Popular Posts

Wednesday, December 21, 2016

ለክብሬም የፈጠርሁት


ክርስቲያን ሁሉ በህይወትህ የምትፈልገው አንድ ነገር ምንድነው ተብሎ ሲጠየቅ የሚመልሰው "እግዚአብሄርን ማክበር" የሚል ነው፡፡ ምንም እንኳን እግዚአብሄርን ማክበር የሚለው ንገግር ሰፊ ፣ ግልፅ ያልሆነና ተጨማሪ ማብራሪያ የሚያስፈልገው መልስ ቢሆንም ትክክለኛ መልስ ነው፡፡ የተሰራነውና የተፈጠርነው ለእግዚአብሄር ክብር ነው፡፡  
በስሜ የተጠራውን ለክብሬም የፈጠርሁትን፥ የሠራሁትንና ያደረግሁትን ሁሉ አምጣ እለዋለሁ። ኢሳይያስ 43፡7
ሁላችንም ልባችን የሚቃጠልለት እግዚአብሄርን የማክበር አላማ ግን ምንድነው ? በህይወታችን የምንፈልገው ምንድነው? እግዚአብሄር ማክበራችንንና አለማክበራችንን እንዴት እናውቃለን? እግዚአብሄርን ማክበራችን እንዴት ይመዘናል? እግዚአብሄርን ማክበራችን እንዴት እናሳካዋለን፡፡ እግዚአብሄርን ማክበር በተግባር ምን ማድረግ ነው? እግዚአብሄርን ማክበራችን እንዴት ይለካል? የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ እግዚአብሄር የማክበር አላማችንን ለማሳካት እጅግ ይጠቅመናል፡፡  
ለእግዚአብሄር ክብር መኖር ማለት
·         ለሌሎች መልካምን ማድረግ ነው

በምናደርገው መልካምነት የእግዚአብሄርን መልካምነት ማሳየት ማንፀባረቅ ነው፡፡ ከምድራዊ ሰዎች የእንካ በእንካ አሰራር የተለየ ከእግዚአብሄር ብቻ የሚገኝን በሁኔታዎች ላይ ያልተደገፈ መልካምነት በመኖር ለሰዎች ወደ እግዚአብሄር ማመልከት ነው፡፡ ሰዎች የእኛን ኑሮ አይተው ይህ የሰው ስራ አይደለም ብለው እግዚአብሄርን ራሱን እንዲያመሰግኑት ማድረግ ነው፡፡ ለሁሉም ሰው መልካምነትን በማሳየት የእግዚአብሄርን ታላቅ ችሎታ ማሳየት ነው፡፡

መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ። ማቴዎስ 5፡16

እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤ 1ኛ ጴጥሮስ 2፡9

·         የእግዚአብሄርን ስም መሸከም ማለት ነው

የእግዚአብሄር ስም በመልካም ሁሉ እንዲነሳ ሰዎች በእኛ ህይወት የእግዚአብሄርን ፍቅር እንዲያዩ ማድረግ ነው፡፡ በእኛ ምክኒያት የእግዚአብሄር ስም በክፉ አንዳይነሳ መጠንቀቅ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ስም ከፍ ብሎ እንዲታይ የሚያስፈልገውን መስዋእትነት ሁሉ መክፈል ነው፡፡ እግዚአብሄርን በሚገባ መወከል ማለት ነው፡፡

ጌታም፦ ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና ሂድ፤ ስለ ስሜ ስንት መከራ ሊቀበል እንዲያስፈልገው እኔ አመለክተዋለሁና አለው።ሐዋርያት 20፡15-16

·         ቃሉን በመታዘዝ ፍሬ ማፍራት ነው

ጌታን የምናከብርበትን መመሪያ የእግዚአብሄርን ቃል በመስማትና በመታዘዝ በዚያም ፍሬ በማፍራት ለእግዚአብሄርን ያለንን ፍቅርና አክብሮት ማሳየት ነው፡፡

በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል። ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ ብትሆኑ በዚህ አባቴ ይከበራል። ዮሐንስ 15፡7-8

·         ሃጢያትን መፀየፍ ከክፋት መሸሽ ነው፡፡

እግዚአብሄርን ማክበር ሃጢያትን በመፀየፍና በመሸሽ ቅዱስ የሆነውን እግዚአብሄርን በመምሰል ለቅዱሳን እንደሚገባ መኖር ነው፡፡ እግዚአብሄርን ማክበር ስጋችንን ሃጢያት በመከልከል እግዚአብሄርን ደስ ማሰኘት ነው፡፡

ለቅዱሳን እንደሚገባ ግን ዝሙትና ርኵሰት ሁሉ ወይም መመኘት በእናንተ ዘንድ ከቶ አይሰማ፤ ኤፌሶን 5፥3

ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ 6፡19-20

·         የእግዚአብሄርን ፍላጎት መፈፀም ማለት ነው

ከፍላጎታችን በላይ የእግዚአብሄርን ፍላጎት ማሟላት ፣ የእኛን ፍላጎት ወደጎን በማድረግ የእርሱን ፍላጎት ማስቀደም ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለማድረግ ራሳችንን መስጠት ማለት ነው፡፡ ከምንም ስሜታችን በላይ እግዚአበሄርን ለማስደሰት ቅድሚያ መስጠት ነው፡፡

ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ እያለ ይጸልይ ነበር። ሉቃስ 22፡42

·         እግዚአብሄርን ብቻ መፍራት ማለት ነው

እንድንፈራቸው የሚፈልጉ በጣም ብዙ ነገሮች ባሉበት አለም ውስጥ እግዚአብሄርን ብቻ መፍራት ፣ እግዚአብሄርን ከሌሎች ጌቶች ጋር አለመቀላቀል ፣ ብቻውን መያዝና በህይወታችን የመጀመሪያውን ስፍራ መስጠት እግዚአብሄርን ከፍ ማድረግ ነው፡፡

ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ አትናወጡም፥ ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 3፡14-15

·         እግዚአብሄርን ማመን ማለት ነው

በአካባቢያችን ያሉትን ነገሮች ባለማየት የማይታየውን እግዚአብሄርን በቃሉ ማመንና መታዘዝ ነው፡፡ ይህ በተፈጥሮ አይን የማይታየውን እግዚአብሄር በእኛ እንዲታይና እንዲከበር ያደርገዋል፡፡  

እንግዲህ ሁልጊዜ ታምነን፥ በእምነት እንጂ በማየት አንመላለስምና በሥጋ ስናድር ከጌታ ተለይተን በስደት እንዳለን የምናውቅ ከሆንን፥ 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡6-7

·         ገንዘብን አለመውደድ ነው

ገንዘብን ሁሉንም ነገር ሊገዛ እንደማይችል በጣም ውስን እንደሆነ መረዳታችን ፣ መኖሪያችን እግዚአብሄር እንጂ ገንዘብ እናዳይደለ ማወቃችን ፣ ከገንዘብ ይልቅ ወደጌታ መጠጋታችንና ገንዘብን መናቃችን እግዚአብሄርን ያከብረዋል፡፡
ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም። ማቴዎስ 6፡24

·         የነፍሳችንን ጥያቄ መርሳት ነው

ነፍሳችን ብዙ ጥያቄ አላት ፡፡ ጥያቄዋን ሁሉ ከሰማንና ከቃሉ በላይ ካከበርናት እግዚአብሄርን አናከብረውም፡፡ እግዚአብሄርን ለማክበር የነፍሳችንን ጥያቄና ጩኸት መርሳት ይጠይቃል፡፡ ከነፍሳችን በላይ ቃሉን መስማትና መታዘዝ እግዚአብሄርን በህይወታችን ያከብረዋል፡፡

የእግዚአብሄርን ነገር አክብዶ ለመያዝ የራስን ነገር ቀለል አድርጎ መያዝ ይጠይቃል፡፡ ለእግዚአብሄር ስራ ቅድሚያ ለመስጠት የነፍሳችንን ጥያቄ አለመስማትና ቸል ማለት ይኖርብናል፡፡

ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታልና፤ ስለ እኔ ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ግን እርሱ ያድናታል። ሉቃስ 9፡24

ነገር ግን ሩጫዬንና ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን አገልግሎት እርሱም የእግዚአብሔርን ጸጋ ወንጌልን መመስከር እፈጽም ዘንድ ነፍሴን በእኔ ዘንድ እንደማትከብር እንደ ከንቱ ነገር እቆጥራለሁ። ሐዋርያት 20፥24
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ክብር #ራእይ #አላማ #ግብ #ውሳኔ #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ብርሃን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #መንገድ #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

No comments:

Post a Comment