ደግሞ የሃጢያት መጠቀሚያ ይሆናል፡፡ ሰው ከፅድቅና ከሃጢያት መጠቀሚያነት ገለግልተኛ ሊሆን አይችልም፡፡
ሰው እግዚአብሄርን ለማስደሰት የእግዚአብሄርን ቃል ማንበብና ማሰላለስ በእግዚአብሄር ቃል አእምሮውን ማደስ አለበት፡፡
የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። ሮሜ 12፡2
ሰው ግን በእግዚአብሄር ቃል አእምሮውን ለማደስ ራሱን ካልሰጠ የሰይጣንን ሃሳብ አላስተናግድም ብሎ ቢፍጨረጨር አይችልም፡፡ ሰው አእምሮው በእግዚአብሄር ቃል ካልተሞላ ወደደም ጠላም ከእግዚአብሄር ቃል ውጭ በሆነ ነገር ይሞላል፡፡
ሰው ራሱን ለእግዚአብሄር ጥበብ ካልሰጠና የእግዚአብሄርን ጥበብ ካልፈለገ ወደደም ጠላም የምድርን ጥበብ ሲያስተናገድ ይኖራል፡፡
ይህ ጥበብ ከላይ የሚወርድ አይደለም፤ ነገር ግን የምድር ነው፥ የሥጋም ነው፥ የአጋንንትም ነው፤ ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ስራ ሁሉ አሉና። ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፥ በኋላም ታራቂ፥ ገር፥ እሺ ባይ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት፥ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት። ያዕቆብ 3፡15-17
ሰው እግዚአብሄርን ለማገልገል ራሱን ካልለየ አለምንና ሰይጣንን ያገለግላል፡፡ ሰው እግዚአብሄርን ካልወደደ አለምን ይወዳል፡፡ ሰው አለምን ላለመውደድ ከሚፍጨረጠጨር ይልቅ እግዚአብሄርን ቢወድ ፍሬያማ ይሆናል፡፡
ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም። 1ኛ ዮሃንስ 2፡15-16
ብልቶቻችሁንም የዓመፃ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለኃጢአት አታቅርቡ፥ ነገር ግን ከሙታን ተለይታችሁ በሕይወት እንደምትኖሩ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፥ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ። ሮሜ 6፡13
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #የዓመፃየጦርዕቃ #የጽድቅየጦርዕቃ  #አቅርቡ #አታቅርቡ #መናገር #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ቃል #መዳን #ማድረግ #መስዋእት #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Saturday, December 30, 2017

ለነገ (ለሚመጣው አመት) አትጨነቁ

ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል። ማቴዎስ 6፡34
በጌታ ለመኖርና ኢየሱስን ለመከተል እያንዳንዱ ቀን ተግዳሮት አለው፡፡ እያንዳንዱ ቀን የሚመጣው ከተወሰነ ተግዳሮት ጋር ነው፡፡ ይብዛም ይነስም ተግዳሮት ይዞ የማይመጣ ቀን የለም፡፡ ሁሉም ቀን የሚመጣው የራሱ የተግዳሮት ድርሻን ይዞ ነው፡፡
ቀን ይዞ ለሚመጣው ተግዳሮት የሚመጥን ፀጋ በቀን ውስጥ ይለቀቃል፡፡ ለእያንዳንዱ ቀን ተግዳሮት የሚበቃ የእግዚአብሄር ፀጋ በእያንዳንዱ ቀን ውስጥ አለ፡፡ እያንዳንዱ ቀን የራሱ ድርሻ ተግዳሮትና ለዚያ ተግዳሮት የሚበቃ የራሱ ድርሻ የሚያስችል ሃይል አለው፡፡
በነገ ውስጥ የሚለቀቀውን ፀጋ ዛሬ ማየትና መለማመድ አንችልም፡፡ ወይም ዛሬ ላይ ቆመን ነገር መኖር ወይም ማስተካካል ወይም ደህና ማድረግ አንችልም፡፡ በዛሬ የሚለቀቀው የሚያስችል የእግዚአብሄር ሃይልን የምንለማመደው በዛሬ ውስጥ ያለውን ተግዳሮት ለማለፍ ብቻ ነው፡፡
ሰው የነገን ተግዳሮት በዛሬ ፀጋ ሊጋፈጠው በመሞከር ይጨነቃል፡፡ የዛሬን ተግዳሮት ብቻ ለመኖር ከነገ ተግዳሮት ጋር ላለመቀላቀል  መረጋጋት ይጠይቃል፡፡ የዛሬን ተግዳሮት በዛሬ ፀጋ ተወጣውና ለጥ በል፡፡ ስለነገ አትጨነቅ፡፡ ስለነገ ባልተለቀቀ ፀጋ ውስጥ ሆነህ ስነገ መጨነቅ ከንቱ ነው፡፡  ስለነገ ለማሰብ ትክክለኛው ጊዜ ነገ ነው፡፡ ነገ ላይ ተግዳሮቱም ይታወቃል ፀጋውም ይገለጣል፡፡ ነገ ላይ ስለነገ ማሰብ ውጤታማ እቅድ ነው፡፡ ዛሬ ላይ ስለነገ መጨነቅ ብክነት ነው፡፡
ነገ የሚመጣው በሬሱ ጊዜ ነው፡፡ ነገ የሚመጣው ከራሱ ተግዳሮትና ከራሱ ፀጋ ጋር ነው፡፡ ነገ ሲመጣ ለነገ የሚሆን እምነት አብሮት ይመጣል፡፡ ነገ ሲሆን ለነገ ተግዳሮት የሚሆን ፀጋ ይለቀቃል፡፡ ለዚያም ነው ብዙ ጊዜ የተጨነቅንበት ነገር ጊዜው ሲደርስ ሸክሙ የሚበነው፡፡
እምነት ግን መጥቶአልና ከእንግዲህ ወዲህ ከሞግዚት በታች አይደለንም። ገላትያ 3፡25
ስለነገ ማድረግ የምትችለው አንድ ነገር የሚያስጨንቅህን በጌታ ላይ መጣል ብቻ ነው፡፡ ስለነገ የሚያስጨንቅህን በእርሱ በእግዚአብሄር ላይ ከመጣል ውጪ ውጤታማ ነገር የለም፡፡ አባታችን እግዚአብሄር አንደሆነ እንደ እኛ የታደለና መጨነቅ የሌለበት ሰው የለም፡፡
ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል። ማቴዎስ 6፡34
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ጭንቀት #ነገ #ማረፍ #ጣሉ #ክፋት #ፀጋ #ምናን ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

