Popular Posts

Wednesday, December 28, 2016

የዝምታ አምልኮ

ከእግዚአብሄር ጋር ላለን ግንኙነት መጠናከር ጠቃሚ ከሆኑ የተለያዩ የጥሞና መንገዶች አንዱ ዝምታ ነው፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር ያለን ግንኙነት ስምረት የሚለካበት አንዱ መንገድ ዝምታ ነው፡፡
ስጋ ሁል ጊዜ መናገር ይፈልጋል፡፡ ስጋ የሚረካው በመናገር ነው፡፡ ስጋ በህይወት የመጡትን ተግዳሮቶች ለመፍታት የሚሞክረው በመናገር ብዛት ነው፡፡ ስለዚህ ነው አንዳንድ ጊዜ አልናገርም ብለን ስንወስን ስጋ ከውስጣችን ሲጮህና ሲቃወም የምንሰማው፡፡ ስጋ ራሱን የሚያረካው በመናገር ነው፡፡
ስጋ ዝም ማለትና ማረፍ አይፈልግም፡፡ ስጋ ነገሮችን በንግግር መቆጣጠር ይፈልጋል፡፡ ስጋ ለእግዚአብሄር ጊዜ መስጠት አይፈልግም፡፡ ስጋ ለእግዚአብሄር ስፍራን በመስጠት በዝምታ መጠበቅ አይፈልግም፡፡ ስጋ ዝምታን እንደ ሽንፈትና እንደ አቅመቢስነት ነው የሚያየው፡፡ አንደበቱን መግታት የማይችል ብዙ የሚለፈልፍ ሰው ካያችሁ በስጋው የተሸነፈ ሰው ነው፡፡
ተወዳጆች ሆይ፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፥ ለቍጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና። ሮሜ 12፡19
ፀጥታ የመታመን ምልክት ነው፡፡ ፀጥ የሚለው እግዚአብሄር የልብን ጩኸት ይሰማል የሚል ሰው ነው፡፡ ፀጥ የሚል ሰው የህይወት ቁልፉ እግዚአብሄር ጋር እንጂ ሰው ጋር እንደሌለ የሚያምን ሰው ነው፡፡ ፀጥ የሚል ሰው የሰው ቁጣ የእግዚአብሄርን ፅድቅ እንደማይሰራ (ያዕቆብ 1፡20) የተረዳ ሰው ነው፡፡ ያልታመነ ሰው ይናወጣል፡፡ ያላመነ ሰው በፀጥታ መቀመጥ አይችልም፡፡
የእስራኤል ቅዱስ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ በመመለስና በማረፍ ትድናላችሁ፤ በጸጥታና በመታመን ኃይል ይሆንላችኋል፤ ኢሳይያስ 30፡15
ሳንናወጥ በዝምታ እግዚአብሄርን መጠበቅ በእግዚአብሄር ላይ መደገፋችንን ያሳያል፡፡ በፀጥታ እግዚአብሄርን መጠበቃችን ለእግዚአብሄር ስፍራን መስጠታችንን ያሳያል፡፡ በፀጥታ መቀመጣችን "ካለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና" (ዮሐንስ 15፡5) ያለውን ቃል በማመን በእርሱ ላይ እርፍ ማለታችንን ያሳያል፡፡ ፀጥታችን እግዚአብሄር ምድርን እንደሚገዛ ማመናችንን ያሳያል፡፡
ዕረፉ፥ እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ እወቁ፤ በአሕዛብ ዘንድ ከፍ ከፍ እላለሁ፥ በምድርም ላይ ከፍ ከፍ እላለሁ። መዝሙር 46፡10
በዝምታ የሚኖር ሰው ሃይሉን ባላስፈላጊ መናወጥ አያባክንም፡፡ በእርግጥም በዝምታ እግዚአብሄርን የሚጠብቅ ሰው ሃይሉን እንደንስር ያድሳል፡፡
እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፥ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፥ አይደክሙም። ኢሳይያስ 40፡31
የምናድርበት መንገድ ነው፡፡ ዝምታ ለእግዚአብሄር የምናመልክበት መንገድ ነው፡፡ ዝምታ ለእግዚአብሄር የምንገዛበት መንገድ ነው፡፡
ከሁሉም በላይ ልንከተለው ስለሚገባው ስለኢየሱስ ዝምታ መፅሃፍ ቅዱስ ሲናገር እንዲህ ይላል፡፡
እነሆ የመረጥሁት ብላቴናዬ፥ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ወዳጄ፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፥ ፍርድንም ለአሕዛብ ያወራል። አይከራከርም አይጮህምም፥ ድምፁንም በአደባባይ የሚሰማ የለም። ማቴዎስ 12፡18-19

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ዝምታ #ማረፍ #መታመን #መደገፍ #ፀጥታ #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #መንገድ #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment