Popular Posts

Friday, May 26, 2017

የመኖሪያ ፈቃድ

እግዚአብሄር ሰውን በመልኩና በአምሳሉ የፈጠረው ሰው ከእርሱ ጋር እንዲግባባ ነው፡፡ ሰው በምድር ላይ የእግዚአብሄርን አላማ እንዲያስፈፅም በእግዚአብሄር መልክና አምሳል ተፈጥሮአል፡፡
ሰው ሃጢያት በሰራና በእግዚአብሄር ላይ ባመፀ ጊዜ ከእግዚአብሄ ጋር የነበረው የአባትና ልጅ ግንኙነት ተቋረጠ፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር መግባባት አቃተው፡፡ ሰው የተፈጠረበትን አላማ እውነትን አጣው፡፡
ኢየሱስ ወደምድር የመጣውና የሃጢያት እዳችንን ሁሉ የከፈለው የእግዚአብሄር ልጆች እንድንሆንና የእግዚአብሄር መንፈስ እንዲያድርብንና ወደ እውነት ሁሉ እንዲመራን ነው፡፡    
እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋል፥ ሁሉንም ታውቃላችሁ። እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነተኛም እንደ ሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ። 1ኛ ዮሃንስ 2፡20፣27
የእግዚአብሄር መንፈስ ለጥቂት ሰዎች ብቻ አይደለም፡፡ በጌታ ኢየሱስ ያመነ ሰው ሁሉ ከቅዱሱ ቅባት ተቀብሎዋል፡፡ በእያንዳንዱ የህይወት ክፍላችን የእግዚአብሄር ምሪት ስለሚያስፈልገን ይህ የተቀበልነው ቅባት በእኛ ውስጥ ይኖራል፡፡
የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን? 1ኛ ቆሮንቶስ 3፡16
ይህ በእኛ ውስጥ ለዘላለም የሚኖረው ቅባት የእግዚአብሄርን መንገድ ያስተምረናል፡፡
ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል። ዮሃንስ 16፡13
ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ። ዮሐንስ 14፡15-17
አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል።ዮሐንስ 14፡26
እከሌ ካላስተማረኝ ዋጋ የለኝም እስከማንል ድረስ ወይም ግዴታ ሌላ አስተማሪ ሊያስተምረን እስከማያስፈልገን ድረስ ቅባቱ በህይወታችን ማወቅ ያለብንን ነገር ሁሉ ያስተምረናል፡፡
በውስጣችን የሚኖረው ቅባት የሚያስተምረን አንዳንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሳይሆን ዘወትር ያስተምረናል፡፡ የእግዚአብሄርን ነገር ከየት አገኘዋለሁ እሰከማንል ድረስ የእግዚአብሄር እውነት በቅባቱ በልባችን ቀርቦዋል፡፡
ከእምነት የሆነ ጽድቅ ግን እንዲህ ይላል፦ በልብህ፦ ማን ወደ ሰማይ ይወጣል? አትበል፤ ይህ ክርስቶስን ለማውረድ ነው፤ ወይም፦ በልብህ፦ ወደ ጥልቁ ማን ይወርዳል? አትበል፤ ይህ ክርስቶስን ከሙታን ለማውጣት ነው። ሮሜ 10፡6-7
ይህ በውስጣችን ያለው ቅባት የሚያስተምረን ስለሁሉ ነው፡፡ በህይወታችን ያለውን ሃላፊነት የምንወጣበትን እውቀት ሁሉ ይሰጠናል፡፡ ይህ ትንሽ ነው ብሎ የሚንቀውና የማያስተምረን ነገር የለም፡፡ እግዚአብሄር ከምናስበው በላይ ስለህይወት ዝርዝር ነገራችን እንደሚገደው ሁሉ  በውስጣችን ያለው ቅባት ስለዝርዝር ነገራችን ሁሉ ያስተምረናል፡፡ ማቴዎስ 10፡30
ይህ ቅባት የሚያስተምረው ነገር ሁሉ አስተማማኝ እውነት ነው፡፡ በሌላ በማንም ባትተማመኑ በውስጣችሁ ቅባት መተማመን አለባችሁ፡፡ ማንም ቢዋሽ ይህ ቅባት እውነተኛውን ነገር ይናገራል፡፡
እንዳስተማረን በእርሱ ልንኖር ይገባናል፡፡ በሌላ በምንም ለመኖር ብንፈራ ቅባቱ ባስተማረን ለመኖርት መፍራት የለብን፡፡ ሌላ ምንም ያስተናል ብንል ብንጠራጠር ቅባቱ ግን አያስተንም፡፡ በሌላ በምንም እውቀት ለመኖር ነፃነቱ ባይኖረን ቅባቱ እንዳስተማረን ለመኖር ግን ነፃነቱ ሊኖረን ያስፈልጋል፡፡ በቅባቱ ምሪት ነፃ ካልሆንን በምንም ነፃ አንሆንም፡፡
እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋል፥ ሁሉንም ታውቃላችሁ። እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነተኛም እንደ ሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ። 1ኛ ዮሃንስ 2፡20፣27
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #መንፈስቅዱስ #አፅናኝ #እውነት #ምሪት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት  #ድምፅ #ቅባት #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #መውደድ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment