የአለም የአሰራር ስርአትና የእግዚአብሄር መንግስት አሰራር ፍፁም የተለያዩ ናቸው፡፡
የአለም አሰራር በፍፁም በራስ ወዳድነትና በስጋ ምኞት ላይ የተመሰረተ አሰራር ነው፡፡ የእግዚአብሄር መንግስት አሰራር ደግሞ በፍቅር ላይ የተመሰረተ ነው፡፡
ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም። 1ኛ ዮሐንስ 2፡15-16
ሰው በአለም ሲኖር ራሱ በራሱ ላይ ጌታ ሆኖ ነው የሚኖረው፡፡ ያመረውን ያደርጋል ያላመረውን አያደርግም፡፡ እግዚአብሄርን ያስደስታል ወይ? እግዚአብሄርን ያስቆጣል ወይ? ብሎ አያስብም፡፡ ምክኒያቱም በአለም የሚኖር ሰው እግዚአብሄር ጌታው አይደለም፡፡ በህይወቱ የእግዚአብሄርን ጌትነት ጥሎታል፡፡
የእግዚአብሄር መንግስት አሰራር ደግሞ በፍቅርና በፍቅር ላይ ብቻ የተመሰረተ ነው፡፡ የአለም አስተሳሰብና የእግዚአብሄር መንግስት አስተሳሰብ ፍፁም የተለያዩ ናቸው፡፡
አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ የምትል ናት። ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም፦ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የምትል እርስዋን የምትመስል ይህች ናት። ከእነዚህ የምትበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለችም። ማርቆስ 12፡30-31
በእግዚአብሄርት መንግስት ውስጥ የሚኖር ሰው በራሱ ላይ ጌታው እርሱ ራሱ ሳይሆን ጌታ ኢየሱስ ነው፡፡ እርሱ ያመረውን ሳይሆን ጌታ የወደደውን ነው የሚያደርገው፡፡ ጌታ አድርግ የሚለውን ያደርጋል፡፡ ጌታ ተው የሚለውን ይተዋል፡፡
የአለም አሰራርና ክርስትና አብረው የማይሄዱ በጣም የተለያየ አሰራር ስላላቸው ጌታን የሚቀበል ሰው ንስሃ መግባት አለበት፡፡ ጌታን የሚቀበል ሰው የአስተሳሰብ ለውጥ ካላመጣ በአለም በሚኖርበት አስተሳሰብ በእግዚአብሄር መንግስት ልኑር ካለ የማይሆን ነገር እየሞከረ ነው፡፡ ሰው ጌታን ሲቀበል የእግዚአብሄርን ቃል በመቀበል ከአለማዊ አስተሳሰብ ቀኝ ኋላ ዙር ብሎ ወደ ኋላ ካልዞረ እግዚአብሄር ያዘጋጀለት በረከት ውስጥ መግባት ያቅተዋል፡፡
ንስሃ ማለት ባዶ ሃይማኖታዊ ስርአት መፈፀም ሳይሆን አለማዊ አስተሳሰብ መለውጥ መንገድን መለወጥ ነው፡፡ ሰው በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ እንደ አለማዊነት አሰራር በመኖር ሊሳካለት አይችል፡፡
ሰው ወደጌታ ሲመጣ መጀመሪያ መረዳት ያለበት ሁለቱ መንግስታት ፍፁም የተለያዩ እንደሆኑና በአለማዊ አሰራር በእግዚአብሄረ መንግስት መቀጠል እንደማይቻል አስተሳሰቡን መለወጥ እንዳለበት ነው፡፡
እውነተኛ ንስሃ ያልገባና የአለምን አሰራር ጥሎ በእግዚአብሄር መንግስት አሰራር በቃሉ ለመኖር ልቡን ያላዘጋጀ ሰው በክርስትናው ሊዘልቅ አይችልም፡፡
ንስሃ ጌታን ስንቀበል የምናደርገው የአንድ ጊዜ ድርጊት ሳይሆን የህይወት ዘይቤ ነው፡፡ ንስሃ ጌታን ሲቀበል ብቻ የሚገባው ነገር ሳይሆን አለማዊ ሃሳቡን በእግዚአብሄር ቃለ ለመለወጥ ልብን ሁል ጊዜ ማዘጋጀት ነው፡፡ የንስሃ ህይወት አለማዊ አስተሳሰብን ጥሎ የእግዚአብሄርን ቃል ለመቀበል ትሁት መሆን ማለት ነው፡፡
ጌታ ኢየሱስን ተቀብሎ ለዳነ ሰው ወደበረከት መግቢያው ብቸኛው መንገድ የንስሃ ህይወት ነው፡፡ ሰው በማንኛውን ጊዜ እንደቃሉ ያልሆነውን ሃሳቡን ትቶ ለእግዚአብሄር ቃል የሚገዛ ልብ ከሌለው በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ሊባረክ አይችል፡፡
ሰው በማንኛውም ጊዜ የሚያውቀውን እውቀት ለእግዚአብሄር መንግስት እውቀት ለመተው የንስሃ ህይወት ያስፈልገዋል፡፡ ሰው በአለም ከኖረበት አስተሳሰብ ወደ እግዚአብሄር መንግስት አስተሳሰብ ለመለወጥ ሁሌ በትህትና ሊኖር ይገባዋል፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ንስሃ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #አለም #ሃጢያት #ድምፅ #ቅባት #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #የህይወትፍሬ #መናገር #ቅባት #ትግስት #መሪ
No comments:
Post a Comment