Popular Posts

Follow by Email

Wednesday, December 7, 2016

የህይወት ዛፍ ፍሬ

እግዚአብሄር ሰውን ሲፈጥረው በራሱ መልካምና ክፉን እንዲያውቅ አድርጎ አልነበረም የፈጠረው፡፡ ሰው ሲፈጠር እግዚአብሄርን እየሰማ እየታዘዘ እንዲኖር ነው፡ ሰው ሲፈጠር በየዋህነት እግዞአብሄርን እየተከተለ እንዲኖር ነው የተፈጠረው፡፡
ሰው የተፈጠረው በህይወት ዛፍ ፍሬ እንዲኖር ነው፡፡ ሰው የተፈጠረው አንድ ምሪት ብቻ በየዋህነት እንዲከተል ነው፡፡
እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው፦ ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና። ዘፍጥረት 2፡16-17
ሰው በሃጢያት ሲወድቅ መልካምና ክፉውን በራሱ እየመረጠ እንዲኖር ተገደደ፡፡ ሰው በራሱ ሆነ፡፡ ሰው በግምት ለመኖር ተገደደ፡፡ ሰው ለእግዚአብሄር አንድ ምሪት በየዋህነት የመመራትን እድሉን ሊያገኘው አልቻለም፡፡
ሰው ክፉና መልካምን በራሱ ለመለየት ስለመረጠ ከእግዚአብሄር ክብር ወደቀ፡፡ ሰው በእግዚአብሄር ብቻ የመመራት እድሉን አጣው፡፡ ሰው በአንዱ የህይወት ዛፍ ፍሬ የመኖር ነፃነቱን ተነፈገ፡፡ የሰው ህይወቱ ተከፋፈለ፡፡ የሰው ህይወቱ ተሰነጠቀ፡፡ ሰው የእግዚአብሄርን አላማ ሳተ፡፡
ሰው መልካም ነው ብሎ የሚያስበው ሁሉ መልካም አይደለም፡፡ ሰው ክፉ ነው ብሎ የሚያስበው ሁሉ ደግሞ ክፉ አይደለም፡፡ ስለዚህ ሰው በራሱ ምርጫ ባሪያ ሆነ፡፡
አሳቤ እንደ አሳባችሁ መንገዳችሁም እንደ መንገዴ አይደለምና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፥ እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ አሳቤም ከአሳባችሁ ከፍ ያለ ነው። ኢሳይያስ 55፡8-9
ኢየሱስ የሃጢያታችንን እዳ ከከፈለ በኋላ ግን እግዚአብሄር ወደ ቀድሞ አንዱ ምሪት ሊመልሰን የሚያስፈልገውን የሃጢያት እዳ ሁሉ በልጁ በኢየሱስ በኩል ከፈለ፡፡ አሁንም ኢየሱስን ስንቀበለው በልባችን መኖር ይጀምራል፡፡
የእግዚአብሄር ህይወት በልባችን ሲኖር በአእምሮዋችን "ይህ ክፉ ነው" "ይህ መልካም ነው" በሚል ብቻ በራሳችን ከመኖር እንወጣለን፡፡ በውስጣችን ያለውን የእግዚአብሄርን ህይወትን በየዋህነት ከተከተልን የእግዚአብሄር ወዳዘጋጀልን የክብር ደረጃ እንደርሳለን፡፡
በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና። ሮሜ 8፡2
"ይህ ክፉ ነው" "ይህ መልካም ነው" ብለን መምረጥ ሳያስፈልገን በውስጣችን ያለውን መንፈስ በመከተል ብቻ የእግዚአብሄርን ፈቃድ በሙላት በመፈፀም እግዚአብሄርን እናስደስተዋለን፡፡
እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋል፥ ሁሉንም ታውቃላችሁ። እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነተኛም እንደ ሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ። 1ኛ ዮሐንስ 2፡20፣27
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #መንፈስቅዱስ #የእውቀትዛፍፍሬ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ምሪት #ድምፅ #ቅባት #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #የህይወትፍሬ #መናገር #ቅባት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment