Popular Posts

Wednesday, May 24, 2017

የአባቶች እምነት ምስክርነት በ40 ጥቅሶች

ዕብራውያን 111-40

እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው። ለሽማግሌዎች የተመሰከረላቸው በዚህ ነውና። ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተዘጋጁ፥ ስለዚህም የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን። አቤል ከቃየል ይልቅ የሚበልጥን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ፥ በዚህም፥ እግዚአብሔር ስለ ስጦታው ሲመሰክር፥ እርሱ ጻድቅ እንደ ሆነ ተመሰከረለት፤ ሞቶም ሳለ በመሥዋዕቱ እስከ አሁን ይናገራል። ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ፥ እግዚአብሔርም ስለ ወሰደው አልተገኘም። ሳይወሰድ እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ ተመስክሮለታልና፤ ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ኖኅ ገና ስለማይታየው ነገር ተረድቶ እግዚአብሔርን እየፈራ ቤተ ስዎቹን ለማዳን መርከብን በእምነት አዘጋጀ፥ በዚህም ዓለምን ኰነነ፥ በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ሆነ። አብርሃም የተባለው ርስት አድርጎ ሊቀበለው ወዳለው ስፍራ ለመውጣት በእምነት ታዘዘ፥ ወዴትም እንደሚሄድ ሳያውቅ ወጣ። ለእንግዶች እንደሚሆን በተስፋ ቃል በተሰጠው አገር በድንኳን ኖሮ፥ ያን የተስፋ ቃል አብረውት ከሚወርሱ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር፥ እንደ መጻተኛ በእምነት ተቀመጠ፤ መሠረት ያላትን፥ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ ይጠብቅ ነበርና። ተስፋ የሰጠው የታመነ እንደ ሆነ ስለ ቈጠረች፥ ሣራ ራስዋ ደግሞ ዕድሜዋ እንኳ ካለፈ በኋላ ዘርን ለመፅነስ ኃይልን በእምነት አገኘች። ስለዚህ ደግሞ በብዛታቸው እንደ ሰማይ ኮከብ እንደማይቈጠርም በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ የነበሩት የሞተን ሰው እንኳ ከመሰለው ከአንዱ ተወለዱ። እነዚህ ሁሉ አምነው ሞቱ፥ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል አላገኙምና፤ ዳሩ ግን ከሩቅ ሆነው አዩትና ተሳለሙት፥ በምድሪቱም እንግዶችና መጻተኞች እንዲሆኑ ታመኑ። እንዲህ የሚሉት ለእነርሱ የሚሆነውን አገር እንዲፈልጉ ያመለክታሉና። ያን የወጡበትን አገር አስበው ቢሆኑ፥ ሊመለሱ ጊዜ በሆነላቸው ነበር፤ አሁን ግን የሚበልጠውን እርሱም ሰማያዊ አገር ይናፍቃሉ። ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ በእነርሱ አያፍርም፥ ከተማን አዘጋጅቶላቸዋልና። አብርሃም በተፈተነበት ጊዜ ይስሐቅን በእምነት አቀረበ፥ የተስፋን ቃል የተቀበለው፦ በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃል የተባለለት እርሱም አንድ ልጁን አቀረበ፤ እግዚአብሔር ከሙታን እንኳ ሊያስነሣው እንዲቻለው አስቦአልና፥ ከዚያም ደግሞ በምሳሌ አገኘው። ይስሐቅ ሊመጣ ስላለው ነገር ያዕቆብንና ዔሳውን በእምነት ባረካቸው። ያዕቆብ ሲሞት በእምነት የዮሴፍን ልጆች እያንዳንዳቸው ባረካቸው፥ በዘንጉም ጫፍ ተጠግቶ ሰገደ። ዮሴፍ ወደ ሞት ቀርቦ ሳለ በእምነት ስለ እስራኤል ልጆች መውጣት አስታወሰ፥ ስለ አጥንቱም አዘዛቸው። ሙሴ ከተወለደ በኋላ ወላጆቹ ያማረ ሕፃን መሆኑን አይተው በእምነት ሦስት ወር ሸሸጉት የንጉሥንም አዋጅ አልፈሩም። ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ፤ ከግብፅም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለ ጠግነት እንዲሆን አስቦአልና ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ፤ ብድራቱን ትኵር ብሎ ተመልክቶአልና። የንጉሡን ቍጣ ሳይፈራ የግብፅን አገር የተወ በእምነት ነበር፤ የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶአልና። አጥፊው የበኵሮችን ልጆች እንዳይነካ ፋሲካንና ደምን መርጨትን በእምነት አደረገ። በደረቅ ምድር እንደሚያልፉ በኤርትራ ባሕር በእምነት ተሻገሩ፥ የግብፅ ሰዎች ግን ሲሞክሩ ተዋጡ። የኢያሪኮ ቅጥር ሰባት ቀን ከዞሩበት በኋላ በእምነት ወደቀ። ጋለሞታይቱ ረዓብ ሰላዮችን በሰላም ስለ ተቀበለቻቸው ከማይታዘዙ ጋር በእምነት አልጠፋችም። እንግዲህ ምን እላለሁ? ስለ ጌዴዎንና ስለ ባርቅ ስለ ሶምሶንም ስለ ዮፍታሔም ስለ ዳዊትና ስለ ሳሙኤልም ስለ ነቢያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛልና። እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፥ ጽድቅን አደረጉ፥ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ፥ የአንበሶችን አፍ ዘጉ፥ የእሳትን ኃይል አጠፉ፥ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፥ ከድካማቸው በረቱ፥ በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ፥ የባዕድ ጭፍሮችን አባረሩ። ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤ ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ፤ በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፥ ተፈተኑ፥ በመጋዝ ተሰነጠቁ፥ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፥ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ። እነዚህም ሁሉ በእምነታቸው ተመስክሮላቸው ሳሉ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አላገኙም፥ ያለ እኛ ፍጹማን እንዳይሆኑ እግዚአብሔር ስለ እኛ አንዳች የሚበልጥ ነገርን አስቀድሞ አይቶ ነበርና።                

No comments:

Post a Comment