Popular Posts

Follow by Email

Friday, December 23, 2016

መንፈሳዊ ጤንነታችን የምንለካባቸው 12 መንገዶች

የክርስትና ህይወታችንን ስኬት የምንመዝነው የተመገብነውን ምግብ ጤንነት በማየት ነው፡፡ የምንሰማው ነገር ጤናማ ካልሆነ ህይወታችን የተሳካ ቢመስለን እንኳን እየቀጨጭን እንደሆንን ማወቅ አለብን፡፡ የምንበላውን ምግብ ጤንነት እርግጠኛ ከሆንን ደግሞ እያደግን እየለመልምን እንደሆነ እርግጠኛ እንሆናለን፡፡
በክርስቶስ ኢየሱስ ባለ እምነትና ፍቅር አድርገህ፥ ከእኔ የሰማኸውን ጤናማ ቃል ምሳሌ ያዝ፤ 2ኛ ጢሞቴዎስ 1፡13
የምንመገበውን ምግብ ጤንነት ለመገምገም የሚረዱ አስራ ሁለት መመዘኛዎች

·         የምሰማው ጤናማ ትምህርት በፍቅር እንድኖር ያበራታታል
የምንሰማው ትምህርት በፍቅር እንድኖር የማያበረታታ ከሆነና ፍቅርን በሌሎች መሰል ነገሮች የተካ ከሆነ ጤነኛ ምግብ እንዳልተመገብን ምልክቱ ነው፡፡ በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ በፍቅር ካልኖርንና ካላገለገልን በሁኔታዎች ተቋቁመን ማለፍና እግዚአብሄር የጠራንን የመንግስቱን ስራ ለረጅም ጊዜ ማገልገል ያቅተናል፡፡ የማንኛውም ትምህርት አላማ በፍቅር እንድኖር ማድረግ ነው፡፡    
የትእዛዝ ፍጻሜ ግን ከንጹሕ ልብና ከበጎ ሕሊና ግብዝነትም ከሌለበት እምነት የሚወጣ ፍቅር ነው፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 1፡5
·         የምንመገበው ጤናማ ትምህርት በእግዚአብሄር እንዳምን ይረዳል  

የምመገበው ምግብ በእምነት እግዚአብሄርን እንዳይ የሚታየውን የምድራዊውንና ጊዜያዊውን ነገር እንዳላይ ካበረታታኝ ጤነኛ ምግብ እንደተመገብኩ ማረጋገጫው ነው፡፡ 

የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፥ ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና፤ የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው። 2ኛ ቆሮንቶስ 4፡17-18

·         ጤናማ ትምህርት በትዕቢት እንድናስብ አያደርግም

አንዳንዴ የምንሰማው ትምህርት ራሳችንን በትክክል እንዳናይ ይጋርደናል፡፡ ትምህርቱ ከሆንነው በላይ በትቢት እንድናስብ ያደርጋል፡፡ ጤናማ ትምህርት ግን ከፍ ባልን ቁጥር ይበልጥ ትሁት እንድንሆን ያደርጋል፡፡ የምንሰማው ትምህርት ሌሎችን በአክብሮት እንድንይዝ ካላበረታታና ሌሎችን እንድንንቅ ካደፋፈረን የተሳሳተ ትምህርት ነው፡፡

እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው፥ እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ። ሮሜ 12፡3

·         ጤናማ ትምህርት ሰማያዊ ነገር ላይ እንዳተኩር ያደርጋል

የምንመገበው መንፈሳዊ ምግብ ሃሳባችን ምድራዊ እንዲሆ ካደረገ በልባችን ያለው ብርሃን እንዳያጠፋው መጠንቀቅ አለብን፡፡ የምንበላው ምግብ የሰማይን ሃሳብ ይበልጥ የሚያጎላው ካልሆነና በላይ ያለውን እንድንፈልግ ካልረዳን  ምግባችንን በፍጥነት መቀየር አለብን፡፡ 

እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፥ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ እሹ፤ በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም። ቆላስይስ 3፡1-2

·         ጤናማ አስተምሮት ለስኬትና ለብልፅግና እንድቸኩል አያደርግም
የምንማረው ትምህርት የእግዚአብሄርን ፅድቅና መንግስቱን እንድፈልግ ካላበረታታ ይልቁንም ለሁለት ጌቶች ለገንዘብና ለጌታ እንድንገዛ ካበረታታ እንዲሁም ስለኑሮ እንድንጨነቅ ካደረገ የተመገብነው ትምህርት ጤናማነት ያጠራጥራል፡፡ በታማኝነት የሚባርከውን የእግዚአብሄርን እርምጃ እንዳንታገስ ካደረገና በፍጥነት መበልፀግ እንደምንችል ካስተማረ የስህተት ትምህርት ነው፡፡ ጤናማ ትምህርት ያለኝ ይበቃኛል እንድንል ያሳርፋል፡፡
የታመነ ሰው እጅግ ይባረካል፤ ባለጠጋ ለመሆን የሚቸኵል ግን ሳይቀጣ አይቀርም። ምሳሌ 28፡20


·         ጤናማ ትምህርት መስማት በይቅርታና በምህረት እንድመላለስ ያደርጋል

የምመገበው ምግብ ሰዎችን እንድጠላ የሚያበረታታ ከሆነና በልቤ ቂምና ምሬትን እንዳልይዝ ካልገሰፀኝ ጤነኛ ትምህርት እየተመገብኩ አይደለም ማለት ነው፡፡ ጥላቻ የመንፈሳዊ ህይወትን ጤና የሚያስተጓጉል መርዝ በመሆኑ  የበደለንን ሁሉ ይቅር ማለት እንደምንችል የማያስተምር አስተምሮት ጤናችን እንዲጓደል ያደርጋል፡፡

መራርነትና ንዴት ቁጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ። እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፥ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ። ኤፌሶን 4፡31-32

·         ጤናማ ምግብ ለአገልግሎት ያነሳሳል 

የተወለድነው ወደ እግዚአብሄር ቤተሰብ ውስጥ ነው ፡፡ የክርስቶስ አካል ደግሞ ህያውና ሰራተኛ ነው፡፡ ስለዚህ የበላነውን ምግብ ጤነኝነት የምንመዝነው ከፊት ይልቅ ለአገልገሎት በመነሳታችን ነው፡፡ ለአገልግሎት ያለን ፍላጎት እየወረደ ከሆነ ጤነኛ ምግብ እየበላን አይደለንም፡፡ የምንመገበው ምግብ የአገልግሎትን ክብር ካላሳየንና አለምን ንቀን ጌታን አንድናገለግል ካላበረታታን የምንመገበው ምግብ ጤነኝነቱ ያጠራጥራል፡፡

ልዩ ልዩን የእግዚአብሔርን ጸጋ ደጋግ መጋቢዎች እንደ መሆናችሁ፥ እያንዳንዳችሁ የጸጋን ስጦታ እንደ ተቀበላችሁ መጠን በዚያው ጸጋ እርስ በርሳችሁ አገልግሉ፤ 1ኛ ጴጥሮስ 4፡10

·         የምመገበው ምግብ የሰውን ድካም የሚያጎላ መሆን የለበትም

የምንመገበው ምግብ የራሳችንን ከንቱነት የሚያጎላና የእግዚአብሄርን እርዳታ የማያሳይ ከለሆነ ለመንፈሳዊ ህይወት እድገታችን ከፍተኛ እንቅፋት ነው፡፡ በሚያስችለው በእግዚአብሄር ፀጋ ላይ ሳይሆን በእኛ ድካም ላይ የሚያተኩር ትምህርት አጉል ሃይማኖተኝነት እንጂ እውነተኛ ክርስትና አይደለም፡፡

በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ፤ ወይስ ምናልባት የማትበቁ ባትሆኑ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ እንዳለ ስለ እናንተ አታውቁምን? 2ኛ ቆሮንቶስ 13፡5

·         የምንመበው መልካም ትምህርት እንደ እንግዳና መጻተኛ እንድኖር ያደርጋል  

የምመገበው ምግብ በአለም ውድድር ውስጥ ተዘፍቄ የክርስትና አላማዬን እንዳልስት አድርጎኛል ወይ ብሎ መጠየቅ ብልህነት ነው፡፡ የምሰማው ትምህርት እንደ እንግዳና ምፃተኛ ራሴን ከአለም ጉድፍ እንድጠብቅና እግዚአብሄርን በማገልገል አላማና ጌታን በማክበር እንድኖር አድርጎኛል፡፡

ወዳጆች ሆይ፥ ነፍስን ከሚዋጋ ሥጋዊ ምኞት ትርቁ ዘንድ እንግዶችና መጻተኞች እንደ መሆናችሁ እለምናችኋለሁ፤ 1ኛ ጴጥሮስ 2፡11

·         የምንመገበው ትምህርት አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ መሆን የለበትም

የምመገበው ትምህርት የእግዚአብሄርን ሃሳብ በመረዳት በመንፈስ ቅዱስ እንድመራ ነፃነቱን የሚሰጠኝ ነው ወይስ እንደ መጀመሪያ ትምህርት በአትቅመስና አትንካ እስራት ውስጥ የሚጨምረኝ ነው ? የምመገበው ትምህርት በሃይማኖታዊ ስርአቶች ላይ ያተኮረ ብቻ ከሆነና በመንፈስ ቅዱስ በመመራት እግዚአብሄርን እንድናስደስት የማይለቅ ከሆነ የእድገት ጠር የሆነ ትምህርት ነው፡፡

እንደዚህ ያለ ሰው ራስ ወደሚሆነው አይጠጋም፥ . . .ከዓለማዊ ከመጀመሪያ ትምህርት ርቃችሁ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ፥ እንደ ሰው ሥርዓትና ትምህርት። አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ ለሚሉት ትእዛዛት በዓለም እንደምትኖሩ ስለ ምን ትገዛላችሁ? እነዚህ ሁሉ በመደረግ ሊጠፉ ተወስነዋልና።  ቆላስይስ 2፡20-22

·         የምሰማው ትምህርት ዘላለማዊ ህይወትን የሚያስይዝ መሆን ነው ያለበት
በምናደርገው በማንኛውም ውሳኔ ዘላለም እንደሚኖሩ ሰዎች በክርስቶስ የፍርድ ወንበር እንደምንቀርብ ሰዎች እነዶሆን የማያበረታታ ትምህርት ጤናማ ትምህርት አይደለም፡፡  

መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፥ የተጠራህለትንም በብዙም ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የታመንህለትን የዘላለምን ሕይወት ያዝ። 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡12

·         የምሰማው ንፁህ ትምህርት ወደ ክርስቶስ የሚያሳይ ነው

የትምህርትን ጤነኝነት አንደኛው መመዘኛ ትምህርቱ ወደ ክርስቶስ ማሳየቱ ወይም አለማሳየቱ ነው፡፡ ለሰው ክብርን የሚያመጣ ክርስቶስን የሚሸፍን ትምህርት ጤናማ ትምህርት አይደለም፡፡ ክብርን ለክርስቶስ የማያመጣ ማንኛውም ትምህርት ለጤናም ሆነ ለእድገት የማይጠቅም ትምህርት ነው፡፡
 
እርሱ ያከብረኛል፥ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና። ዮሃንስ 16፡14

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ክብር #ጤናማ #አላማ #ሰማይ #ዘላለም #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #መንገድ #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment