Popular Posts

Thursday, December 15, 2016

ይህን ያውቁ ኖሯል? የክሪስማስ እውነተኛ ትርጉም

ብዙ ሰው ክሪስማስን ሲያስብ እውነተኛ ትርጉሙን በፍፁም አያስበውም፡፡ ለአንዳንዱ የበአል ሰሞን ነው፡፡ ለሌላው አዲስ አመትን የሚቀበልበት የመጨረሻው ወር ነው፡፡ ለሌላው የክሪስማስ ስርአቶች የሚታዩበት ፣ ቤቶችና ሱቆች በክሪስማስ ዛፍ የሚያሸበርቁበት ፣ ቤትና አካባቢው በክሪስማስ መብራቶች የሚሽቆጠቆጥበት ወቅት ነው፡፡ ለሌላው ክሪስማስ የሚበላበትና የሚጠጣበት ከቤተሰብ ጋር የሚገናኙበት የአመቱ መዝናኛ ጊዜ ነው፡፡ እንዲሁ ለሌላው ክሪስማስ ልብስና ቁሳቁስ የሚለወጥበትና በአዲስ የሚተካበት ጊዜ ነው፡፡
ግን ክሪስማስ ይህ ብቻ ነው? ክሪስማስን ስናስብ ይህን ብቻ የምናስብ ከሆነ የክሪስማስን ዋናውን አላማ ስተነዋል፡፡ ክሪስማስ በዚህ ብቻ ካሰብነው ዋና ነገር በህይወታችን ጎድሏል ማለት ነው፡፡
እውነት ነው አለም ክሪስማስን ዋናው የንግድ ጊዜና የአመቱ ዋናው ንግድ ወቅት አድርጋዋለች፡፡ ክሪስማስ ዋናውን መልክቱን ከመሳቱ የተነሳ የክሪስማስ ዋናው ባለቤት አይጠቀስም፡፡
እወነት የክሪስማስ ትርጉሙና አላማው ይህ ነው? እኛ የምናከብረው ክሪስማስና ለልጆቻችን የምናስተላልፈው ክሪስማስ ይህ ነው?
እውነተኛውን የክሪስማስ ትርጉም እንመልከት፡፡  
ክሪስማስ የምስራች ነው
ሰው በሃጢያት ምክኒያት ከእግዚአብሄር ክብር ወድቆ በሃዘን በነበረበት ጊዜ የኢየሱስ መወለድ ታላቅ የምስራች ነው፡፡  
መልአኩም እንዲህ አላቸው፦ እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።  ሉቃስ 2፡10-11
ክሪስማስ  ስለተስፋ ይናገራል
ሰው ሁሉ በሃጢያት ከተስፋ ርቆ በነበረበት ጊዜ ለሰው ልጆች ብርሃን ሊሆን ኢየሱስ ወደምድር የመጣበት ኢየሱስ የተወለደበት በአል ነው፡፡ ክሪስማስ ኢየሱስ በመወለዱ የሰው ልጆች የመዳን ተስፋ እንደገና የለመለመበት ነው፡፡
ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። ማቴዎስ 1፡21
ክሪስማስ  ስለደህንነት ያውጃል
ለሃጢያት መድሃኒት የተወለደበት ጊዜ በመሆኑ ክሪስማስ መድሃኒት ነው፡፡
ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና። ሉቃስ 2፡11
ክሪስማስ ፍቅር ነው
ኢየሱስ ወደምድር የተወለደው ለእኛ ነፍሱን አሳልፎ ለመስጠት ነው፡፡
ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም። ዮሃንሰ 15፡13
ክሪስማስ ስጦታ ነው
የሰው ልጆች በሃጢያታቸው ምክኒያት ለዘላለም ከእግዚአብሄር እንዳይለያዩ ለሃጢያታቸው እዳ እንዲከፍል እንድያ ልጁን ለአለም በስጦታ የሰጠበት በዓል ነው፡፡
በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዮሐንስ 3፡16
ክሪስማስ የብርሃን ጊዜ ነው
የአለም ብርሃን የሆነው የኢየሱስ መወለድ ለአለም በጨለማ ውስጥ የበራ ብርሃን ነው፡፡
በነቢዩም በኢሳይያስ፦ የዛብሎን ምድርና የንፍታሌም ምድር፥ የባሕር መንገድ፥ በዮርዳኖስ ማዶ፥ የአሕዛብ ገሊላ፤ በጨለማ የተቀመጠው ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፥ በሞት አገርና ጥላ ለተቀመጡትም ብርሃን ወጣላቸው የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ። ማቴዎስ 4፡14-16
ክሪስማስ መስዋእትነት ነው
ኢየሱስ በእግዚአብሄር መልክ ሲኖር ሳለ ስለእኛ ሃጢያት ሰው ሆነ፡፡ ኢየሱስ እኛን ከበደል ለማዳን ከሰው ተወለደ፡፡
ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ፊልጵስዩስ 2፡7-8
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ገና #በዓል #ፍቅር #ተስፋ #ደስታ #መስዋእት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ብርሃን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  #የዋህነት #ንፁህ

No comments:

Post a Comment