ብዙ ሰዎች በአመቱ መጀመሪያ ላይ ውሳኔን ይወስናሉ፡፡ በዚህ አመት እንደዚህ አደርጋለሁ ፣ እንደዚህ እሆናለሁና እንደዚህ አገኛሁ በማለት ለራሳቸው ቃል ይገባሉ፡፡ አንዳንዶቹ እንዳሉትም ማድረግም ይጀምራሉ ነገር ግን አይዘልቁበትም፡፡
ይህ በየአመቱ እየተደጋገመ የሚመጣ በውሳኔ አለመፅናትና የህይወት ለውጥ እጦት ታዲያ የውሳኔ እጥረት ነው ወይስ የሌላ ያሰኛል፡፡
ፍላጎት ብቻውን የሚያመጣው ነገር የለም፡፡ የዚህ ሁሉ ችግር የፍላጎት እጥረት ሳይሆን የራእይ እጥረት ነው፡፡ ፍላጎት በእውቀትና በመረዳት ሲሆን ወደ ፍሬያማነት ያደርሳል፡፡
ሰው የተፈጠረበትን አላማ ሲረዳ ፣ ራእይ ሲኖረውና ሰው የሚሄድበትን ሲያውቅ ሁል ቀን የውሳኔ ቀን ነው ሁል ቀን የተግባር ቀን ነው ሁልጊዜ የፍያማነት ቀን ነው፡፡
ሰው እግዚአብሄር ለምን እንደፈጠረው ከመፅሃፍ ቅዱስ ፈልጎ ሲረዳ ለመኖር ፣ ለመስራትና ለመለወጥ በቂ አቅም ይኖረዋል፡፡ ለተለየ አላማ እግዚአብሄር ወደ ምድር እንዳመጣው የተረዳ ሰው አላማውን ለመፈፀም የማይከፍለው ዋጋ አይኖርም፡፡ በህይወቱ ያለውን የእግዚአብሄርን አላማ የተረዳ ሰው ራእዩ እንዳይተኛ ይጎተጉተዋል፡፡
ለእግዚአብሔር እንደ ማለ፥ ለያዕቆብም አምላክ እንደ ተሳለ፦ በእውነት ወደ ቤቴ ድንኳን አልገባም፥ ወደ ምንጣፌም አልጋ አልወጣም፥ ለዓይኖቼም መኝታ ለሽፋሽፍቶቼም እንቅልፍ፥ ለጕንጮቼም ዕረፍትን አልሰጥም፥ ለእግዚአብሔር ስፍራ፥ ለያዕቆብ አምላክ ማደሪያ እስካገኝ ድረስ ብሎ። እነሆ፥ በኤፍራታ ሰማነው፥ በዱር ውስጥም አገኘነው። መዝሙር 132፡2-6
ሰው ለምን አገልግሎትና ስራ ወደ ምድር እንደመጣ ሲረዳ ስራውን ጨርሶ እግዚአብሄርን እስከሚያከብር አያርፍም፡፡
የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር፥ ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው። 2ኛ ቆሮንቶስ 11፡28
በምድር ያለበትን አላማ የተረዳ ሰው ከአላማው ሊያስተጓጉለው የሚመጣውን ማንኛውንም ነገር ይንቃል፡፡
የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። ዕብራውያን 12፡1-2
ሰው የተፈጠረበትን አላማ ከእግዚአብሄር ሲያገኝ የኋላውን በመርሳት ሁልጊዜ ወደፊት ይዘረጋል፡፡
ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ገና እንዳልያዝሁት እቈጥራለሁ፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ፥ በክርስቶስ ኢየሱስ ከፍ ከፍ ያለውን የእግዚአብሔርን መጥራት ዋጋ እንዳገኝ ምልክትን እፈጥናለሁ። ፊልጵስዩስ 3፡13-14
ህይወታችንን እግዚአብሄር በልቡና በሃሳቡ እንዳለ ለመምራት ራእይ ያስፈልገናል፡፡ ራእይ ሲኖረን የት እንደምንሄድ ስናውቅ ለህይወታችን ጉልበት ይሆነዋል፡፡ ህይወታችንን ለመለወጥ አቅም የሚሰጠን ጥሩ ነገር መፈለጋችን ሳይሆን እግዚአብሄር በህይወታችን ሊሰራ ያለውን መረዳትና ለተፈፃሚነቱ ከእግዚአብሄር ጋር አብሮ መስራት ነው፡፡
ኢየሱስ ግን፦ አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ ብሎ መለሰላቸው። ዮሃንስ 5፡17
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#እይታ #ራእይ #አላማ #ግብ #ውሳኔ #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ብርሃን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #መንገድ #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ
No comments:
Post a Comment