Popular Posts

Saturday, December 31, 2016

ብቸኛው መመዘኛ

ለእግዚአብሄር ክብር እንደመፈጠራችን መጠን በህይወታችን ለእግዚአብሄር ብቻ መኖር እንፈልጋለን፡፡ የልባችን ጩኸት በእግዚአብሄር በልብና በሃሳቡ እንዳለ የእግዚአብሄርን ፈቃድ አድርጎ ማለፍ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ምኞት የለንም፡፡  ዳዊት በዘመኑ የእግዚአብሄርን ፈቃድ አገልግሎ አንቀላፋ ተብሎ እንደተመሰከረለት እንዲመሰከርልን እንፈልጋለን፡፡ በምድር ላይ የሚያረካን ለእግዚአብሄር ክብር መኖር ብቻ ነው፡፡
ታዲያ በስኬት ማገልገላችንና አለማገልገላችን የሚለካው እንዴት ነው የሚለውን ጥያቄ መመለስ አገልግለን በህይወት እንድናርፍ ያደርገናል፡፡ ከእኔ ምንድነው የሚጠበቀው? ከእኔስ ምንድነው የማይጠበቀው? የሚለውን ጥያቄ መልስ ማወቅ ሃላፊነታችንን በትኩረት እንድንወጣ ያስችለናል፡፡
አንድ ቀን ጉዞዋችንን ዞር ብለን ስናየው ለእግዚአብሄር በሚገባ የተኖረ ህይወት እንድናይ እንፈልጋለን፡፡ በመጨረሻ እግዚአብሄር "መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ" እንዲለን እንጠብቃለን፡፡
ግን እግዚአብሄር ህይወታችንን የሚመዝነው በምንድነው? መመዘኛው መስፈርት ምንድነው ?
እግዚአብሄር አፈፃፀማችንን የሚለካው ስለታማኝነታችን ነው፡፡ እግዚአብሄር የሚጠይቀን ስለሰጠን በእጃችን ላይ ስላለው ስጦታ እንጂ ስላልሰጠን ነገር አይደለም፡፡ እግዚአብሄር የሚጠይቀን በህይወታችን ስላስቀመጠው ስለሰጠን መክሊት ነው፡፡ እግዚአብሄር የሚጠይቀው እንዴት እግዚአብሄር ላይ በመደገፍ በታማኝነት የሰጠንን ነገር ማስተዳደራችንን ብቻ ነው፡፡
ጊዜ
የሰጠንን ጊዜ እንዴት በታማኝነት እንደተጠቀምንበት ይጠይቀናል፡፡ እግዚአብሄር በቀን ስለሰጠን 24 ሰአት እንጂ ስላልሰጠን 25 ሰአት አይጠይቀንም፡፡ የሰጠንን 24 ሰአት ግን እንዴት ለእግዚአብሄር ክብር እንደተጠቀምንበትና እግዚአብሄር በህይወታችን ላስቀመጠው ራእይና ሃላፊነትና እንዳዋልነው ታማኝነታችን ይለካል፡፡ እግዚአብሄር ያለው አንድና ብቸኛ መመዘኛ ታማኝነት ነው፡፡   
እውቀት
እግዚአብሄር የሰጠንን እውቀት ካለመሰሰት ለእግዚአብሄር መንግስት ተጠቅመንበታል? እግዚአብሄር እንዴት እውቀታችንን በታማኝነት እንደተጠቀምንበት ይለካል፡፡ ለተገለጠልን የፈቃዱ እውቀት ምን ያህል እየኖርን እንደሆነ ይፈትናል፡፡ ስላልተረዳነውና ስለማናውቀው የእግዚአበሄር ፈቃድ እንጠየቅም፡፡
የጌታውንም ፈቃድ አውቆ ያልተዘጋጀ እንደ ፈቃዱም ያላደረገ ያ ባሪያ እጅግ ይገረፋል፤ ያላወቀ ግን መገረፍ የሚገባውንም ያደረገ ጥቂት ይገረፋል። ብዙም ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል፥ ብዙ አደራም ከተሰጠው ከእርሱ አብዝተው ይሹበታል። ሉቃስ 12፡47-48
ገንዘብ
እግዚአብሄር ለመዝራትና ለመብላት የሰጠንን ገንዘብ እንዴት እያስተዳደርን እንዳለን እንጂ ስለሌለን ስለ ቢሊዮን ብር  አይጠይቀንም፡፡ የሰጠንን እንዴት እንዳዋልነው ግን ይጠይቀናል፡፡
እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፥ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም። ለዘሪ ዘርን ለመብላትም እንጀራን በብዙ የሚሰጥ እርሱም የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል ያበረክትላችሁማል፥ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያሳድጋል፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 9፡7፣10
ጉልበት
እግዚአብሄር የሰጠንን ማንኛውም ሃይል እንዴት እንደተጠቀምንበት ታማኝነታችንን ማየት ይፈልጋል፡፡ ያለንን ሃይልና ተሰሚነት የተጠቀምንበት ለመገንባት ይሁን ለማፍረስ ታማኝነታችንን ይለካል፡፡ ያለንን ሃይልና ጉልበት ለራሳችን ራስወዳድነት ወይም ለፍቅርና ለሌሎች ጥቅም እንዳዋልነው ማወቅ ይፈልጋል፡፡  
የሚያገለግልም ቢሆን፥ እግዚአብሔር በሚሰጠኝ ኃይል ነው ብሎ ያገልግል፤ ክብርና ሥልጣን እስከ ዘላለም ድረስ ለእርሱ በሚሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን። 1ኛ ጴጥሮስ 4፡11
የስኬታችን አንዱና ብቸኛው መመዘኛው እግዚአብሄር የሰጠን ማንኛውም መክሊት በመልካም የማስተዳደር ታማኝነታችን ነው፡፡
ጌታውም፦ መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። ማቴዎስ 25፡21
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ታማኝነት #መክሊት #ጊዜ #ጉልበት #እውቀት #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ምህረት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment