ንስሃ በጣም አስፈላጊ ከሆኑ ነገሮች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ንስሃ እግዚአብሄርን እና ሰውን የሚያስማማ ብቸኛው ነገር ነው፡፡ ንስሃ ህይወታችንን ይለውጣል፡፡ ህይወታችን የሚለወጠው ንስሃ በገባንበት መጠን ብቻ ነው፡፡
ንስሃ ማለት ደግሞ የአስተሳሰብ ለውጥ ማለት ነው፡፡ ንስሃ ማልቀስ አይደለም ፡፡ ንስሃ መፀፀት አይደለም፡፡ ንስሃ መንገድን መለወጥ ነው፡፡
እግዚአብሄር ሰውን ሲፈጥረው ፍፁም አድርጎ ፈጥሮታል፡፡ ነገር ግን ሰው አትብላ የተባለውን በመብላት በእግዚአብሄር ላይ አመፀ፡፡ ከአመፀኛው አዳም የተወለድን ሁላችን በአመፅ ተወለድን፡፡
እግዚአብሄር ደግሞ ቅዱስ ነው፡፡ እግዚአብሄር ስለ አብዛኛው ሰው ብሎ መንገዱን አይለውጥም፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር ለመኖር መለወጥ ያለብን እኛ ነን፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር የምንኖረው በእግዚአብሄር መንገድ ነው፡፡ እግዚአብሄር የሚቀበለን የእርሱን መንገድ ከተቀበልን ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄር ንጉስ ነው፡፡ እግዚአብሄር ስለማንም ሰው ቃሉን አይለውጥም፡፡
ከእግዚአብሄር ጋር ለመኖር የወደቅንበትን የቀድሞ ሃሳብ መተው አለብን፡፡ በወደቅንበት አስተሳሰብ ከእግዚአብሄር ጋር መቀጠል አንችልም፡፡ ከሰይጣም መንግስት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግስት ለመምጣት የአስተሳሰብ ለውጥ (ንስሃ) ያስፈልጋል፡፡ ካለ እውነተኛ ንስሃና ካለ አስተሳሰብ ለውጥ ከአለም ወደ እግዚአብሄር መንግስት መምጣት አይቻልም፡፡
የአለም አሰራርና የእግዚአብሄር መንግስት አሰራር በፍቅርና በጥላቻ መካከል እንዳለው ልዩነት ነው፡፡ የአለምና የእግዚአብሄር ቤተሰብ አሰራር በፍቅርና በራስ ወዳድነት መካከል እንዳለው ልዩነት ነው፡፡ በአለም አሰራር በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ሊሳካልን አይችልም፡፡ በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ በአለም መርህ ልንከናወን አንችልም፡፡ ሁለቱ መንግስቶች አምላካቸው ፍላጎታቸው አሰራራቸው እጅግ ተቃራኒዎች ናቸው፡፡
በአለም የኖርንበት መርህ በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ስኬታማ አያደርገንም፡፡ ሰዎች በአለም የኖሩበትን አሰራር በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ሊኖሩበት ሲሞክሩ ህይወታቸው በከንቱ ይባክናል፡፡ በእግዚአብሄር ምንግስት እንዲሳካልን ከአለምን አሰራር ነፃ መውጣት አለብን፡፡
ስለዚህ ርኵሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ። ያዕቆብ መልእክት 1፡21
ከአለም ስንመጣ ባለን እውቀት አይደለም የምንቀጥለው፡፡ በእግዚአብሄር መንግስት ከአዲስ ነው የምንጀምረው፡፡ በእግዚአብሄር መንግስት በጀመርነው እርምጃ አይደለም የምንቀጥለው በእግዚአብሄር መንግስት ወደሃላ ዞረን ነው የምንመለሰው፡፡
በእግዚአብሄር መንግስት ለመማር የቀድሞ ሃሳባችንን ለመለወጥ ትሁት መሆን አለብን፡፡ በእግዚአብሄር መንግስት የእግዚአብሄርን ቃል አሰራር ለመማርና ለመለወጥ ካልተዘጋጀን ህይወታችን የትም አይደርስም፡፡ የህይወት ለውጥና ፍሬያማነት የሚገኘው የቀድሞውን አስተሳሰባችንን ጥለን በአዲሱ አሰራር ለመኖር የዋህ ስንሆን ብቻ ነው፡፡
ጌታን እንደተቀበልን ብቻ ሳይሆን በየእለቱ የራሳችንን ሃሳብ ጥለን የእግዚአብሄርን ቃል መርህ ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን አለብን፡፡ በእግዚአብሄር መንግስት የሚሳካልን ሃሳባችንን ለመለወጥ በፈቀድን መጠን ብቻ ነው፡፡ ካለ በለዚያ የእስራኤል ህዝብ ወደተስፋይቱ ምድር መግባት አቅቶት የሴይርን ተራራ አርባ አመት እንደዞረ እኛም ካለውጤት እንዲሁ እንባክናለን፡፡
ስለዚህ ነው በእግዚአብሄር ፈቃድ ሃሳባችንንና መንገዳችንን እንድንለውጥና የመጣንበትን አለም አንዳንመስል መፅሃፍ ቅዱስ የሚያዘን፡፡
የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። ሮሜ 12፡2
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
No comments:
Post a Comment