እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው በመልኩና በአምሳሉ
ነው፡፡ ውስጠኛው ሰው የተፈጠረው እግዚአብሄርን መስሎ ነው ፡፡
እግዚአብሄር ላይ ባመፀ ጊዜ ሰው መንፈስ ከእግዚአብሄር
ተለየ፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር የነበረው የአባትና የልጅ ግንኙነት ተቋረጠ፡፡ ሰው እግዚአብሄርን የሚመስልበት መልኩ ጠፋ፡፡ ሰው የእግዚአብሄር
ህይወት ፍሬ የነበረውን ፅድቅ ሰላም ደስታ ፍቅር በጎነት የመሳሰሉትን ባህሪ አጣ፡፡
ሰው እግዚአብሄርን ባለመታዘዝ በሰይጣን ግዛት
ውስጥ ከወደቀ በኋላ እነዚህን የመንፈስ ፍሬዎች ሁሉ አጣ፡፡ ከእውነተኛው የህይወት ምንጭ ጋር ስለተለያየ እነዚህን የመንፈስ ፍሬዎች
ማፍራት ተሳነው፡፡ ከመልካምነት ግንድ ላይ ተቆርጦና ተለያይቶ መልካም ፍሬ የሚያፈራ ቅርንጫፍ የለም፡፡
ወንድሞቼ ሆይ፥ በለስ ወይራን ወይስ ወይን በለስን ልታፈራ ትችላለችን? ከጨው ውኃም ጣፋጭ ውኃ አይወጣም። ያዕቆብ 3፡12
ክርስትና እውነተኛ ህይወት ነው፡፡ ካለ እግዚአብሄር
እውነተኛን ፍሬ ማፍራት መሞከር ልፋት ነው፡፡
በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ። ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንዳይቻለው፥ እንዲሁ እናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ አትችሉም። እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና፡፡ ዮሐንስ 15፡4-5
ሰው የተጠራው እግዚአብሄርን ለመምሰል ነው፡፡
ሰው በኢየሱስ አዳኝነት ሲያምን ዳግመኛ ይወለዳል፡፡ ሰው እግዚአብሄር ያዘጋጀውን የመዳኛ መንገድ ሲቀበል መንፈሱ ህይወት ይዘራል፡፡
ህይወት ያለው ነገር ደግሞ አድጎ ፍሬ ማፍራቱ አይቀርም፡፡
አሁንም እግዚአብሄርን መምሰል የምንችለው በባህሪያችን
ፍሬ ነው፡፡ ከእውነተኛ ህይወት ጋር መገናኘታችን የሚታወቀው የመንፈስ ፍሬ በህይወታችን ሲታይ ነው፡፡
በክርስቶስ የእግዚአብሄርን ቃል ስንታዘዝ ፍሬን
ማፍራት እንጀምራለን፡፡ ለእግዚአብሄር ቃል አብዝተን በታዘዝን ቁጥር የመንፈስን ፍሬ በህይወታችን ይበዛል፡፡
ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር
እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል። ዮሐንስ 15፡5
የእግዚአብሄር ህይወት እንዳለንና ህይወታችን እያደገ
እንደሆነ የሚታየው የእግዚአብሄር ባህሪ የሆኑትን የመንፈስ ፍሬዎች ስናፈራና ፍሬዎቻችንም ሲበዙ ነው፡፡
የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው። ገላትያ 5፡22
ክርስትና
እውነተኛ ህይወት ነው፡፡ የመንፈስን ፍሬ አብዝተን ባፈራን መጠን ሰዎች ይህንን እውነተኛ ፍሬ ለመጠቀም ወደ እኛ ይሳባሉ፡፡ የመንፈስ
ፍሬ በህይወታችን በታየ መጠን ሰዎች እኛን መሆን ይፈልጋሉ እንዲሁም እኛ የምንከተለውን ጌታ ኢየሱስን መከተል ይፈልጋሉ፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች
https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች
https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #የመንፈስፍሬ #ፍቅር #ሰላም
#ደስታ #ዘር #ባህሪ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #የእግዚአብሄርህይወት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ
#በጎነት #የዋሃት #ራስንመግዛት #ትግስት #መሪ
No comments:
Post a Comment