Popular Posts

Sunday, March 19, 2017

ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛል


ነገር ግን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ። ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፥ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፤ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም። በመንፈስ ብትመሩ ግን ከሕግ በታች አይደላችሁም። ገላትያ 5፡16-18
ክርስትና ባዶ የሃይማኖት ስርአትን የመጠበቅ ወግ አይደለም፡፡ ክርስትና ህይወት ነው፡፡ ክርስትና የመንፈስና የስጋ እውነተኛ ትግል ነው፡፡
እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና፥ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ። ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም ተስኖታል፤ ሮሜ 8፡5-7
የመንፈስንና የስጋን ምኞት ማወቅ ይጠቅመናል፡፡
ሰባቱ የስጋና የመንፈስ ምኞት ልዩነቶች
የስጋ ፈቃድ ለእግዚአብሄር ህግ የመገዛት ሃሳብ አይደለም፡፡ ስጋ ለእግዚአብሄር ፈቃድ ግድ የለውም፡፡
ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም ተስኖታል፤ ሮሜ 8፡7
የስጋ ፈቃድ ለጊዜው ራስን ማስደሰት ነው፡፡ የመንፈስ ፈቃድ እግዚአብሄርን ማስደሰት ነው፡፡
ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም። 1ኛ ዮሐንስ 2፡15-16
የስጋ ፈቃድ በሚታይ ነገር መመካት ነው፡፡ የመንፈስ ፈቃድ በማይታየው በእግዚአብሄር መንግስት አሰራር መመካት ነው፡፡  
ሥጋን የለበሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ። ነገር ግን፦ የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ ተብሎ እንደ ተጻፈው ይሆን ዘንድ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ጽድቅ ቅድስናም ቤዛነትም በተደረገልን በክርስቶስ ኢየሱስ የሆናችሁ ከእርሱ ነው። 1ኛ ቆሮንቶስ 1፡29-31
የስጋ ፈቃድ በምድር ላይ በቅንጦት መኖር ነው፡፡ የመንፈስ ፈቃድ መሰረታዊ ፍላጎትን አሟልቶ ጌታን መከተል ነው፡፡  
በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን? ትመኛላችሁ ለእናንተም አይሆንም፤ ትገድላላችሁ በብርቱም ትፈልጋላችሁ፥ ልታገኙም አትችሉም፤ ትጣላላችሁ ትዋጉማላችሁ ነገር ግን አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም፤ ትለምናላችሁ፥ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁና አትቀበሉም። ያዕቆብ 4፡1-3
እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፥ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ እሹ፤ በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም። ቆላስይስ 3፡1-2
የስጋ ፈቃድ እኔ የእኔ ለእኔ ነው፡፡ የመንፈስ ፈቃድ ሌላውን ማገልገል ሌላውን መጥቀም ነው፡፡
ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤ እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፥ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ። ፊልጵስዩስ 2፡3-4
የስጋ ፈቃድ ምድራዊ ነገር ላይ ያተኮረ ነው፡፡ የመንፈስ ፈቃድ ከምድራዊ ውድድር ወጥቶ ለሰማያዊው አገር ለመስራት ነው፡፡
መጨረሻቸው ጥፋት ነው፥ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው። እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፥ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፤ ፊልጵስዩስ 3፡19-20
የስጋ ፈቃድ እውነት በሚመስል ማታለያው ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ የመንፈስ ፈቃድ ግን እውነተኛ ትክክለኛውን ነገር በማድረግ ላይ ያተኮረ ነው፡፡
ነገር ግን መራራ ቅንዓትና አድመኛነት በልባችሁ ቢኖርባችሁ፥ አትመኩ በእውነትም ላይ አትዋሹ። ይህ ጥበብ ከላይ የሚወርድ አይደለም፤ ነገር ግን የምድር ነው፥ የሥጋም ነው፥ የአጋንንትም ነው፤ ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ስራ ሁሉ አሉና። ያዕቆብ 3፡14-16
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #በክርስቶስ #መንፈስ #የእግዚአብሄርንእይታ #ስጋ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ማየት #በስጋደረጃ #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አዲስፍጥረት #ክርስቶስ #ስፍራ #ማእረግ #ስልጣን

No comments:

Post a Comment