ከፀሐይም በታች አዲስ ነገር የለም

የሆነው ነገር እርሱ የሚሆን ነው፥ የተደረገውም ነገር እርሱ የሚደረግ ነው፤ ከፀሐይም በታች አዲስ ነገር የለም። መክብብ 1፡9
በምድር ላይ ቢሆንልኝ ብለን እጅግ ስንመኘው የነበረ ስናገኘው ለዚህ ነው እንደዚህ የሆንኩት ብለናል፡፡ በምድር ላይ እንደተራራ ገዝፎብን የነበረ ነገር ስንደርስበት ትንሽነቱ አስገርሞናል፡፡ በምድር ላይ ስንናፍቀው የነበረ ስናገኘው ሰልችቶናል፡፡ በምድር ላይ እንደ አድማስ ርቆብን የነበረ ነገር ስንቀርበው ምንም አዲስነት አላገኘንበትም፡፡ እደርስበት ይሆን ብለን እጅግ የፈለግነው ውይ ይሄ ነው እንዴ ብለናል፡፡
በምድር ላይ ብናገኘው ህይወታችን ይለወጣል ብለን አስበን የነበረው ነገር ህይወታችንንን ሊለውጥ ሳይችልና ሲቀር ቅር ሲያሰኘን ምስክር ሆነናል፡፡
በምድር ላይ ይህ ያላቸው ሰዎች የታደሉ ናቸው ብለን ያሰብናቸው ሰዎች ያገኙትን ስናገኝ ቀድሞ እንዳስብነው እንዳልታደሉ ደርሰንበታል፡፡ አሁንም ሰዎች እኛ ፈልገን ስናገኘው የተሰናከልንበትን ነገር እጅግ ሲፈልጉ ስናይ ይህ የተሳተ ግምታቸው ነግሩን ባገኙት ጊዜ ቅር እንደሚያሰኛቸው ስለምናውቅ እናዝናላቸዋለን፡፡
በምድር ላይ አንዲህ ብሆን እኮ ብለን የተመኘነውን ስንሆን ወዲያው ረስተነው አሁን ደግሞ ፍላጎታችን እጅግ የተለየ ሆኗል፡፡
ከሰማይት በታች አዲስ ነገር የለም፡፡ አዲስ ነገር ያለ ከመሰለን ስላልደረስንበት ብቻ ነው፡፡ የደረሱበት ምንም አዲስ ነገር እንደሌለ እንደተረዱት ስንደርስነበት ምንም አዲስ ነገር እንደሌለ ይገባናል፡፡ ውይ እነርሱን ባደረገኝ የምንላቸው ሰዎች ከዚህ መቼ በወጣሁ ብለው ሲመኙ ደርሰናል፡፡
ብቻኛው አዲሱ ነገር የእግዚአብሄርን ስራ በምድር ላይ ሰርቶ እግዚአብሄርን በህይወታችንና በአገልግሎታችን ማክበር ነው፡፡
እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርሁህ፤ ዮሃንስ 17፡4
ብቸኛው አዲሱ ነገር ሰውን መውደድ ፣ ሰውን ማገልገል ፣ ሰውን መጥቀምና ሰውን ማንሳት ነው፡፡
በምድር ላይ አዲሱ ነገር በዘላለማዊ እይታ የምድር ህይወትን እንደ እንግድነት መኖር ብቻ ነው፡፡ አዲሱ ነገር በምድር ላይ እንደ እግዚአብሄር መልክተኛ ፈቃዱን ፈፅሞ ማለፍ ብቻ ነው፡፡ በምድር ላይ አዲሱ ነገር በሰማይ መዝገብን መሰብሰብ ነው፡፡
ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ፤ ማቴዎስ 6፡19-20
በምድር አዲሱ ነገር በዘላለማዊ ሽልማትን እንደሚቀበል ራስን መግዛት ነው፡፡ በምድር አዲሱ ነገር በምድር ገንዘብ የዘላለም ወዳጆችን ማፍራት ነው፡፡
እኔም እላችኋለሁ፥ የዓመፃ ገንዘብ ሲያልቅ በዘላለም ቤቶች እንዲቀበሉአችሁ፥ በእርሱ ወዳጆችን ለራሳችሁ አድርጉ። ሉቃስ 16፡9
ብቸኛው አዲስ ነገር በምድር ለሚቀር ዘላለማዊ ላልሆነ ለጊዜያዊ መብል አለመስራትና ዘላለማዊ ለሆነ ለማይጠፋ መብል መስራት ነው፡፡
ለሚጠፋ መብል አትሥሩ፤ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ፤ እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና። ዮሃንስ 6፡27
ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል። 1ኛ ዮሃንስ 2፡17
አዲሱ ነገር ጌታ ኢየሱስ ብቻ ነው፡፡ አዲሱ ነገር ከጌታ ጋር መኖር ነው፡፡ አዲሱ ነገር ጌታን መውደድ ነው፡፡ አዲሱ ነገር ጌታን ኢየሱስን መከተል ብቻ ነው፡፡ ዘመን የማይሽረው አዲሱ ነገር ጌታን መውደድ ጌታን መከተል ጌታን ማገልገል ብቻ ነው፡፡ 
ከላይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ ከምድር የሚሆነው የምድር ነው የምድሩንም ይናገራል። ከሰማይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው። ዮሃንስ 331
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ዘላለማዊ #አዲስ #ልብ #ሰማይ #ዘላለም #ጌታ #ከፀሐይበታች #ያልፋሉ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ወንጌል #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Friday, December 29, 2017

የእውነተኛ ውበት ሁለቱ መለኪያዎች

ለእናንተም ጠጕርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጎናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ። 1 ጴጥሮስ 3፡3-4
ውበታችሁ በውጫዊ ነገሮች በመሽሞንሞን ይኸውም ሹሩባ በመሠራት፣ በወርቅ በማጌጥና በልብስ አይሁን፤ ነገር ግን ውበታችሁ በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ፣ ገርና ጭምት መንፈስ ያለበት፣ ምንጊዜም የማይጠፋ የውስጥ ሰውነት ውበት ይሁን። 1ኛ ጴጥሮስ 3፡3-4 (አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
የውጭ ውበት መልካም ነው ዋጋም አለው፡፡ ነገር ግን ከውጭው ውበት ጋር ሲነፃፀር የውስጡ ውበት ዋጋው እጅግ የከበረ ነው፡፡
ከውስጡ ውበት አንፃር የውጭው ውበት ብዙ ዋጋ አያስከፍልም፡፡ ከውስጡ ውበት አንፃር የውጭው ውበት ባነሰ ጊዜና ጥረት ይገኛል፡፡
የውጪው ውበት ለሰው የእግዚአብሄር ስጦታ ሲሆን ማንም ሊመካበት የማይችል ውበት ነው፡፡ የውስጡ ውበት ግን የሰው ለእግዚአብሄር ስጦታና ሰውን የሚያስመሰግነው ውበት ነው፡፡ የውጭው ውበት ራስን በማስለመድ የሚመጣ መልካም ባህሪ ነው፡፡
እግዚአብሔርን ለመምሰል ግን ራስህን አስለምድ - 1ኛ ጢሞቲዮስ 4፡7
የውጭው ውበት አንዴ ተሰርተነው የምናስደንቅበት ሲሆን የውስጡ ውበት ግን የህይወትን ዘመን ሁሉ ትጋትን የሚጠይቅ ዘለቄታዊ ውበት ነው፡፡
ውበት ሐሰት ነው፥ ደም ግባትም ከንቱ ነው፤ እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን እርስዋ ትመሰገናለች። ምሳሌ 31፡30
የውጭው ውበት እግዚአብሄርን አያስደንቀውም የውስጡ ውበት ግን እግዚአብሄር ከሰው የሚፈልገው ስለሆነ እግዚአብሄርን ደስ ያሰኘዋል፡፡ የውጭው ውበት እንደ ዛፍ ቅጠል ሲሆን የውስጡ ፍሬ ግን እንደ ዛፍ ፍሬ ነው፡፡
የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው። ገላትያ 5፡22
የውስጡ ውበት የሚለካው ተለዋዋጭ በሆነው በገፅታ ሳይሆን በባህሪ ነው፡፡ የውስጡ ውበት የሚለካው በቅላት ሳይሆን በአመለካከት ነው፡፡ የውስጡ ውበት የሚለካው በርዝመት ሳይሆን በትግስት ነው፡፡ የውስጡ ውበት የሚለካው በቅጥነት ሳይሆን በትህትና ነው፡፡
የውስጥ ውበት የሚለካባቸውን እግዚአብሄር ከእያንዳንዳችን የሚፈልጋቸውን ሁለት ወሳኝ ባህሪያትን እንመልከት፡-
የዋህነት
የዋህነት ማለት ክፉን በክፉ ለመመለስ ሙሉ ሃይል ይዞ ነገር ግን ሃይልን ለክፋት ላለመጠቀም መወሰንና ራስን ማግዛት ነው፡፡
የዋህ ማለት ሞኝ ማለት ሳይሆን ክፋትን በክፋት ላለመመለስ ራሱን የሚገዛ ቁጥብ ሰው ማለት ነው፡፡ የዋህ ማለት ሃይል እንዳለው እያወቀ ሃይሉን ለክፋት ሳይሆን ለመልካምነት ብቻ ለመጠቀም የወሰነ ራሱን የሚገዛ ማለት ነው፡፡  
የዋሆች ብፁዓን ናቸው፥ ምድርን ይወርሳሉና። ማቴዎስ 5፡5
ዝግተኛነት
ዝግተኛ ማለት እግዚአብሄርን የማይቅድም ፣ እግዚአብሄርን የሚያስቀድም ፣ እግዚአብሄርን የሚከተል ፣ የእግዚአብሄርን እርምጃ የሚታገስና በእግዚአብሄር የሚመራ ሰው ማለት ነው፡፡ ዝግተኛ ወይም ጭምት ማለት በራሱ አነሳሽነት ድርሻዬ ነው ብሎ የፈለገውን የማይወስድ እግዚአብሄር ድርሻውን እስኪያሳየው የሚጠብቅ እግዚአብሄር ካላሳየው በራሱ ማስተዋል የማይደገፍ በራሱ የማይመራ ማለት ነው፡፡
በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ ምሳሌ 3፡5
ለእናንተም ጠጕርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጎናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ። 1 ጴጥሮስ 3፡3-4
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ባህሪ #ፍቅር #ልብ #የዋህ #ዝግተኛ #የመንፈስፍሬ #ውበት #የልብሰው #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ወንጌል #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Thursday, December 28, 2017

ከዚህ ዘመን ይልቅ ያለፈው ዘመን ለምን ተሻለ?

በምድር ስንኖር ኑሮን አንድናቆምና እጅ እንድንሰጥ ሊያስፈሩን የሚመጡ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ አንዳንድ ሰው ወጥቶ ህይወትን መጋፈጥ ሲፈራ ተኝቶ መዋል ያምረዋል፡፡ ሌላው ደግሞ ቶሎ ኢየሱስ እንደገና ተመልሶ ወይም እርሱ ወደ ሰማይ ሄዶ ችግርና መከራን ማምለጥ ይመኛል፡፡ ሰው በጌታ በኢየሱስ ያመነ ሰው ወደ ሰማይ የሚሄድበት ጊዜ አለው፡፡ ላሁን ግን የሚሰራ ስራ ስላለ በዚሁ ይቀመጣል፡፡
አንዳንዴ የሰዎችን ክፋት ስናይ ዘመኑ ያስፈራናል፡፡ እግዚአብሄር ግን የሚፈልገው በዚህ በእንግድነት አገር ታምነን እንድኖር ነው፡፡
በሰማይ የሚሸነፍ የምትቋቋመውቅ ጠላት ስለሌለ ማሸነፍ የሚባለውም ገድል የለም፡፡ ጌታ የሚፈልገው እዚሁ ጠላት ያለበት ኖረህ እንድታሸነፍ ነው፡፡ እዚሁ ጭለማ አህዛብን ድቅድቅ ጨለማ አህዛብን በሚሸፍንበት ምድር ነው ብርሃንህን ሊያወጣ የሚፈልገው፡፡ (ኢሳያስ 60፡1-2) እዚሁ በሞት ጥላ መካከል ነው አብሮህ መሆን የሚፈልገው፡፡ (መዝሙር 23፡4) እዚሁ በጠላቶችህ ፊት ለፊት ነው ራስህን በዘይት መቀባት የሚፈልገው፡፡ (መዝሙር 23፡3) እዚሁ ደረቁ ምድር ላይ መቶ እጥፍ እንድታፈራ የሚፈልገው፡፡ (ዘፍጥረት 26፡22) በምንም ነገር እጅ እንድትሰጥ ሳይሆን በጠበበው ደጅ ታግለህ እንድትገባ ነው የሚገፈልገው፡፡ (ማቴዎስ 7፡13) በትንሽ በትልቁ የሚያለቅስ ልፍስፍስ ሳይሆን ተናጣቂ ግፈኛ እንድትሆን ነው የሚፈልገው፡፡ (ማቴዎስ 11፡12)
ለዚህ ነው በምድር ተቀመጥ ታምነህ ተሰማራ ነው የሚለው፡፡
በእግዚአብሔር ታመን፥ መልካምንም አድርግ፥ በምድርም ተቀመጥ፥ ታምነህም ተሰማራ። መዝሙር 37፡3
ስለዚህ ነው የበፊቱን ያለፈውን ኑሮ አያሰብክ የወደፊቱ አይመርህ የሚለው፡፡ ምክኒያቱም እግዚአብሄር የሰጠህ ፀጋ ለዘመኑ ክፋት የሚበቃ ነው፡፡
እንደ ድሮ መንገድ ባይሆንም አሁንም ለጌታ የተሰጡ ሰዎች አሉ፡፡ እንደለመድከው ባይሆንም አሁንም ለጌታ መስዋእት የሚሆኑ ሰዎች አሉ፡፡ እንዳሰብከው ባይሆንም አሁንም ለጌታና ለጌታ ክብር ብቻ የሚኖሩ ሰዎች አሉ፡፡ እንደለመድነው ባይሆንም አሁንም ጌታን በሙሉ ልባቸው እያገለገሉ ያሉ ሰዎች አሉ፡፡  
እግዚአብሄር በዘመናት መካከል አይለወጥም፡፡ ዘመን ሊለወጥ ዘመን ሊከፋ ይችላል ነገር ግን የማይለወጠው እግዚአብሄር ዘመኑን ለእኛ መልካምነት ይሰራዋል፡፡
ባለፈው ዘመን መልካም ያደረገው እግዚአብሄር እንደሞተ ሁሉ ያለፈው ዘመን ለምን የተሻለ አትበል፡፡
ከዚህ ዘመን ይልቅ ያለፈው ዘመን ለምን ተሻለ? ብለህ አትናገር፤ የዚህን ነገር በጥበብ አትጠይቅምና። መክብብ 7፡9-10
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር  share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ  #ስብከት #መዳን #ዘመን #እምነት #ወንጌል #ማኅበረተኛ #ስብከት #ቃል #ዝራ #የምድርጨው #የአለምብርሃን #ተነሺ #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #እወጃ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

Wednesday, December 27, 2017

በወንጌልም ማኅበረተኛ እሆን ዘንድ

በወንጌልም ማኅበረተኛ እሆን ዘንድ ስለ ወንጌል ሁሉን አደርጋለሁ። 1ኛ ቆሮንቶስ 9፡23
ይህን ሁሉ የማደርገው፣ ከወንጌል በረከት እካፈል ዘንድ፣ ስለ ወንጌል ብዬ ነው።(አዲሱ መደበኛ ትርጉም) 1ኛ ቆሮንቶስ 9፡23
በአለም ላይ ሰዎች ከትልቅ ድርጅት ስለገዙት አክሲዮን ይናገራሉ፡፡ ሰዎች በአለም ላይ ስለገዙትና ስላላቸው ቦንድ በኩራት ይናገራሉ፡፡ ይህ ሁሉ ለምድር ይጠቅማል፡፡
ሰው ግን የታወቁ የምድር ማህበሮች ማህበርተኛ ሆኖ ነገር ግን በወንጌል ማህበርተኛ ካልሆነ ምስኪን ሰው ነው፡፡
የምድር ጉዟቸውን መልስ ብለው ሲያዩ ፎቅ አልሰራሁም ታዋቂ አልሆንኩም ውድ መኪና አልነዳሁም ነገር ግን በህይወቴ ዘመን ሁሉ ቤተክርስትያንን ደግፌያለሁ የሚሉ የተባረኩ ሰዎች አሉ፡፡
የምድር ጉዟቸውን መለስ ብለው ሲያዩ ተምሬ ዶክተር አልሆንኩም ነገር ግን ወንጌልን ለመስበክ ህይወቴን ሙሉ ሰጥቼያለሁ በማለት በህይወታቸው የሚረኩ ሰዎች አሉ፡፡
እኔም እላችኋለሁ፥ የዓመፃ ገንዘብ ሲያልቅ በዘላለም ቤቶች እንዲቀበሉአችሁ፥ በእርሱ ወዳጆችን ለራሳችሁ አድርጉ። ሉቃስ 16:9
አላገባሁም አልወለድኩም ነገር ግን በህይወቴ ሁሉ የእግዚአብሄርን ቤተክርስትያን የወንጌል ስራ ስደግፍ ኖሬያለሁ የሚሉ በሚገባ የተኖረ ህይወት የሚኖራቸው ሰዎች አሉ፡፡
በምድር ላይ የምንም ማህበር አባል ያልሆኑ የወንጌል ግን ማህበርተኛ ለመሆን ህይወታቸውን የሚያፈሱ ጉልበታቸውን ገንዘባቸውን እውቀታቸውን ጊዜያቸውን ለወንጌል ስራ የሚሰጡ የተባረኩ ሰዎች አሉ፡፡
አሁንም በ2018 ዓም ያዳነንን ወንጌል ማህበርተኛ ለመሆን የማይጠፋ የዘላለም ሽልማት ስለሚያስገኘው ስለወንጌል ሁሉንም ለማድረግ እንወስን ፡፡
በወንጌልም ማኅበረተኛ እሆን ዘንድ ስለ ወንጌል ሁሉን አደርጋለሁ። 1ኛ ቆሮንቶስ 9፡23
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እምነት #ወንጌል #ማኅበረተኛ #ስብከት #ቃል #ዝራ #የምድርጨው #የአለምብርሃን #የአመፃገንዘብ #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #እወጃ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

Tuesday, December 26, 2017

አንድነትን ለመጠበቅ የሚጠቅሙ ምክሮች

በአንድነት ውስጥ ብቻ የተቀመጠ ታላቅ እምቅ ጉልበት አለ፡፡ አንድነትን መፈለግ ጤነኝነት ነው፡፡ አንድነት ግን በምኞት ብቻ አይመጣም፡፡ አንድ ለመሆን በመፈለጋችን ብቻ አንድነት አይመጣም፡፡
አንድነት በእድል አይመጣም፡፡ አንድነት ከሌለን ስላልሰራንበት ነው እንጂ እድለኛ ስላልሆንን አይደለም፡፡ አንድ ከሆንን አንድ የሆነው የአንድነትን መንገድ ተረድተን በትጋት ስለሰራንበት እንጂ እድለኛ ስለሆንን አይደለም፡፡
አንድነት ቅፅበታዊ አይደለም፡፡ አንድነት ረጅም ቀጣይነት ያለው ትጋትን የሚጠይቅ ግብ እንጂ በቅፅበት የሚመጣ ነገር አይደለም፡፡
በአንድነት ውስጥ የታመቀ እጅግ ታላቅ ጉልበት አለ፡፡ ያንን ታላቅ ጉልበት መጠቀም የምንችለው በአንድነት ስንቆም ብቻ ነው፡፡ በአንድነት ውስጥ ያለውን ጥቅም ለመጠቀም ለአንድነት ትጋትን መማሳየት ይኖርብናል፡፡
አንድ ሰው እንዴት ሺህን ያሳድድ ነበር? ሁለቱሳ እንዴት አሥሩን ሺህ ያሸሹ ነበር? ዘዳግም 32፡30
አንድነት ለሰነፎች እና ለልፍስፍሶች አይደለም፡፡ ማንም መንገደኛ አንድነትን ሊረብሽ ይችላል፡፡ አንድነትን ለመጠበቅ ግን ትጋትና ጥንካሬ ይጠይቃል፡፡ ማንም ሰው በስንፍና አንድነትን ሊያፈርስ ይችላል በአንድነት ውስጥ የተቀመጠውን ጠቅም ለመጠቀም ግን ጥበብና ማስተዋል ይጠይቃል፡፡ ማንም ሰው በስንፍና አንድነትን ሊያፈርስ ይችላል ነገር ግን አንድነት በትጋት ይጠበቃል፡፡
አንድነት በልባችን እኛን ለማይመስል ሰው ስፍራን ማዘጋጀት ይጠይቃል፡፡ ማንም መንገደኛ የሚመስለውንና የሚመቸውን ይሰበስባል፡፡ ማንም መንገደኛ አዎ አዎ የሚለውን ሁሌ ሃሳቡን የሚቀበለውን ይወዳል፡፡ ማንም መንገደኛ ከእርሱ የተለየወን ሰው ይጥላል፡፡ ነግር ግን ለአንድነትና ስለላቀ ውጤት የማይመስሉንን ሰዎች የሚቀበል የልብ ስፋት ይጠይቃል፡፡
ማንም ሰው የእርሱ ሃሳብ ትክክለኛ ይመስለዋል፡፡ አንድነት ከእኛ የተለየ የሚያስቡትን ሰዎች ሃሳብ ማስተናገድ ይጠይቃል፡፡ ሞኝ ትክክለኛ ስለመሰለው ስለራሱ ሃሳብ የሌሎችን ሰዎች ሁሎ ሃሳብ ሊጥል እና አንድነትን ሊረብሽ ይችላል፡፡
አንድነት ተመሳሳይነት አይደለም፡፡ አንድነት የተለያዩ ሰዎች ለአንድ አላማ መስራት ነው፡፡ ሰውን ሁሉ ተመሳሳይ ለማድረግ የሚፈትነውን ማለፍ ካላለፍን ለእንድነት መስራት አንችልም፡፡ የተለያዩ ሰዎችን ማስተናገድ ፈተና ነው፡፡ ሁሉም ሰው ተመሳሳይ ቢሆን ይቀላል፡፡ ሰው ለሁሉም ሰው አንድ ህግ አውጥቶ ሁሉም አንድ እያሰቡ ፣ ሁሉም እንድ እየተናገሩና ሁሉም አንድ እንዲኖሩ ይመኛል፡፡ ሰው ሁሉንም ተመሳሳይ ለማድረግ ተስደፋ ካልቆረጠ አንድነት የማይታሰብ ነው፡፡
አንድነት የተለያዩ ሰዎች ራሳቸውን እንዲሆኑና ነገር ግን ለአንድ አላማ እንዲሰሩ ማድረግ መቻል ነው፡፡ ሰዎችን ሁሉ ተመሳሳይ ለማድረግ መሞከር ሰዎችን ሁሉ መግደልና በሰዎችን ውስጥ ያለውን የተለያየ እምቅ ጉልበትን ማባከን ነው፡፡
እንዲያውም አንድነት ማለት እያንዳንዱ የራሱን ስራ መስራት ማለት እንጂ አንድ ጣራ ስር መሰብሰብ ፣ አንድ አይነት መልክ መያዝ አንድ አይነት አስተሳሰብ ማሰብና አንድ አይነት ነገር መናገር አይደለም፡አንድነት ማለት በአንድ አለማ ስር በመሆን እያንዳንዱ የተሰጠውን ስራ የራሱን ልዩ ስራ መስራት ማለት ነው፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ራእይ #መዳን #እምነት #አንድነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ህብረት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አላማ #ግብ #ፅናት #ትግስት #ትጋት

Monday, December 25, 2017

አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል

ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ . . . የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል። ኢሳይያስ 9፡6
የአለቅነት ብቸኛው ጥቅም ሰዎች ሲገለገሉና ሲጠቀሙ ማየት ነው፡፡ አለቅነት በራሱ ጥቅም አይደለም፡፡ የአለቅነት ጥቅም ሰዎች ካሉበት እግዚአብሄር ወደ አየላቸው ደረጃ ሲደርሱ ማየት ነው፡፡ አለቅነት ሰዎች ከታሰሩበት ነገር ተፈትተው በነፃነት እግዚአብሄርን ሲያገለግሉ ማየት ነው፡፡
አለቅነትን ለራሳቸው ጥቅም የሚጠቀሙበት ሰዎች በአለም ላይ ስላሉ አለቅነት ከጥቅም ጋር ተያይዞዋል፡፡ በአገራችንም ያለውም አባባል ሲሺም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል የሚለው አባባል የመጣው አለቅነትን ከተጠቃሙነት ጋር አያይዞ ነው፡፡ ነግር ግን አባባሉ መሆን የነበረበት "ሲሾም በትጋትና በታማኝነት ህዝብን ያላገለገለ ሲሻር ይቆጨዋል" መሆን ነበረበት፡፡ አለቅነት ሰውን ከመጥቀም ያለፈ ጥቅም የለውም፡፡ አለቅነት ግን እግዚአብሄርን አገልግሎ ከእግዚአብሄር ሽልማትን ከመቀበል ውጭ ጥቅማ ጥቅም የለውም፡፡
የአለቅነትን ሃላፊነት የተረዱ ሰዎች አለቅነትን እንደ ጥቅም አይጓጉለትም፡፡ የአለቅነት ሃላፊነትን የተረዱ ሰዎች ሸክሙ እንጂ ጥቅሙ ትዝ አይላቸውም፡፡ የአለቅነትን ሸክም የተረዱ ሰዎች አላቅነትን እንደጥቅም አይፈልጉትም፡፡   
እርግጥ ነው በአለም ያሉ ሰዎች አለቅነትን እንደመጠቀሚያ ይጠቀሙበታል፡፡ በአለም ያሉ ሰዎች ከሰው ውስጥ ትልቁን ድርሻ ለመጠቀም የአለቅነትን ስልጣን በጭካኔ ይጠቀሙበታል፡፡ በአለም ብዙ አለቅነት ያለው ብዙ ይጠቀማል ትንሽ አለቅነት ያለው ትንሽ ይጠቀማል፡፡ በአለም ያሉ ሰዎች አለቅነትን ሰውን ለመበዝበዝ ይጠቀሙበታል፡፡
ኢየሱስ ግን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ የአሕዛብ አለቆች እንዲገዙአቸው ታላላቆቹም በላያቸው እንዲሠለጥኑ ታውቃላችሁ። ማቴዎስ 20፡25-26
አለቅነትን ለራስ ጥቅም መጠቀሚያ ማድረግ የእግዚአብሄር ሃሳብ አይደለም፡፡ አለቅነት የመጠቀሚያ መንገድ አይደለም፡፡
በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፥ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት፤ ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ፤ 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 5፡2-3
አለቅነት ሃላፊነት ነው፡፡ አለቅነት ሸክም ነው፡፡ አለቅነት የትጋት ስራ ነው፡፡ አለቅነት ታማኝነት ነው፡፡ አለቅነት መሰጠት ነው፡፡ አለቅነት ፊት ቀዳሚነት ነው፡፡ አለቅነት ማንም ባያደርገው እኔ አደርገዋለሁ ማለት ሃላፊነት መውሰድ ነው፡፡ አለቅነት ምሪትን በየጊዜው በመስጠት የመጥቀም የማገልገል መንገድ ነው፡፡  
በእናንተስ እንዲህ አይደለም፤ ነገር ግን ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፥ ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የእናንተ ባሪያ ይሁን፤ እንዲሁም የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም። ማቴዎስ 20፡26-28
አለቅነት ሰላምን መስጠት ነው፡፡ አለቅነት ሰዎችን ወደ ሰላም ምንም ወዳልጎደለበትና ምንም ወዳልተበላሸበት ቦታ መርቶ ማድረስ ነው፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ሰላም #ድንቅመካር #ሃያልአምላክ #የሰላምአለቃ #የዘላለምአባት #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ማገልገል #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #አለቅነት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Sunday, December 24, 2017

የእኔ ምስክርነት

አቢይ እባላለሁ፡፡ ጌታን ያገኘሁት በ 17 ዐመቴ ነበር፡፡
ጌታን ያገኘሁት በአክስታችን ምስክርነት ነበር፡፡ አክስታችን ጌታን የምታውቀው በደርግ ዘመን ነው፡፡ በደርግ ዘመን ጌታን በመመስከር ታስራ ታውቃለች ስለጌታ ብዙ ዋጋን የከፈለች የእምነት ሴት ነች፡፡ ሁሌ ስለጌታ ትመሰክርልን ነበር፡፡ ቤተክርስትያን ልዩ ፕሮግራም ሲኖር ዛሬ ድራማ አለ ኑ እዩ እያለች ባገኘነው አጋጣሚ ቃሉን እንድንሰማ ትጋብዘን ነበር፡፡
እኔ ለሃይማኖት ግድ አልነበረኝም፡፡ እንዲያውም 2 ሰአት ቤተክርስትያን መቀመጥ ጊዜን እንደማባከን ነበር የምቆጥረው፡፡
አባቴና እናቴ በትምህርት በጣም ያምኑ ስለነበረ እኔም በትምህርት በጣም አመን ነበር፡፡ ሰው ተምሮ ዲግሮ ካለው በቃ የህይወት ጥያቄው ይመለሰላ ብዬ አስብ ነበር፡፡ ስለዚህ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ እያለሁ ለትምህርት ልዩ ትኩረት ሰጥቼ አጠና ነበር፡፡ ወላጆቼ በጣም እንዳጠና ያበረታቱኝና እንደሚቻል ይነግሩኝ በእኔም ይተማመኑ ስለነበር እወድቃለሁ ብዬ አላስብም ነበር፡፡
ነገር ግን ማትሪክ አልመጣለኝም ነበር፡፡ የማትሪክ ውጤቴ ለዲግሪም ሆነ ለዲፕሎማ አለማሳለፉ የህይወት አመለካከቴን ቀየረው፡፡ ልቤን ያለዘጋጀሁለት ውድቀት ነበር፡፡ ህይወት ጨለመብኝ፡፡ የተለያዩ ኮርሶችን ለመውሰድ ሞክሬም እልተሳካልኝም፡፡
ያን ጊዜ ነው ጌታ ትኩረቴን ያገኘው፡እስከዚያ ድረስ ለጌታና ለመንፈሳዊ ነገር ትኩረት አልሰጥም ነበር፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ተስፋ የሚሆነኝን አገኘሁ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነበር ጌታን የተቀበልኩት፡፡
ነገር ግን ጌታንም ተቀብዬ እንደሚገባ አልመላለስም ነበር፡፡ ሁልጊዜ አልፀልይም፡፡ ሁልጊዜ አላነብም፡፡ የምፀልይ የነበረው ችግር ሲገጥመኝ ብቻ ነበር፡፡ ጌታንም ብቀበል በእኔነት የተሞላሁ ነበርኩ፡፡ ጌታ ለሁሉም ነገሬ እንደሚያስፈልገኝ አላምንም ነበር፡፡
ነገር ግን አንድ ወንድም ወደ አንድ የመፅሃፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ይዞኝ ሄደ፡፡ የመፀሃፍ ቅዱስ ትምህርት ቤቱ ከገባሁ ጀምሮ የእግዚአብሄርን ቃል በሃይል የሚያስተምሩ አስተማሪ ስለነበሩ እጅግ ወደድኩት በተከታታይ መማር ጀመርኩ፡፡ እዚያ እያለሁ ነበር እንግዲህ ጌታን ለማገልገል የወሰኩት፡፡ በተለይ የሚያስተምሩን አስተማሪ ጌታ እንዳገለግለው ሲጠራኝ ማቴዎስ 6፡25-33 ሰጠኝ ብለው ብዙ ጊዜ ስለ እምነት ያስተምሩን ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ስለምበላውና ስለምለብሰው መጨነቅ ከህይወቴ ሞተ፡፡
ጌታን ከመከተሌ ባሻገር ጌታን የማገልገል ውሳኔዬን ወላጆቼ በቀላሉ አላዩትም፡፡ በጊዜው ስራ አልሰራም ትምህርትም አልማርም በማለቴ እጅግ ግራ ገብቷቸው ነበር፡፡ እኔ ግን የአገልግሎት ጥሪ በህይወቴ በግልፅ ስለሰማሁ በመንፈሳዊ የመፅሃፍ ቅዱስ ትምህርትና በአገልግሎት ቀጠልኩ፡፡
በዚያን ጊዜ አገልግሎት የጀመርኩት እኛ ቤት እሁድ ከሰአት 120 ፕሮግራም ሊያዩ የሚመጡትን ልጆች ሰብስቤ በማስተማር ነበር፡፡
አሁንም ጌታን በተለይ በማስተማር አገለግላለሁ፡፡ በእነዚህ ሁሉ ዘመናት የማስተማር ፀጋ በህይወቴ እንደሚሰራ አይቻለሁ፡፡ በውስጤ የሚፈሰው ትምህርት ብዛት ለራሴም ያስደንቀኛል፡፡ ይህ የእኔ ችሎታ እንዳልሆነ ስለምረዳ ሁልጊዜ ትሁት ያደርገኛል፡፡ በእኔ ውስጥ ከሚሰራው የእግዚአብሄር ፀጋ ውጭ ምንም የሚያስመካ ነገር የለኝም፡፡ እግዚአብሄር ስለተጠቀመብኝ እንጂ እኔ የማልጠቅም ባሪያ ነኝ፡፡
አሁን በዛን ጊዜ በወሰንኩት ጌታን እስከ መጨረሻው የመከተል ውሳኔ ደስተኛ ነኝ፡፡ ጌታን ለማገልግል እንደገና እንድወስን እድል ቢሰጠኝ ጌታን ለማገልግል የወሰንኩት ውሳኔ እንደገና እወስነዋለሁ፡፡ ጌታን ለማገልገል በመወሰኔ ሁሌ ከመደሰት በስተቀር አንድ ቀንም ተፀፅቼ አላውቅም፡፡ አንዳንዴ እንዲያውም ምነው አንድ ብቻ ሳይሆን ከአንድ በላይ ነፍስ ቢኖረኝና ለጌታ ባስገዛሁለት ብዬ አስባለሁ፡፡   
እግዚአብሄር በእነዚህ ሁሉ ዘመናት እንደ አይኑ ብሌን ሲንከባከበኝ አይቻለሁ፡፡ እግዚአብሄር በሁሉ ነገር ባርኮኛል፡፡ የሚያስፈልገኝ ነገር ሁሉ አለኝ፡፡ ስወድቅ ሲያነሳኝ ፣ ሳዝን ሲያኝናናኝ ፣ ስደክም ሲደግፈኝ አይቼዋለሁኝ፡፡ ከዚህ በላይ እንክብካቤ ከእግዚአብሄር አልጠብቅም፡፡ ከሚያደርግልኝ እንክብካቤ በላይ እንክብካቤ ያለም አይመሰለኝም፡፡
እንደተራራ የገዘፉትንና ይደረስባቸው ይሆን ብዬ ደጋግሜ የጠየኩትን ብዙ ህልሞቼን እግዚአብሄር አሳይቶኛል፡፡ ህልሜን እየኖርኩት ነው፡፡ ብዙ የሚፈፀሙ ህልሞች ደግሞ አሉኝ፡፡  
አሁን በህይወቴ እግዚአብሄር ደስተኛ ነኝ፡፡ አሁን ባለሁበት እግዚአብሄር ባደረሰኝ ደረጃ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ምንም እንደ ጎደለኝ አይሰማኝም፡፡ ከእኔ በላይ ደስተኛ ሰው በምድር ላይ ያለ አይመስለኝም፡፡ የእግዚአብሄር ሰላም በውስጤ እንደወንዝ ይፈስሳል፡፡ በክርስቶስ ይህ ሁሉ ነፃነት አለ እንዴ ብዬ እስከማስብ ድረስ እጅግ ነፃነት ይሰማኛል፡፡
እነዚህን ሁሉ አመታት በድል የጠበቀኝን እንዳገለግለው ታማኝ አድርጎ የቆጠረኝን እግዚአብሄርን አመሰግነዋለሁ፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ገና #በዓል #ፍቅር #ተስፋ #ደስታ #መስዋእት #ምስክርነት #መዳን #ምስጋና #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ብርሃን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  #ኢየሱስ #ጌታ

Saturday, December 23, 2017

አንድም አሳብ ይሁንላችሁ

በክርስቶስም አንዳች ምክር ቢሆን፥ የፍቅር መጽናናት ቢሆን፥ የመንፈስ ኅብረት ቢሆን፥ ምሕረትና ርኅራኄ ቢሆኑ፥ ደስታዬን ፈጽሙልኝ፤ በአንድ አሳብ ተስማሙ፥ አንድ ፍቅር አንድም ልብ አንድም አሳብ ይሁንላችሁ፤ ፊልጵስዩስ 2:1-2
እንግዲህ በጌታ እስር የሆንሁ እኔ በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤ በትሕትና ሁሉና በየዋህነት በትዕግሥትም፤ እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ፤ በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ። ኤፌሶን 4፡1-3
የእግዚአብሄር መንግስት ስራ ሁሉም ያለውን ፀጋ የሚያዋጣበት የህብረት ስራ እንጂ የአንድ ሰው ስራ አይደለም፡፡ የእግዚአብሄር መንግስት ስራ የህብረት ስራ ነው፡፡ በእግዚአብሄር መንግስት መፍትሄ ሁሉ በአንድ ሰው ውስጥ ብቻ አልተቀመጠም፡፡ የእግዚአብሄር መንግስት ብዙ ብልቶች እንዳሉት አካል ይመሰላል፡፡  
አካልም አንድ እንደ ሆነ ብዙም ብልቶች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ብልቶች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደ ሆኑ፥ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው፤ 1ኛ ቆሮንጦስ 12፡12
በአንድ አካል ብዙ ብልቶች እንዳሉን፥ የብልቶቹም ሁሉ ሥራ አንድ እንዳይደለ፥ እንዲሁ ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን፥ እርስ በርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው ብልቶች ነን። ሮሜ 12፡4-5
የእግዚአብሄር ስራ የህብረት ስራ በመሆኑ አንድነት ወሳኝ ነው፡፡ በሰዎች መካከል አንድነት ከፈረሰ ህብረት ይፈርሳል፡፡ አንድነት ከፈረሰ መንግስት አይቆምም፡፡
እርስ በርሱ ተለያየ፥ እንግዲህ መንግሥቱ እንዴት ትቆማለች? ማቴዎስ 12፡26
በመፅሃፍ ቅዱስ አንድነት እንዲኖረን አንድነታችንን ተግተን እንድንጠብቅ አበክሮ የሚያስጠነቅቀን ለዚህ ነው፡፡
አንዳንድ ጊዜ አንድ ነገር የሚሆንበትን ምክኒያት ከመግለፅ ይልቅ አንድ ነገር የማይሆንበትን ምክኒያት መግለፅ ይቀላል፡፡ አንድነት አሁንም አንድነት የሚጠበቅበትን ሁኔታ ከማስረዳት ይልቅ አንድነት የማይጠበቅበትን ሁኔታ ማስረዳት ስለ አንድነት ያለንን መረዳት ይጨምራል፡፡
አንድነት የማይጠበቅበትን ምክኒያትና አንድነትን መጠበቅ የማይፈልጉ አምስት አይነት ሰዎችን እንመልከት፡፡
1.      ሰዎች ከጋራ አጀንዳ ይልቅ የራሳችው የግል አጀንዳ ሲኖራቸው አንድነትን መጠበቅ አይፈልጉም፡፡
ሰዎች ህብረትን የሚፈልጉት የእግዚአብሄርን መንግስት ጥቅም ለማስከበር ሳይሆን የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሆን ህብረትን አይፈልጉም፡፡
ሰው የእግዚአብሄርን ፈቃድ ሳይሆን ምኞቱን ከተከተለ አንድነትን ሳይሆን መለየትን ይፈልጋል፡፡  
መለየት የሚወድድ ምኞቱን ይከተላል፥ መልካሙንም ጥበብ ሁሉ ይቃወማል። ምሳሌ 18፡1
2.     ሰዎች ጨካኞችና የማይራሩ ሲሆኑ አንድነትን መጠበቅ አይፈልጉም፡፡
ሰዎች ለእግዚአብሄር መንግስት ስምረት ግድ ሳይኖራቸው ሲቀር ለአንድነት ግድ አይኖራቸውም፡፡ ሰዎች ከእግዚአብሄር ምነገሰት ሸክም ይልቅ የሚያከብሩት ሌላ አለማ ካላቸው ለአንድነት ዋጋ ለመክፈል ዝቅ ማት ያቅታቸዋል፡፡ አንድነት ዋጋ ያስከፍላል፡፡ አንድነት እኛን የማይመስሉንን ሰዎች መቀበል ይጠይቃል፡፡ አንድነት የተለያየን ሰዎች ለአንድ አላማ መቀራረብን ይጠይቃል፡፡ ለመንግስቱ እውነተኛ ሸክም ያለው ሰው ለአንድነት የሚያስከፍለውን ዋጋ ሁሉ ይከፍላል፡፡ ለመንግስቱ ሸክም ያለው ሰው ከእርሱ ስሜት ይልቅ የአንድነት የጋራ ጥቅም ይበልጥበታል፡፡
እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፥ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፥ ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ፤ በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት። ቆላስይስ 3፡13-14
3.     ሰዎች ሰነፍና ሀሞተ ቢስ ሲሆኑ አንድነትን መጠበቅ አይፈልጉም፡፡
አንድነትን መጠበቅ ለሰነፍ ሰው አይደለም፡፡ አንድነትን መጠበቅ ትጋት ይጠይቃል፡፡ አንድነትን መጠበቅ መነጋገር መወያየት በቀጣይነት በትጋት ችግሮችን መፍታት ይጠይቃል፡፡ አንድነትነ መጠበቅ የደካማ ሰዎች አይደለም፡፡ አንድነትም መጠበቅ የፈሪዎች አይደለም፡፡ አንድነትን መጠበቅ የደካ ሰዎች አይደለም፡፡ አንድነትን መጠበቅ የእምነት ሰዎች ነው፡፡ አንድነትን መጠበቅ የልበ ሰፊ ሰዎች ነው፡፡  አንድነትን መጠበበቅ የደፋር ሰዎች ነው፡፡
በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ። ኤፌሶን 4፡3

ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ። ኤፌሶን 4፡12-13
4.     ትእቢተኛና ትምክተኛ ሰዎች አንድነትን መጠበቅ አይችሉም፡፡
ሰዎች ከሌላው እበልጣለሁ ሲሉና ሁሉንም የሚያውቁ ሲመስላቸው አንድነትን መጠበቅ ያቅታቸዋል፡፡ ሰዎች ራሳቸውን አዋርደው ወደ አንድነት ሃሳብ ከመምጣት ይልቅ የእኔ ሃሳብ ብቻ ይሁን ካሉ አንድነት ሊጠበቅ ይችልም፡፡ ሰዎች ለመሸነፍ ሲፈቅዱ አንድነት ይመጣል፡፡ ሰዎች የእኔ ሃሳብም ባይሆን የሚበልጠው ይሁን ካሉ አንድነት ይመጣል፡፡ ነገር ግን ሰዎች ሁሌ የእኔ መንገድ ብቻ ነው ትክክለ ካሉ ከማንም ጋር መስማማትና መስራት ያቅታቸዋል፡፡
በመጨረሻው ሁላችሁ በአንድ ልብ ሁኑ፥ የሌላው መከራ ለእናንተ እንደሚሆን አድርጉ፥ እንደ ወንድሞች ተዋደዱ፥ ርኅሩኆችና ትሑታን ሁኑ፤ 1ኛ ጴጥሮስ 3፡8
እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ፤ የትዕቢትን ነገር አታስቡ፥ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ። ልባሞች የሆናችሁ አይምሰላችሁ። ሮሜ 12፡16
5.     ሰዎች ስስታም ሲሆኑ አንድነትን አይፈልጉም፡፡  
ሰዎች ስስታም ሲሆኑ ህይወታቸውን ለሌላ ሰው ለማካፈል ሲሰስቱ አንድነትን ይቃወማሉ፡፡ በማካፈልና በመስጠት ብቻ ላይ ነው አንድነት የሚመሰረተው፡፡ ሰዎች ግን መስጠት ሲሰስቱ ለማካፈል ፈቃደኛ ሳይሆኑና መቀበል ብቻ እንደሚገባቸው ሲያስቡ አንድነት አይታሰብም፡፡
ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ። 1ኛ ቆሮንቶስ 1፡10
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ራእይ #መዳን #እምነት #አንድነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ህብረት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #የዘላለምህይወት #ፅናት #ትግስት #መሪ

Friday, December 22, 2017

#ኢየሱስ

የገና በአል ትርጉም የተረሳ ይመስላል፡፡ የገና በአል ሲታሰብ መብላት ከታሰበ ፣ የገና በአል ሲታሰብን መጠጣት ከታሰበ ፣ የገና በአል ሲታሰንብ መልበስ ከታሰበ ፣ የገና በአል ሲታሰብ የገና ዛፍ ከታሰበ የገና በአል ሲታሰብ ከረሜላ እና ቸኮሌት ከታሰበ ፣ የገና በአለ ሲታሰብ ጣፋጭ ብስኩትና ኬክ ከታሰበ ፣ የገና በአል ሲታሰብ እረፍትና መዝናናት ከታሰበ ፣ የገና በአልዕ ሲታሰብ ዘፈንና ዳንራ ከታሰበበ ፣ የገና በአል ሲታሰብ መጠጣትና መስከር ከታሰበ ምንም ሃይማኖተኛ ብንሆን የገናን ትርጉም አናውቀውም ማለት ነው፡፡
ገና የሚበላበት የሚጠጣበት የሚዘፈንበት የሚጨፈርበት አይደለም፡፡ ገና እግዚአብሄር ለሰዎች የሰጠው ስጦታ ኢየሱስ የሚዘከርበት እግዚአብሄር የሚመሰገንበትና በስጦታው ምክኒያት ያገኘነው የክርስትና ነፃነት በአል የሚደረግበት ጊዜ ነው፡፡ ገና የእግዚአብሄርን ስጦታ የማክበርበት ጊዜ ነው፡፡ ገና የእግዚአብሄርን ስጦታ የምናጣጥምበት ጊዜ ነው፡፡  
የገና ምክኒያት ኢየሱስ ነው፡፡
ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። ማቴዎስ 1፡21
የገና ምክኒያት እግዚአብሄር ለሰው ልጆች ስጦታ መስጠቱ ነው፡፡
በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዮሃንስ 3፡16
የገና ምክኒያት ስጦታውን የተቀበሉ ከሃጢያት መዳናቸው ነው፡፡
እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም፤ ቲቶ 3፡5
የገና በአል በእግዚአብሄር ስጦታ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቃችን ነው፡፡
እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡19
የገና በአል ኢየሱስን የተቀበልን የእግዚአብሄር ልጅ መሆናችን ነው፡፡
ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ዮሃንስ 1፡12
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ገና #በዓል #ፍቅር #ተስፋ #ደስታ #መስዋእት #ሃጢያት #መዳን #ነፃነት ## #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ብርሃን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  #ኢየሱስ #ጌታ