Popular Posts

Follow by Email

Wednesday, March 29, 2017

ያለመናከል ቁልፎች

የክርስትና መንገድ ጀምረው የተሰናከሉ ልባቸው የቀዘቀዘና ወደሃላ የቀሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ለመሰናከል ግን ምንም አይነት ጥሩ ምክኒያት የለም፡፡ እግዚአብሄር በምንም ነገር እንዳንሰናከል ይፈልጋል፡፡   
በክርስትና ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት ጥበብና ጥንቃቄ የሚጠይቅ ነው፡፡ ከሰው ጋር እንዴት እንደምንኖር ማወቅ ከፍ ካሉ እውቀቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ በተለይ በሰዎች ላለመሰናከል መማር ረጅም መንገድ እንድንጓዝ ይረዳናል፡፡ እግዚአብሄር በነፃነት እንድናገለግለው ይፈልጋል፡፡
ከመሰናከል ተጠብቀን እግዚአብሄርን በሙላት እንድናገለግል የሚረዱ ሶስቱን መንገዶች እንመልከት፡፡
1.      ከሰው አለመጠበቅ

ብዙ ሰዎችን የሚያሰናክላቸው ከሰዎች መጠበቅ ነው፡፡ ሰዎች ምንም ሊያደርጉልን አይችሉም፡፡ ሰዎችን እግዚአብሄር ካልተጠቀመባቸው ምንም ሊያደርጉልን አይችሉም፡፡  እግዚአብሄር በጊዜው የተጠቀመባቸው ሰዎች ደግሞ ያላሰብነውንና ያልገመትነውን ነገር ሲያደርጉልን እናያለን፡፡ ላለመሰናከል ከሰው አለመጠበቅ ወሳኝ ነው፡፡ ከሰው ባልጠበቅን መጠን ሰው ባላደረገልን ጊዜ መሰናከላችን በእጅጉ ይቀንሳል፡፡ ከሰው በጠበቅን መጠን ሰው መልካም ባላደረገልን ጊዜ መሰናከላችን እንዲሁ ይጨምራል፡፡

እኛም እንዲሁ ለሰው የምናደርገው እግዚአብሄር ስለተጠቀመብን ብቻ እንደሆነ መርሳት የለብንም፡፡ ሰው መልካም ሊያደርግልን ቢጨነቅም እግዚአብሄር ካልተጠቀመበት ከመጨነቅ ውጭ ምንም ሊያደርግልን አይችልም፡፡

እግዚአብሔርን፦ አንተ ጌታዬ ነህ አልሁ፤ ከአንተ በቀር በጎነት የለኝም። መዝሙር 16፡2

2.     ሰዎችን ጌታን በሚመስሉበት የህይወት ክፍላቸው ብቻ መከተል

ከመፅሃፍ ቅዱስ ቀጥሎ የሰዎች ህይወት ጌታን እንዴት እንደምንከተል ብዙ ጥበብን ይሰጠናል፡፡  ጌታን በሚመስሉበት የህይወታችው ክፍላቸው ሰዎች መከተል መፅሃፍ ቅዱሳዊ ነው፡፡ ነገር ግን ሰዎችን ሙሉ ለሙሉ መከተል ለመሰናከል ራስን መጋበዝ ነው፡፡

እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ። 1 ቆሮንቶስ 11፡1

3.     እኛ ለሰዎች በምናደርገው ነገር ላይ ብቻ ማተኮር
መፅሃፍ ቅዱስ ለተሳካ የክርስትና ህይወት
ጤናማ ያልሆነ በሌላ ሰው ላይ መደገፍ ለክርስትና ህይወት ጠንቅ እንደሆነ መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምታል፡፡ ሁለቱም አንድ  ስጋ ይሆናሉ የተባሉት ባልና ሚስት እንኳን አንዳቸው በአንዳቸው ላይ ጤናማ ያልሆነ መደገፍ እንዳይኖራቸው መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡  
ዳሩ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እናገራለሁ፤ ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ፥ የሚያለቅሱም እንደማያለቅሱ፥ ደስ የሚላቸውም ደስ እንደማይላቸው፥ የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው፥ በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና። 1ኛ ቆሮንቶስ 7፡29-31
እንድትወስዱባቸው ተስፋ ለምታደርጉአቸው ብታበድሩ፥ ምን ምስጋና አላችሁ? ኃጢአተኞች ደግሞ በትክክል እንዲቀበሉ ለኃጢአተኞች ያበድራሉ። ሉቃስ 6፡34
4.     በሰው ላይ እንድትደገፍ የሚያደርጉህን ነገሮች በፍጥነት ማስወገድ  
በሰው ላይ እንድንደገፍ የሚያደርጉን ነገሮች በቀነሱና ራሳችንን በቻልን ቁጥር የመሰናከያ ምክኒያቶች ይቀንሳሉ፡፡
ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ከፊት ይልቅ ልትበዙ፥ በጸጥታም ትኖሩ ዘንድ ልትቀኑ፥ የራሳችሁንም ጉዳይ ልትጠነቀቁ፥ እንዳዘዝናችሁም፥ በውጭ ባሉት ዘንድ በአገባብ እንድትመላለሱ፥ አንዳችም እንዳያስፈልጋችሁ በእጃችሁ ልትሠሩ እንለምናችኋለን። 1ኛ ተሰሎንቄ 4፡11-12
5.     አይናችንን በጌታ ላይ ማድረግ

ሰዎችን እግዚአብሄር ሲጠቀምባቸው እናያለን፡፡ ሰዎችን እግዚአብሄር ሲጠቀምባቸው ባየን መጠን እግዚአብሄር ስለተጠቀመባቸው ብቻ መሆኑን መርሳት የለብንም፡፡ ሰዎች የመልካምነት ምንጭ አይደሉም፡፡ የመልካምነት ብቸኛ ምንጭ እግዚአብሄር ነው፡፡ ኢየሱስ በምድር ላይ ሰው ሆኖ በተመላለሰ ጊዜ ቸር መምህር ሲሉት አይናቸውን ከስጋ ለባሽ ላይ አንስተው የቸርነት ምንጩ ላይ እንዲያደርጉ አስተምሮዋል፡፡
           ኢየሱስም፦ ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም። ሉቃስ 18፡19
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #አትሰናከሉ #ነፃነት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #አርነት #ሃላፊመልክ #ቃል #ማሰላሰል #ጌታንማየት #ከሰውአለመጠበቅ #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ 

No comments:

Post a Comment