Popular Posts

Thursday, December 1, 2016

የአስቸኳይ ጊዜ ፀሎት

ፀሎት ሁል ጊዜ የምናደርገው ደስ የምንሰኝበትና የምንረካበት የህየወት ዘይቤ እንጂ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አይደለም፡፡ ሁል ጊዜ ወደእርሱ እንድንቀርብ እግዚአብሄር ይፈልጋል፡፡
በመፅሃፍ ቅዱስ የእግዚአብሄርና የህዝቡ ግንኙነት እንደባልና ሚስት ግንኙነት ጊዜ ተጠቅሶ እናገኘዋለን፡፡ ይታያችሁ ሚስት ባልዋን የምትፈልገውና ከባልዋ ጋር የምታወራው ከባልዋ የሆነ ነገር ስትፈልግ የሆነ ፣ ልክ የፈለገችውን ስታገኝ ደግሞ ብትለየው ፣ እንደገና ባልዋን የምትፈልገው ደግሞ ከባልዋ የምትፈልገው ሌላ ነገር ሲገኝ ብቻ ቢሆን ይህ ጤናማ ትዳር አይደለም፡፡
ባልና ሚስት ከሁሉም በላይ ወዳጆችና ጓደኛሞች ናቸው፡፡ የባልና ሚስትን ትልቁን ድርሻ የሚይዘው አብሮነትና ፣ ማውራትና መነጋገር ነው፡፡ አንድ ልጅ አባቱን የሚያናግረው ከአባቱ የሆነ ነገር ሲፈልግ ብቻ ቢሆን ይህ የተበላሸ የአባትና የልጅ ግንኙነት እንደሆነ በቀላሉ እናስተውላለን፡፡ ምክኒያቱም ልጅ አባቱን የሚፈልገው ለአንድ ነገር ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ነገር ሁልጊዜም ነው፡፡ አባት ልጁን ማየት ይፈልጋል ፣ ከልጁ ጋር ማዋራት ይፈልጋል ፣ ከልጁ ጋር መጫወት ይፈልጋል፡፡ ከልጁ ጋር አብሮ መቀመጥ ጊዜ ማሳለፍ ይፈልጋል፡፡ አባት ልጁን ይራበዋል ይናፍቀዋል፡፡
እንደዚሁ እግዚአብሄር እኛን ልጆቹን ይራበናል ይጠማናል ይናፍቀናል፡፡ ለእርሱ ጊዜ እንድንሰጥ ይፈልጋል፡፡ እርሱና እኛ ብቻ የምንገናኝበትን ጊዜ እንድናዘጋጅለት ይፈልጋል፡፡ ትኩረታችን እንድንሰጠው ይፈልጋል፡፡ በእኛና በእርሱ መካከል ምንም ነገር ጣልቃ እንዲገባ እግዚአብሄር አይፈልግም፡፡
እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ መንፈስ ቅዱስ፦ በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ አለ። ሐዋርያት 13፡2
ከዚህ የመፅሃፍ ቅዱስ ክፍል እንደምንረዳው እነዚህ ሰዎች የተለየ የፀሎት ርእስ እንደነበራቸው የሚያሳይ ምንም ነገር የለም፡፡ ራሳቸውን ለይተው በእግዚአብሄር ፊት ነበሩ፡፡ እግዚአብሄርን ይጠብቁ ነበር፡፡ ለእግዚአብሄር ሙሉ ትኩረታቸውን በመስጠት ከእርሱ ጋር ህብረት ያደርጉ ነበር፡፡ አንድ አስተናጋጅ ተመጋቢ ጋር ቀርቦ ምን ይጠጣሉ ምን ይበላሉ እንዴት ይሁንሎት ብሎ እንደሚጠይቅና ተመጋውን ለማስደሰት እንደሚጠብቅ እንደሚያገለግለውም እነርሱም በእግዚአብሄር ፊት ይቆዩ ይጠብቁ ነበር፡፡
እግዚአብሄር የሚፈልገውን ለማድረግ ተዘጋጅተው ይሰሙት ነበር፡፡ ጊዜያቸውን ለእግዚአብሄር ሰጥተው በፊቱ ነበሩ፡፡ እግዚአብሄርን ያመልኩ ነበር ከፍ ከፍ ያደርጉት ያወድሱት ነበር፡፡
የምንጠይቀው ነገር ሲኖር ብቻ መሆን የለበትም እግዚአብሄርን መፈለግ ያለብን፡፡ ከመሬት ተነስተን የእግዚአብሄርን ፊት መፈለግ አለብን፡፡ የፀሎት ጥያቄ ባይኖረንም እግዚአብሄርን ማምለክና በፊቱ መቆየት ይጠበቅብናል፡፡ ከእርሱ ጋር ህብረት ለማድረግ ብቻ ከእርሱ ጋር መሆን ያስፈልገናል፡፡ በሌሎች ነገሮች ላይ ባተሌ በመሆን እግዚአብሄርን አለመፈለግ በቂ ምክኒያት አይደለም፡፡ ለእግዚአብሄር ጊዜ ላለመስጠት ለምናቀርበው ማንኛውም ምክኒያት እግዚአብሄር አያጨበጭብልንም፡፡ ለምንም ነገር ባተሌ ብንሆን ለእግዚአብሄር ባተሌ መሆን ተቀባይነት የሌለው ሰንካላ ምክኒያት ነው፡፡
የእኛን ኑሮ ለማሸነፍ በሚል እግዚአብሄርን ችላ ማለት እግዚአብሄር የማይቀበለው ሰንካላ ምክኒያት ነው፡፡ ኑሮህን ለማሸነፍ የምረዳን እኔን ፈልገኝ ነው የሚለው እግዚአብሄር፡፡ ሌላ የምንፈልገውን ትተን እግዚአበሄርን ስንፈልግ ሌሎች ፍላጎቶቻችን ይሟላሉ፡፡ እግዚአብሄርን መፈለግ ትተን ሌሎች ነገሮችን ስንፈልግ የህይወት አላማችን እንጎድላለን፡፡
እግዚአብሄር የፈጠረን ለእርሱ ክብር ነው፡፡ እግዚአብሄ የፈጠረን ዋናው አላማ ከእርሱ ጋር ህብረት እንድናደርግ ነው፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር ህብረት እንዳናደርግ ምንም ምክኒያት ካገኘን ከህይወት ዋናው ግባችን እንደወደቅን ማረጋገጫው ነው፡፡
እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው ቤተሰብ ፈልጎ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሰውንም በመልኩና በአምሳሉ የፈጠረው ካለምንም እንቅፋት ከሰው ጋር ህብረትን ለማድረግ ነው፡፡
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ራእይ #ፀሎት #እግዚአብሄርንመፈለግ #መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ጥሪ #አላማ #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ግብ #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment